Saturday, 14 June 2014 11:48

ማዕከሉ ከሚቀበላቸው ህፃናት አብዛኞቹ በቤተዘመድ ተደፍረው ይመጣሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

አራት ሺህ ገደማ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እርዳታ አግኝተዋል

         ሙሉ አህመድ ትባላለች፡፡ የ15 ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ የት እንደተወለደች አታውቅም፡፡ ራሷን ያገኘችው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ከዚያም እንደ እናት ልጅ የምታያት ዘመዷ ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው፡፡ “ዘመዴ የምትሄድበት ሁሉ ይዛኝ ትሄድ ነበር፤ አንድ ቀን ግን ቤተሰብ ለመጠየቅ ገጠር ስትሄድ ይዛኝ መሄድ አልቻለችም” የምትለው ሙሉ፤ የዘመዷ ባልና እሷ ብቻ ቤት ውስጥ መቅረታቸውን ትናገራለች፡፡
መጀመሪያውኑም  የዘመዴ ባል አመለካከቱ ጥሩ ስላልነበር እፈራው ነበር ያለችው ሙሉ፤ የዚያን እለት ውጭ አምሽቶና ጠጥቶ ነበር የመጣው” ትላለች፡፡ ራቱን ጠረጴዛ ላይ አድርጋለት መኝታ ቤቷን ቆልፌ ልትተኛ ስትል ቁልፉን በሩ ላይ አጣችው፡፡ ቁልፉን ማን እንደወሰደው ያወቀቸው ግን በኋላ ነው፡፡
የዘመዷ ባል የሚስቱ አለመኖር የሰጠውን ነፃነት በመጠቀም እንዳሻው መናገር እንደጀመረ ታስታውሳለች፡፡ “ድሮም አንቺን እንጂ እህትሽን ፈልጌ አይደለም እዚህ የምኖረው” አለኝ ትላለች፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፡፡ “ብዙ ታግሎና ደብድቦ፣ ደፈረኝና ቤቱን ጥሎ ወጣ፡፡ እኔም ለሰዎች ነግሬ ወደዚህ ማዕለል መጣሁ” በማለት ለአስገድዶ መደፈር ያጋለጣትን ያንን ክፉ አጋጣሚ ትናገራለች። ከአራት ወር በፊት የተፈፀመባት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል፤ ለስነ ልቦና ቀውስ፣ ለትምህርት ማቋረጥና መሰል ችግሮች እንደዳረጋት የምትናገረው ሙሉ፤ ዘመዴም ይህን ጉድ በስልክ ስትሰማ ወደ ቤቷ ሳትመለስ በዛው ጠፍታ ቀረች፤ በዚህ በዚህ ከፍተኛ ብስጭትና ምሬት ይሰማኛል ብላለች፡፡
“ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ለአራት ዓመታት ትምህርቴን አቋርጫለሁ፤ አሁን ደግሞ በዚህ ምክንያት ለአምስተኛ ጊዜ ማቋረጤ ነው” የምትለው ሙሉ፣ እስካሁን 10ኛ ክፍል እደርስ ነበር ስትል ትቆጫለች፡፡ አስገድዶ የደፈረኝ ሰው ተይዞ በዋስ ከተለቀቀ በኋላ፣ ፍ/ቤት የተለያየ ቀጠሮ ቢኖረውም እስካሁን ሊቀርብ አልቻለም፤ አሁንም ሰኔ 11 ፍርድ ቤት ቀጠሮ አለኝ ብላለች፡፡
 የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ህፃናት ተሀድሶና ማቋቋሚያ ድርጅት (አፕሪፍስ) እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በጎዳና ላይ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴት ህፃናት ለመታደግ የተቋቋመ ሲሆን ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ማዕከሉ ከሚመጡት ህፃናት 34 በመቶው በቤተሰቦቻቸው የጾታ ጥቃት የተፈፀመባቸው እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡
ድርጅቱ፤ ለተሀድሶ ወደ ማዕከሉ  የመጡ 34 ተጠቂ ሴት ህፃናትን ለአራት ወራት በፀጉር ሙያ አሰልጥኖ ባለፈው ረቡዕ ድንበሯ ሆስፒታል ፊት ለፊት በሚገኘው ቢሮው ያስመረቀ ሲሆን በዕለቱ በቀረበው ጥናት፤ ወደ ማዕከሉ ከሚመጡት ህፃናት ውስጥ እንደ ሙሉ አህመድ በቤተ ዘመድ የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው በቁጥር እንደሚልቁ ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ ላለፉት 14 ዓመታት ወደ ማዕከሉ ለመጡ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ሴት ህፃናት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠቱንም የድርጅቱ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዝናሽ በዛብህ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳርና በሻሸመኔ እንዲሁም በመተማ ዮሐንስ ወደ ሱዳን ለሚሄዱና ከሱዳን ለሚመለሱ ሴት ህፃናት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ጥቃት ደርሶባቸው ሲመጡ የምግብ፣ የመኝታ፣ የልብስ፣ የንፅህና መጠበቂያና መሰል አገልግሎቶችን ለህፃናቱ ያቀርባል፡፡ የህይወት ክህሎት ስልጠናና የስነ - ልቦና የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡
ድርጅቱ የተጠቁ ህፃናት ጉዳያቸው በፍ/ቤት ተይዞ ቀጠሮ ሲኖራቸው፣ ወደ ፍ/ቤት የማድረስ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በዋናነት የጠፉ ቤተሰቦቻቸውን በማፈላለግ ማቀላቀል፣ ከተቀላቀሉም በኋላ ለተከታታይ ሶስት አመታት ክትትል ማድረግ በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ዘርፍ ነው፡፡ በወንድም፣ በአባት እና በቅርብ ዘመድ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት፤ ተመልሰው ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀል ስለማይችሉ፣ የአደራ ቤተሰብ ተፈልጐ ይሄዳሉ ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በአደራ ቤተሰብ ውስጥ እያሉም ክትትል እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ፤ ህፃናቱ ለምን ወደ ጐዳና እንደሚወጡ ለማወቅ ባካሄደው ጥናት፤ 34 በመቶው በወሲብ ጥቃት፣ 27 በመቶው በቤተሰብ የከፋ ድህነት፣ 19 በመቶው በህገ ወጥ ዝውውር፣ 16 በመቶው በጉልበት ብዝበዛና መሰል ችግሮች ለጐዳና ላይ ጥቃት እንደሚጋለጡ የድርጅቱ ክትትልና ግምገማ ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሽብሩ ገልፀዋል፡፡
ዓምና ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ማዕከሉ የመጡ 106 ህፃናት የህግ ጉዳይ ምን እንደሚመስል በተደረገው ጥናት፤ 23 ሰዎች ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን ማስረጃ በማጣት የህግ ሂደት የተቋረጠባቸው 29 ልጆች፣ በባህላዊ ድርድር ጉዳያቸው የተፈታ 13 ልጆችና ያለ እድሜያቸው ተጋብተው ሲኖሩ ደፈረኝ ብለው ከሰው ሲያበቁ 18 ዓመት ሲሞላቸው በፍ/ቤት ውሳኔ አብረው ከፍቅረኞቻቸው ጋር እንዲቀጥሉ የተደረጉ 4 ሴቶች እንዳሉም ተረጋግጧል፡፡
አንዲት ጥቃት የደረሰባት ሴት የተሃድሶ አገልግሎት፣ የስነ - ልቦና ምክር እና ማረጋጋት ተደርጐላት ቢያንስ አራት ወር በማዕከሉ እንደምትቆይ የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ ማዕከሉ በዓመት 600 ያህል ጥቃት የደረሰባቸውን ሴት ህፃናት የመቀበል አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በአዲስ አበባ ሁለት መጠለያዎች ያሉት ሲሆን ለማዕከል መገንቢያ ቦታ አለማግኘትና የቤት ኪራይ ውድነት ስራውን ፈታኝ እንዳደረገበት ተገልጿል፡፡
ከ7-18 ዓመት ያሉ ጥቃት የደረሰባቸውን ህፃናትና ወጣቶች ብቻ እንደሚቀበል ቢያስታውቅም አንዳንዴ ከፖሊስና ከፍ/ቤት ትልልቅ ሴቶችን እንዲቀበል መገደዱ እንደ ችግር የተጠቀሰ ሲሆን የፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪገኝ በርካታ ምልልስ መደረጉና ጉዳያቸው መታየት ሳይጀምር አንድ አመት ድረስ  በማዕከሉ የሚቆዩ ህፃናት ጭንቀት፣ እንዲሁም “ጉዳዩ መቼ ነው የሚያልቀው” የሚል ጭቅጭቅ ለስራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡
ሙሉ አህመድና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቃት የደረሰባቸው 34 ታዳጊ ሴቶች በውበት ሙያ የተሰጠውን የአራት ወራት ስልጠና አጠናቀው ባለፈው ረቡዕ የተመረቁ ሲሆን ታዳጊዋ ሙሉ፤ ከማዕከሉ ወጥታ በፀጉር ስራ ራሷን ማስተዳደር እንደምትፈልግ ትናገራለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከሁሉም በላይ ግን ጥቂት የፈፀመባት ግለሰብ ተይዞ ተገቢውን ቅጣት ቢያገኝ እንደምትደሰት ገልፃለች።     

Read 3068 times