Saturday, 14 June 2014 11:42

ለመንገድ ጥገና በዓመት 2 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

በነዳጅ ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ ይችላል

    የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ አሁን ያሉት መንገዶች፣ ለረዥም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ፣ ለጥገና በዓመት 2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ገለጸ። ጽ/ቤቱ ያለፉትን 10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ራሽድ መሐመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አሁን እየታየ ያለውን ዕድገት ለማስቀጠል ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ መንገድ በመሆኑ፣ መንገዶችን ለመጠገን የተቋቋመው የመንገድ ፈንድ በጣም መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡ የመንገድ ፈንድ ከ16 ዓመት በፊት ሲቋቋም በአገሪቱ ከ50 እስከ 60ሺ የሚደርሱ መኪኖች እንደነበሩ የጠቀሱት አቶ ራሽድ፤ በአሁኑ ወቅት በብዙ እጅ ጨምረው 400ሺ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ መኪኖች የሚጠቀሙበትን መንገድ በየጊዜው ለመጠገን በጀት መጨመር ስላለበት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በቀጣይ 10 እና 15 ዓመታት የመንገድ ጥገና ፍላጎት ምን መምሰል አለበት? የገንዘብ ምንጩስ ከየት ነው?... በማለት ያደረጉትን ጥናት ለመንግሥት አቅርበው ውሳኔ እየጠበቁ ሲሆን ውሳኔው እንደተሰጠ እንደተፈቀደ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡

በጥናቱ መሰረት ለመንገድ ጥገና 2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ከተለያዩ ምንጮች እየሰበሰቡ ያሉት ገቢ 1.3 ቢሊዮን ብር ስለሆነ የ700 ሚሊዮን ብር ክፍተት እንዳለ አመልክተዋል። ክፍተቱንም ለመሙላት በዋነኛነት የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ በነዳጅ ላይ መጠነኛ የታሪፍ ጭማሪ ማድረግና የመንግሥት ድጎማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በነዳጅ ላይ ጭማሪ ሲደረግ የህብረተሰቡ ኑሮ አይናጋም ወይ? በማለት ተጠይቀው ሲመልሱ አሁን በነዳጅ ላይ የተጣለው ታሪፍ በጣም ትንሽ ነው፡፡ በናፍጣ ላይ ያለው ታሪፍ በአንድ ሊትር 0.9 ሳንቲም ነው፤ አንድ ሳንቲም እንኳ አይሞላም፡፡ አሁንም ህብረተሰቡን በማይጎዳ መልኩ መጠነኛ ጭማሪ ነው የሚደረገው፤ 0.5 ሳንቲም እንኳ አይሞላም ብለዋል።

የታሪፍ ማስተካከያው ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀር ምን እንደሚስል ሲገልጹ፣ በኬንያ ወይም በታንዛንያ ከአንድ ሊትር ነዳጅ የሚሰበሰበው የአንድ ዶላር ግማሽ ወይም 0.50 ዶላር ነው። በእኛ አገር ግን 0.5 ሳንቲም አይደርስም፡፡ እኛ በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ በዓመት የምንሰበስበው ከ60 እስከ 65 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ታንዛንያ ግን በዓመት 350 ሚሊዮን ዶላር ትሰበስባለች በማለት የሚደረገው የታሪፍ ማስተካከያ ጭማሪ ህብረተሰቡን እንደማይጎዳ አስረድተዋል፡፡ ለመንገድ ግንባታ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉና ጽ/ቤቱ ዳግም 16 ቢሊዮን ብር ያህል በመሰብሰብ ከዚህ ውስጥ 90 ከመቶ በላይ ወጪ አድርጎ 339ሺ ኪ.ሜ መንገድ አስጠግኗል፡፡ ለመንገድ ጥገና አንድ ዶላር ስታወጣ፣ የተሽከርካሪ ወጪ በ10 ዶላር እንደሚቀንስ ጥናቶች ያመለክታሉ ያሉት አቶ ራሽድ፤ ምክንያቱም መኪኖች በተበላሸ መንገድ ላይ ሲጓዙ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎች ሊሰበሩ ይችላሉ፡፡ መለዋወጫዎቹ የሚገዙት ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ነው።

ስለዚህ መንገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ በጣም ውድ (ፕሪሽዬስ) ነገር ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በጣም ጥሩ መንገዶች እየተሰሩ ስለሆነ፣ የጉዞ መጓተትና እንግልት ቀንሷል ያሉት አቶ ራሽድ፤ በፊት ከአዲስ አበባ አዳማ ሶስትና አራት ሰዓት ይወስድ የነበረው ጉዞ አሁን ከግማሽ በላይ ቀንሷል፡፡ መቀሌ ለመድረስ ሦስትና አራት ቀን ይፈጅ ነበር፡፡ ዛሬ በአንድ ቀን መግባት ተችሏል፡፡ ይህ የሆነው መንገዱ ምቹ ስለሆነ ነው፡፡ መንገድ ላይ ሲታደር የተለያዩ ወጪዎች (የመኝታ፣ የምግብ፣…) እንግልት አለ፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ወጪ የተሰሩት መንገዶች ካልተጠገኑ ወደ ቀድሞው ደረጃ መመለሳችን ነው፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ የሚደረገውን መጠነኛ ታሪፍ መቀበል ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ መንገድ ፈንድ ራሱ መንገድ የማይጠግን ሲሆን ከተለያዩ የገቢ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በመንገድ ጥገና ላይ ለተሰማሩ የተለያዩ ኤጀንሲዎች እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ ከሚሰበሰበው ከ1.3 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን የመንገዶች ባለስልጣን 65 በመቶ፣ ለዘጠኙ የክልል ገጠሮች 25 በመቶ፣ ለከተሞች ደግሞ 10 በመቶ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

Read 3213 times