Saturday, 14 June 2014 11:28

የሸራተን ሆቴል ሰራተኞችና የማኔጅመንቱ ፍጥጫ ተባብሷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(11 votes)

ኢሰማኮ ማኔጅመንቱ ለድርድር እንዲቀርብ አስጠነቀቀ

ማኔጅመንቱ ህግን በሚጥስ ተግባር ላይ አልደራደርም ብሏል

“የሥራ ማቆም አድማ የመጨረሻ አማራጭ ነው” የሰራተኛ ማህበሩ

     የሸራተን አዲስ ሆቴል ሰራተኞችና ማኔጅመንት ፍጥጫ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ ባለፈው ሀሙስ ከሰዓት በኋላ በፊንፊኔ የባህል ምግብ አዳራሽ በተጠራ አስቸኳይ ስብሰባ፤ ሰራተኞቹ ለቱሪዝም ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ሰራተኛና ማህበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎች በሸራተን ሆቴል ማኔጅመንት ደረሰብን ያሉትን በደል ያስረዱ ሲሆን “በገዛ አገራችን በ10 ፈረንጆች ቅኝ እየተገዛን ነው” ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በበኩሉ፤ የሸራተን ማኔጅመንት በአፋጣኝ ወደ ድርድር እንዲመጣ የአምስት ቀን ጊዜ በመስጠት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ፅፏል፡፡ ከተመሠረተ አራት አመቱን ያስቆጠረው የሸራተን አዲስ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበርና ሰራተኞቹ ለኢንዱስትሪ ፌደሬሽን በጋራ ባሰሙት አቤቱታ፤ ለበርካታ ጊዜያት በደላቸውን ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይና ለሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቁም በደሉ እንደቀጠለ መሆኑን ገልፀው፤ ከዚህ በኋላ ያለው ብቸኛ አማራጭ በደላችንን በሰላማዊ ሰልፍ በመግለፅ የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለም እንዲሰማው ማድረግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

“ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ እያስፈቀዱ በአደባባይ መንግስት ከስልጣን እንዲለቅ በሚጠይቁበት ወቅት እኛ በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንታይበትን አሰራር ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የምንከለከልበት ሁኔታ አይኖርም” ያሉት ሰራተኞቹ፤ እስከዛሬ የሞከሯቸው አማራጮች አለመሳካታቸውን ጠቁመዋል፡፡ “የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ በዘርና በቀለም ልዩነት በማድረግ፣ በጥቅማ ጥቅሞቻችን ላይ እያደረሱት ያለው በደል እስካሁን መፍትሄ አላገኘም” ያሉት የሸራተን መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሳሙኤል፤ “በምንም መልኩ የስራ ማቆም አድማ አናደርግም፤ ስራችንን እየሰራን ግን መብታችንን ለማስከበር ትግላችንን እንቀጥላለን፤ የስራ ማቆም አድማ የመጨረሻው አማራጭ ነው” ብለዋል፡፡ “ትልቋን ኢትዮጵያ በትንሹ ሸራተን ግፍ ውስጥ እንድናይ እየተገደድን ነው” ያሉት ሌላው የማህበሩ አባል፤ ፈረንጆቹ ቀስ በቀስ ቪዛ እየሰጡ ከአገራችን ሊያባርሩን ስለሆነ መፍትሄ እንሻለን ብለዋል፡፡

ማኔጅመንቱ ወደ ድርድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባለመሆኑና የህብረት ስምምነቱ ጊዜ አብቅቷል ብሎ የሆቴሉ ሰሌዳ ላይ በመለጠፉ፣ የኢንዱስትሪ ፌደሬሽን ለኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህራት ኮንፌደሬሽን በፃፈው ደብዳቤ፤ ኢሰማኮ ጣልቃ ገብቶ ማኔጅመንቱ እንዲደራደርና የህብረት ስምምነቱን እንዲፈርም ካልተደረገ ጉዳዩን ወደ ህግ እንደሚወስድ ያሳወቀ ሲሆን ኢሰማኮም የኢንዱስትሪ ፌደሬሽኑ ትብብር መፈለጉን ለማኔጅመንቱ ጠቅሶ በፃፈው ደብዳቤ፤ የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበሩን አቤቱታና የኢንዱስትሪ ፌደሬሽኑን የአግዙኝ ጥያቄ ተቀብሎ መመርመሩን ገልጿል፡፡ ድርድርን በተመለከተ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 130 ንዑስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት መሰረት “የህብረት ድርድር” ለማድረግ የፈለገው ወገን ሌላውን ወገን በጽሑፍ ሊጠይቅ እንደሚችል የጠቆመው ኢሰማኮ ለህብረት ድርድር የሚሆነውን ረቂቅ አዘጋጅቶ እንደሚሰጥና ተጠያቂውም ወገን ጥያቄው በደረሰው በ10 ቀናት ውስጥ ለህብረት ድርድር እንደሚቀርብ ኢሰማኮ በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ማኔጅመንቱ የማህበሩን ጥሪ ተቀብሎ በመደራደር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ የህብረት ስምምነቱ ጊዜውን ጨርሷል በሚል ሰሌዳ ላይ መለጠፉ አለመግባባቱን እያባባሰውና ሰራተኛው ወዳልተፈለገ እንቅስቃሴ እንዲገባ እያደረገው መሆኑን ኢሰማኮ በደብዳቤው ጠቁሞ ማኔጅመንቱን ተችቷል፡፡

ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶት እንኳን የማህበሩንና የፌደሬሽኑን የሰለጠነ የድርድር ጥያቄ ወደጐን የተወው ማኔጅመንቱ፤ ሰራተኛውን ወዳልተፈለገ ጫፍ እየገፋና የሰራተኛውን መብትና ጥቅሙን እየሸራረፈ መሆኑን የጠቆመው ኢሰማኮ፤ የተወሰደው ጊዜ ከበቂ በላይ በመሆኑ የሆቴሉ ማኔጅመንት ይህ ደብዳቤ በደረሰው በአምስት ቀናት ውስጥ ለድርድር እንዲቀርብ ያሳሰበ ሲሆን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ህግ በሚፈቅደው መሰረት ማኔጅመንቱን ለድርድር እንዲቀርብ እንደሚያስገድድ አስታውቋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፌደሬሽኑ የህግ ክፍል ኃላፊ አቶ ሰኢድ ይመር በበኩላቸው፤ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግና ለመሰል እንቅስቃሴዎች የሚቀሩ የህግ ጉዳዮች በመኖራቸው ትንሽ ጊዜ እንዲታገሱ ለሰራተኞቹ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ ኢሰማኮ ለማኔጅመንቱ በሰጠው የአምስት ቀን ጊዜ ውስጥ ለድርድር ካልቀረበ ግን ሁሉንም የማድረግ መብት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፌደሬሽኑ ሊቀመንበር አቶ ቶሌራ ደሬሳም፤ ሰራተኞቹ ያላቸውን ትብብርና አንድነት አድንቀው፤ ሰራተኛው ስራውን በአግባቡ እየሰራና ምርታማነቱን እያሳየ የመብት ጥያቄውን ማሰማት እንደሚችል መክረዋል፡፡

የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት በበኩላቸው፤ ሰራተኛው ለማህበሩ ሙሉ ስልጣን ከሰጠው፣ ከአሁን በኋላ ማኔጅመንቱ ለሚፈፅመው በደል ከመንግስት ፈቃድ ጠይቆ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚወጡ ቃል ገብቷል፡፡ ሰራተኛውም ሙሉ በሙሉ ለማህበሩ ስልጣን መስጠቱን በአንድ ድምጽ አጽድቆ ቃለ ጉባኤ ተፈርሟል፡፡

የሸራተን ማኔጅመንት በበኩሉ፤ ኢንዱስትሪ ፌደሬሽኑ ለኢሰማኮ የፃፈው ደብዳቤ ማኔጅመንቱን ሳይጠይቅ የአንድን ወገን አቤቱታ ብቻ ማስተናገዱን ገልፆ ፌዴሬሽኑን ወቅሷል፡፡ ማኔጅመንቱ ስራውን የሚያከናውነው ህግን መሰረት አድርጐ እንደሆነ ገለፆ፣ የህብረት ስምምነቱ ስራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ ከማርች 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመሆኑ የአገልግሎት ዘመኑ ማርች 1 ቀን 2014 ዓ.ም መጠናቀቁን እና የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 494/98 አንቀፅ 3 መሰረት ከጁን 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅምን በተመለከተ በህብረት ስምምነቱ የተሰጡ መብቶች እንዲቋረጡ ማድረጉን ለኢንዱስትሪ ፌደሬሽኑ በፃፈው ደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የሸራተን ማኔጅመንት አክሎም፤ ለሰራተኛ እቆረቆራለሁ የሚል ወገን መጀመሪያ ድርድሩ ለምን እንደተቋረጠ ካጣራ በኋላ ችግር ፈጣሪውን ወቅሶ ወደ ትክክለኛ መንገድ እንዲመጣ ማድረግና ድርድሩም በሰላም ተጠናቅቆ የኢንዱስትሪ ሰላም በድርጅቱ እንዲሰፍን መትጋት ይጠበቅበታል ብሏል፡፡ ድርጅቱ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ከህግ ውጭ እንደማይነፍግ ጠቁሞ ህግን በሚጥስ ተግባር ላይ ግን እንደማይደራደር አስታውቋል፡፡

Read 4917 times