Saturday, 14 June 2014 11:26

ኢትዮጵያ ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞች እያስተናገደች ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በየቀኑ 1 ሺ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ

አምና ለስደተኞች የምግብ እህል የተገዛው ከኢትዮጵያ ነው

        ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞች እያስተናገደች መሆኑን የገለፀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም አብዛኞቹ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ስደተኞች መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ያለፈውን ዓመት (2013) የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሰሞኑን ባቀረበበት ወቅት፤ በየቀኑ 1 ሺ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ጠቅሶ ካለፈው ዓመት መስከረም ወር አንስቶ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች 140ሺ እንደደረሱ የድርጅቱ ተጠሪና ዳሬክተር ሚ/ር አብዱ ዴንግ ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ሕፃናት፣ ሴቶችና የሚያጠቡ እናቶች መሆናቸውን ሚ/ር አብዱ ጠቅሰው፣ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተፈለገ በስተቀር አሁን ድርጅቱ የቀረው 70 ሚሊዮን ዶላር የሚያገለግለው እስከ መጪው ጥር ወር በመሆኑ፣ በሚቀጥለው ዓመት ለሚያስፈልጋቸው 120 ሚሊዮን ዶላር የዓለም ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ተማፅነዋል፡፡

ከቀያቸው የተፈናቀሉት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የተጠለሉት በቀላሉ በማይደረስበት የጫካ አካባቢ በመሆኑ፣ በየቀኑ ከጋምቤላ አሶሳ፣ ከአሶሳ ወደ ደቡብ ሱዳን ድንበር እየበረሩ በአውሮፕላንና በጀልባ እየተጠቀሙ 15,000 ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው 2013 ዓመት፣ ለስደተኞች 330ሺ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ከ15 አገሮች መግዛቱን ጠቅሶ፣ 46 ከመቶው ከኢትዮጵያ የተገዛ መሆኑን አመልክቷል፡፡ 120 ቶን እህል ከኢትዮጵያ ገበሬዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን በመግዛቱ፣ 67 ሚሊዮን ዶላር ገበሬዎቹ ኪስ መግባቱንና ኢትዮጵያ ብዛት ያለው የምግብ እህል ከተገዛባቸው አምስት አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቁሟል፡፡

Read 1847 times