Saturday, 07 June 2014 14:08

የፍቅር አቡጊዳ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አቶ መርሻ በኩራት ጨበጠው፡፡
ዕድላዊት ብሩህ ፈገግታዋን ፈነጠቀችለች፡፡
እሱም በቡናማ ዓይኖቹ አስተዋላት…
ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ልቧ ተሸበረ፡፡ ያኔ የአተነፋፈስ ስርዓቷ በጥቂቱ ተዛባ፡፡ ከያኔዋ ቅፅበት ጀምሮ ዕድላዊት መልስ ያላገኘችለት ጥያቄ በውስጧ ተጭሯል፡፡
የረሐብ የመሰለ፣ ያን ሰው የማግኘት፣ የራስ የማድረግ፣ በውል ይኼ ነው የማትለው፣ ነገር ግን ጠንካራ ስሜት!
ባለ ቡናማ ዓይኑ ወጣት የሸሚዙን እጅጌ እስከ ክንዱ ጠቅልሎ በውስጠኛው ዓይኗ ለውስጠቷ ይታያታል፡፡ የዳበረ ሰውነቱ፣ ወኔና ቆፍጣናነቱ፣ ማርኳታል፡፡
ሰርክ ቤታቸው እየተገኘ ከእርሷና ከመርሻ ጋር እየተጨዋወተ ያመሻል፡፡ ስለ ስራና ስለ ተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ይወያያል፡፡ በነዚህ ጊዜያት በደንብ አስተውላለች ወጣትነቱ፣ ብስለቱ በዚያ ላይ ደልዳላ ሰውነቱ አስጎምጅቷታል፡፡
እርግጥ ነው አቶ መርሻም ወዶታል፡፡ በስነምግባሩ፡፡ በተሰጠው ኃላፊነት ላይ ባለው ትጋትና ብቃት፣ ከሁሉም በላይ በመንፈሰ ጠንካራነቱ ሊያከብረው ተገዷል፡፡
ይሄይስ የዕድላዊት ሁኔታ አላማረውም፡፡ ድርጊቶቿ ሁሉ ሰላም አሳጥቶታል፡፡ አንጀት በሚበላ ሁኔታ እንባ ባቀረሩ አይኖቿ እየተመለከተችው፣ እየተንቆራጠጠችና ጣቶቿን እያፍተለተለች ትቀባጥራለች፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ወሬዋ ለመልስ የማይመቹ፣ እዚያው በዚያው የሚገጫጩ ፍሬ አልባ ቃላት ስለሚሆኑባት በዝምታ ሲያዳምጣት ይቆይና፡-
“በቃ ልሂድ አይደለም?” ይላታል፡፡
“እባክህ ይሄይስ ትንሽ ቆይ”
“ለምንድነው ዕድል እንዳልሰራ የምታደርጊኝ?”
“ምን አደረኩህ?”
“ይሄው ስንት ወር ሙሉ በተደጋጋሚ እያስጠራሽኝ የረባ ነገር እንኳ ሳትነግሪኝ በጊዜዬ ትጫወቻለሽ፡፡
ቀድሞውንም እኔን ብቻሽን በምትሆኚ ሰዓት መጥራትሽ አግባብነት የለውም! በጣም ነውርና ልፈቅደው የማላስበው ድርጊት ነው እያደረግሽ ያለሽው!”    ጮክ ብስጭት ብሎ፡፡
“የምታስቢው ሁሉ የማይሞከር ነው፡፡ ባለትዳር መሆንሽን፣ ባለቤትሽ ላንቺ ያለውን ፍቅር አስታውሺ እንጂ! እኔም ብሆን የዛን ጨዋ ሰው ጎጆ የማናጋ ከሐዲ አለመሆኔን ብታውቂ ደስ ይለኛል” ረጋ፣ አንገቱን ወደ ፊቷ ሰገግ እያደረገ፡፡
እሷ ፀጥ! አይኖቿን በእንባ ሞልታ ታቀረቅራለች።
የሳሎኑን በር ከፍቶ ሲወጣ ዓይኖቿ ያቆሩትን መራር ፈሳሽ፣ ከታመቀው የስሜት ትንፋሽዋ ጋር እኩል ትለቃቸዋለች…     
(“ፍቅርና ትግል” ከተሰኘው
  የደራሲ ልዑል ግርማ የአጭር ልብወለድ
  መድበል የተቀነጨበ)

Read 2483 times