Saturday, 07 June 2014 14:07

የዝነኛ ደራስያን አስገራሚ እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከአሸባሪዎች ጥቃት ጋር የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም የተወለደው ሴፕቴምበር 11 ቀን 1862 ዓ.ም ነው፡፡ ኒውዮርክን ሲወዳት ለጉድ ነው። ብዙዎቹ ታሪኮቹም ኒውዮርክ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ የጽሑፍ ሥራውን የጀመረው ወህኒ ቤት ታስሮ ሳለ ነው፡፡ ታሪኮችን እየፃፈ ኦ ሔነሪ በሚል የብዕር ስም ለጓደኞቹ ይልካል፤ ጓደኞቹ ደግሞ በኒውዮርክ በሚታተሙ መጽሔቶች ላይ ያወጡለት ነበር፡፡ እነዚያ ድንቅ ታሪኮች ከወህኒ ቤት እንደሚፃፉ ግን ማንም የሚያውቅ አልነበረም፡፡ ሚስቱን በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ባጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወህኒ ቢወረወርም የሚጽፋቸው ታሪኮች ግን የሚያሳዝኑና የሚጨፈግጉ አልነበሩም፡፡ የሚያዝናኑ፣ የሚያስቁና የሚያነቃቁ እንጂ፡፡
ወጣቱ ፖርተር ቱባውን (ያላጠረውን) መዝገበ ቃላት ተሸክሞ ነበር የሚዞረው፡፡ እንደመጽሐፍም ያነበውና በቃላት ይማረክም ነበር፡፡ የቃላት ክህሎቱን ከሼክስፒር ጋር የሚያወደድሩም አልጠፉም። እንዲያም ሆኖ ፖርተር ኮሌጅ የመግባት ዕድል አላገኘም፡፡ በ15 ዓመቱ ነው ትምህርቱን አቋርጦ በአጐቱ መድሃኒት ቤት ሥራ የጀመረው፡፡ በቴክሳስ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና ስፓኒሽ ቋንቋዎችን በቅጡ የተማረ ሲሆን አስፈላጊ ሲሆን የውጭ ቋንቋ ቃላትን በታሪኩ ውስጥ ይጠቀማል፡፡
ኦ ሄነሪ አንዳንዴ “የአሜሪካው ሞፓሳ” በሚል ይታወቃል፡፡ በአጫጭር ልብወለዶች ላይ ያልተጠበቀ አስገራሚ ወይም አሳዛኝ አሊያም አስቂኝ አጨራረስን እንዳስተዋወቀ ይነገርለታል፡፡ ታሪኮቹ ግን ስለተራ ተርታ ሰዎች ነው የሚተርኩት፡፡ እንዲያም ሆኖ  ዓለማቀፋዊ ጭብጦችን የሚያንፀባርቁ ናቸው - ፍቅርን፣ መስዋዕትነትን፣ ክብርንና ርህሩህነትን፡፡
ኦ ሄነሪ ዝናን የተቀዳጀው በአንድ ጊዜ አይደለም። የሚጽፋቸውን ታሪኮች በመላ አገሪቱ ለሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ቢልክም፤ በተደጋጋሚ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ “ነገር ግን ይሄ ጉዳይ አሳስቦኝ አያውቅም፤ አዲስ ቴምብር ለጥፌባቸው ወደ ሌላ ቢሮ እልካቸዋለሁ፡፡ እንዲህ ሲመላለሱ ይቆዩና በአንዱ የህትመት ቢሮ ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ተቀባይነት ያላገኘ ታሪክ ግን ጽፌ አላውቅም” ብሏል፤ አፕሪል 4 ቀን 1909 ዓ.ም ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጠው ብቸኛ ቃለምልልስ፡፡ ለምሳሌ The Emanicipation of Billy የተሰኘው ምርጥ ሥራው ከ10 ጊዜ በላይ ውድቅ እንደተደረገበት ጠቅሶ የማታ ማታ ግን እንደሌሎቹ ሥራዎቹ ሁሉ በአንዱ የህትመት ውጤት ላይ እንደታተመለት ተናግሯል፡፡
የኦ‘ሄነሪ በርካታ አጭር ልብ-ወለዶች ወደ አማርኛ የተተረጐሙ ሲሆን ከእነሱም መካከል The Last Leaf (የመጨረሻዋ ቅጠል) እና The Gift of the magi ይገኙበታል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የደራሲው ሥራዎች ተተርጉመው በዚሁ ጋዜጣ ላይም ለንባብ በቅተዋል፡፡  
የኦኼነሪ ዝነኛ ሥራዎች
Witches Loaves
A Retrieved Reformation
The pimienta Panckes
The Green Door
Let me Feel your pulse (የመጨረሻ ሥራው)
The Ransom of Red chief
Shoes
Ships (የshoes ቀጣይ ሥራው ነው)

Read 5393 times