Saturday, 07 June 2014 13:22

“ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
ዘንድሮስ ለጉዴ ቁመቴ ረዘመ
ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ፣
ይሉ ነበሩ አያቶቻችን፡፡ እንዴት አሪፍ አባባል ነች!! ልክ አሁን ላለንበት ጊዜ ‘በልክ የተሠራች’ አትመስልም! እንዲሁ ነው የዘንድሮ ነገራችን… አለ አይደል… ‘ከመሬት ተነስቶ’ “ያም አገር፣ ያም አገር ይታየኝ ጀመረ…” የሚለው ቁጥር እየበዛ ነው። እናማ…ለዚህኛው ጀርባን ሰጥቶ ወደ እዛኛው የሚንጠራራ ቁጥሩ ሲጨምር ጎበዝ ይሄ ነገር እንዴት ነው ማለት ደግ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እንደ ዘንድሮ ‘አማርኛችን’ ሁሉ…  “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…” “...ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል…” “…ያለምንም ግብ ባዶ ለባዶ አቻ ተለያይተዋል…” “…መርሀ ግብሩን ነድፎ፣ ራዕዩን ሰንቆ በዓላማ ጽናትና በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀስንበት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…” ሳይሆን በፊት አባት አያቶቻችን አሪፍ ነገሮች ትተውልን ነበር፣ ‘አደራ በላ’ እስኪያስመስለን ድረስ ችላ አልነው እንጂ፡፡
እናማ…በአንድ መስመር ተረትና ምሳሌ የሚነሳውን የሀሳብ ጥልቀት ስታዩ ምነዋ እኛ ዘንድ ሲደርስ ‘ባቡሩ’ ተሰናከለሳ! እናማ ከስንት አሥርት ዓመታት በፊት የተነገሩ አባባሎችና ምሳሌዎች ሆድ ባሰንና
ዘንድሮስ ለጉዴ ቁመቴ ረዘመ
ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ፣
የምንል ለበዛንበት ዘመን ‘በእውቅ የተነገሩ’ ይመስላሉ፡፡
“አህያ አታማኻኝብኝ ትበላኝ እንደሆነ እንዲያው ብላኝ አለች፣” የምትል አባባል አለች። ዘንድሮ በየሄዳችሁበት ባልዋላችሁበት ሊያመካኙባችሁ የሚሮጡ መአት ናቸው፡፡ የምር ግን…ከጣቶቻችን ሁሉ ‘አመልካች ጣት’ ሥራ የበዛባት  (‘ጠቋሚ ጣት’ የሚል አማራጭ መለያ ይሰጥልንማ!) “ትበላኝ እንደሁ እንዲያው ብላኝ…”  የሚባልብን ሰዎች ስለበዛን ነው፡፡
እናማ…በ‘ቦተሊካውም’ በሉት፣ በስነ ጥበቡም በሉት፣ በየቢሮውም በሉት፣ በየመንደሩም በሉት በሌላው የምናመኻኝ መአት ነን፡፡ እናማ ይሄኔ ነው  “…ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ፣” የሚያስብለው። ከ‘ሌላ አካባቢ’ ስለተገኙ፣ ‘ሌላ ቋንቋ’ ስለሚናገሩ፣ ከሌላው የተለየ አስተሳሰብ ስላላቸው፣ “ቅልቅል ለሰርግ ብቻ ነው…” ብለው ራሳቸውን ለመሆን የሚሞክሩ ሰዎች… የሚመኸኝባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
“የዚህ ዓለም ፍቅር ሰኞ አዲስ፣ ማክሰኞ ልብስ፣ ረቡዕ ብጥስጥስ…” የሚሏት አባባል ነበረች። ደግሞላችሁ…ዘንድሮ ራሱ ‘ፍቅር’ የሚለው ቃል አገር በቀል የተሻሻለ ትርጉም ካልተበጀለት… ዓለም አቀፉ ትርጉምማ እኛ ዘንድ መሥራት ካቆመ ከራረመ፡፡ እንደውም… አለ አይደል… የዘንድሮ የጦቢያችን ፍቅር “ጧት አዲስ፣ ቀትር ልብስ፡ ማታ ብጥስጥስ…” ይባልልን፡፡
እናላችሁ…ፍቅር ሲዳከም፣ የመተጋገዝና “ሆዴ የአገሬ ልጅ…” መባባል ወደ ‘አፈ ታሪክነት’ ሲለወጥ፣ አስተዳዳሪው “ረግጬ ካልገዛሁ” ሲል፣ የተስተዳዳሪው ትከሻ ሸክም ሲያቅተው… “ያም አገር፣ ያም አገር ይታየኝ ጀመረ…” ማለት ይበዛል፡፡
“ባለቤቱን በፊቱ ማመስገን ከማማት እኩል ነው፣” የሚሏት አሪፍ አባባል አለች፡፡ ዘንድሮ ‘ባለቤቶችን’ ገጽ ለገጽም፣ በጽሁፍም፣ በምስልም፣ በንግግርም ወዘተ. ለማመስገን የምንሯሯጥ መአት ነን፡፡
እንዳለመታደል ሆነና ብዙ ‘ባለቤቶች’ ሳያስነጥሳቸው መሀረብ ሲቀርብላቸው ደስ ስለሚላቸው…ታማኝነቱን ፊት ለፊት እየገለጸ ‘የሚሳካለት’ ሞልቷል፡፡
ይሄኔ አቀርቅሮ የሚለፋው፣ አጎንብሰሶ ላቡን ጠብ የሚያደርገው…የበይ ተመልካች ሆኖ ሲቀር…አለ አይደል… “ያም አገር፣ ያም አገር ይታየኝ ጀመረ…” ማለት ይመጣል፡፡ (በነገራችን ላይ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ከዘጠና ሚሊዮናችን ግማሻችን “በቃ ሂድ፣ ሂድ አለኝ…” ብንል… “ምን ሆናችሁብን!”  “ወገኖቻችንን እንዲህ ሆድ ያስባሳቸው ምን ቢደርስባቸው ነው!” ከመባል ይልቅ… “አንካሳ ዶሮ እንዳይቀድማችሁ…” የምንባል ይመስለኛል፡፡)
ታዲያማ…‘ባለቤቱን’ ፊት ለፊት እያሞገሰ ሽቅብ የሚወጣው በበዛ ቁጥር ሌላው የበይ ተመልካች ሲሆን፣ ቁራሽ እንጀራ ሳያዋጣ እሱ መሶብ ውስጥ እጁን የሚሰድ ሲበዛ፣ ሊጎርስ ያለው ከአፉ ላይ ሲመነተፍ…ይሄኔ “ያም አገር፣ ያም አገር ይታየኝ ጀመረ…” ማለት ይመጣል፡፡
ደግሞላችሁ…መልካም መካሪ እያነሰ የመጣበት ዘመን ነው፡፡ ታዲያማ… “ረጋ ብለህ ከራስህ ጋር ተመካከር…” ከሚለው ይልቅ “አደባልቀውና እርጥቡን ከደረቅ…” የሚለው እየበዛ ሁሉንም ነገር በጨሰ፣ አቧረው ጨሰ መፍታት እንፈልጋለን። “ሚስትህን ስደድ በሬህን እረድ ይላል የባለጌ ዘመድ፣” የምትል ምርጥ አባባል አለች፡፡ ምንም እንኳን ጥናት ምናምን ነገር እኛ አገር ባይለመድም ከብዙ ትዳሮች መፍረስ ጀርባ “ሚስትህን ስደድ በሬህን እረድ…” የሚል መካሪ መኖሩ ነው ይባላል። አንዱ ከአንዱ ጋር እንዴት እርቅ እንደሚያወርድ ሳይሆን አንደኛው ሌላኛውን እንዴት ‘ልክ እንደሚያስገባው’ የሚመክር እየበዛ ‘ሚስት መስደድና በሬ ማረድ’ በየዕለቱ የምንሰማቸው ነገሮች ሆነዋል፡፡
እናማ… እንዲህ አይነት ነገሮች ሲበዙና በሰላምና በእርጋታ የመኖር ተስፋ ሲሟጠጥ፣ “የእኛ…” ከማለት ይልቅ “የእኔ…” ባይ ሲበዛ፣ ‘ባለ አገሩ’ እንደ አገር የለሽ ሲቆጠር…
ዘንድሮስ ለጉዴ ቁመቴ ረዘመ
ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ፣
ማለት ይበዛል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “የወንድምህ ጢም ሲላጭ፣ ጢምህን ውሀ አርስ፣” የሚሏት ምርጥ አባባል አለች፡፡ ነገርዬዋ…አለ አይደል…“ነግ በእኔ…” አይነት ነገር መሆኗ ነው፡፡ እናላችሁ…ዘንድሮ ሁላችንም ምንም ነገር እኛ ዘንድ ሲደርስ ነው የምንነቃው፡፡ እናማ…የወንድሙ ጢም ሲላጭ የእሱ እንደ ሪፕ ቫን ዊንክል የሚንዠረገግለት እየመሰለው ‘እግሩን ሰቅሎ’ ለጥ የሚል መአት ነው፡፡
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ‘ቦተሊካ’ ውስጥ አይታችሁልኝ እንደሆነ፣ የሆነ ቡድን አባል የሆነ ሰው ስለ እሱ ቡድን እውነተኛነት፣ ስለ እሱ አገር ወዳድነት ምናምን ሲሰብካችሁ … ሲጨቀጭቃችሁ… ይከርማል፡፡
ጓደኞቹ በሆነ ባልሆነው እየተንገዋለሉ ፌርማታ እንኳን ሳይደርሱ ‘ሲራገፉ’ ጀርባን አዙሮ “በቡድኔና በዓይኔማ ቀልድ የለም…” አይነት ነገር ሲል ይከርማል፡፡
ታዲያላችሁ… የፈለገ ‘ሰማይ ጫፍ’ ቢወጣ… አለ አይደል… “እንደ ሙቀጫ…” መንከባለል የጦቢያችን ቦተሊካ ‘ታሪካዊ ሀቅ’ ነውና (ቂ…ቂ…ቂ…) ዘጭ ይላል፡፡ ይሄኔ ያመጣዋላ! እንደዛ ምድር ላይ እንዳለ መንግሥተ ሰማያት ሲያንቆለዻዽሰው የከረመውን ቡድን፣ የምድር ሲኦል አድርጎት ቁጭ! ማማት ብቻ ሳይሆን ‘ኤኒሚ ኦፍ ዘ ስቴት’ እንደሚሉት ቁጥር አንድ ጠላት ሆኖ ያርፍላችኋል! የወንድሙ ጢም ሲላጭ፣ ‘ጢሙን ውሀ ሳያርስ’ ይቆይና አንደኛውን ተሸልቶት ያርፈዋል፡፡
የምር ግን…ብዙ ቦታ ነገሬ ካላችሁልኝ “ይሄ ነገር ትክክል አይደለም…”  “እንዲህ አይነት ነገር ሲደረግ እንዴት ዝም ይባላል…” ምናምን የምንለው ሌላው ላይ ሲደርስ ሳይሆን እኛ ዘንድ ሲመጣ ነው፡፡
በእንጭጩ ሲጀመር “ኸረ እባካችሁ…” ሳይባል ይከርምና እኛ ዘንድ ሲደርስ ግን የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራበት የሚገባ ወንጀል የተፈጸመ እናስመስለዋለን፡፡ እናማ “የወንድምህ ጢም ሲላጭ፣ ጢምህን ውሀ አርስ፣” አሪፍ አባባል ነች፡፡
ደግሞላችሁ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል……“ምንጃር ጤፍ ተወቃ ቢሉት ሸንኮራ ሆኖ እብቅ ዓይኔ ገባ አለ፣” የሚሏት አባባል አለች፡፡ ቅጥፈት በዝቷል! ከላይ እስከታች ቅጥፈት በዝቷል! ደረጃው ይለያይ እንጂ ውሸት፣ ማምታታት…የሌለበት ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ “በሬ ወለደ…” ማለት የሚያሳፍር የሚያሸማቅቅ ሳይሆን በብልጥነትና በብልህነት የሚያስፎክርበት ዘመን እየሆነ ነው፡፡
እናማ…ነገሮች የሚሠሩት በእውነትና ሀቅ ላይ ሳይሆን በቅጥፈትና በማምታታት እየሆነ በዛው ልክ ተስፋ እየቆረጠ
ዘንድሮስ ለጉዴ ቁመቴ ረዘመ
ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ፣
ባይ ይበራከታል፡፡
“ያም አገር ያም አገር ይታየኝ ጀመረ…” የምንልበትን ዘመን ያሳጥርልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3528 times