Print this page
Saturday, 07 June 2014 13:20

በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ የህዝብ ስልኮች በሙሉ ተበላሽተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

“ችግሩ እንዳለ እናውቃለን፤ የማፅዳትና የመጠገን ስራ እየተከናወነ ነው” - ኢትዮ-ቴሌኮም

         በመርካቶ ምን አለሽ ተራ አነስተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ኪዮስክ ባለቤት የሆነው ሙዘይን ከድር፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ ስልክ  የማስደወል ስራ ትርፋማ  እየሆነ መምጣቱን ይናገራል፡፡ ከሱቅ  እቃ ከሚገዙት  ደንበኞች ይልቅ ስልክ የሚደውሉት እንደሚበዙ የገለፀው ወጣቱ ነጋዴ፤ በሶስት የመስመር ስልኮችና በአንድ ሞባይል የማስደወል አገልግሎት እየሰጠ በየቀኑ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኝ ይገልፃል፡፡ የገበያ ቀን ሲሆን ከስልክ በቀን እስከ 250 ብር እንደሚያገኝ ጠቁሞ በአካባቢው የተተከሉት የህዝብ ስልኮች አገልግሎት መስጠት ካቆሙ ወዲህ ይበልጥ ገቢው እየጨመረ መምጣቱን ተናግሯል፡፡
የስልክ አገልግሎት ከፍተኛ ተጠቃሚ አለው ይላል - ሙዘይን፡፡ ከመስመር ስልክ ወደ መስመር ስልክ  እንደየቦታው ርቀት በደቂቃ  50 ሣንቲም ያስከፍላል፡፡ ወደ ሞባይል ምልክት ለማድረግ 50 ሣንቲም፣ ለመደወል ደግሞ በደቂቃ 1 ብር ከ50 እንደሚያስከፍል ገልጿል፡፡
ለገሃር አካባቢ አነስተኛ ኪዮስክ ያላት ብዙነሽም፣ ስልክ ማስደወል ትርፋማ ያደርጋል ትላለች፡፡ አንዳንዴ ከሸቀጦች ከምታገኘው ትርፍ ይልቅ ስልክ በማስደወል የምታገኘው እንደሚበልጥ በመጠቆም፡፡ በአካባቢው የመስመር ስልክ በአግባቡ እንደማይሠራ የገለፀችው ነጋዴዋ፣ በሁለት ሞባይሎች አገልግሎቱን እንደምትሠጥ ጠቅሳ፣ በአንደኛው ሞባይል ብቻ በቀን የ100 ብር ካርድ እንደምትሞላና እስከ 150 ብር ድረስ ትርፍ እንደምታገኝበት ተናግራለች፡፡ በአካባቢው በርካታ የህዝብ ስልኮች ቢኖሩም አንዱም አገልግሎት እንደማይሰጥና የስልኮቹ አገልግሎት ከቆመ በኋላ የደንበኞቿ ቁጥር መጨመሩን ገልፃለች፡፡
ከሁለት አመታት በፊት እዚያው ለገሃር አካባቢ ለህዝብ ስልክ ተጠቃሚዎች  ሣንቲም በመዘርዘር የእለት ጉርሱን ያገኝ እንደነበር የነገረን ወጣት እንደሚለው፣ ስልኮቹ ሲበላሹ ጥገና ስለማይደረግላቸውና ንፅህናቸው ስለማይጠበቅ ያለአገልግሎት ቆመዋል፡፡ ከሁለት አመት በፊት 1 ብር በ85 ሣንቲም እየዘረዘረ ለደዋዮች በሚሰጠው አገልግሎት በቀን  እስከ 50 እና 60 ብር ድረስ ትርፍ ያገኝ እንደነበር አስታውሶ፣ ገቢው ከእለት ጉርሱም  አልፎ መቆጠብ ጀምሮ ነበር፡፡ ሥራው ሲቀዛቀዝ  ፊቱን ወደሌላ  የስራ መስክ እንዳዞረ የገለፀው ወጣቱ፤ ሳንቲም በመዘርዘር የሚያውቃቸው ልጆችም  ወደ ታክሲ ተራ እንዳመሩ ይናገራል፡፡
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያየናቸው ለህዝብ ስልክ ማስደወያ የተዘጋጁ ሼዶች በአብዛኛው  የማስታወቂያ መለጠፊያ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ማደሪያ እና መፀዳጃ እንደሆኑ ታዝበናል፡፡ ብዙዎቹ የህዝብ  ስልኮች ከአገልግሎት ውጭ ሲሆኑ ከእነአካቴው በቦታቸው የሌሉም አጋጥመውናል፡፡
ከህዝብ ስልክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በርካታ ችግሮች እንደነበሩ የጠቆሙት የኢትዮ-ቴሌኮም የህዝብና የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አብዱራህማን መሃመድ፤ ሼዶቹ የፅዳት ችግር እንደነበረባቸው አስታውሰው፤ ከፍተኛ ችግር ያለባቸው ሼዶች ተለይተው ሙሉ ለሙሉ እንዲነሱ ተደርገዋል ይላሉ፡፡ መጠገን የሚችሉትም እንዲጠገኑ “ህዳሴ” ለሚባል  የቴሌኮም ኩባንያ ሥራው ተሰጥቶታል ያሉት ኃላፊው፤ በስልኮቹ ላይ የሚታየው ዋና  ችግር “የአጠቃቀም ” መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በኩባንያው በኩል ያለመታከት በየቀኑ ክትትል ይደረጋል፤ ሆኖም ቴክኒሻኖች ያስተካካሉትና የጠገኑት ስልክ ብዙም አገልግሎት ሳይሰጥ ወዲያው ብልሽት ያጋጥመዋል ብለዋል - አቶ አብዱራህማን፡፡
በአጠቃቀም ረገድ ያለውን ችግር ሃላፊው በሁለት ይከፍሉታል፤ አንደኛው ከ3 ዓመት በፊት በተተከሉ አዳዲስ ስልኮች የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ላይ የተፈፀመ  ስርቆት ሲሆን በዚህም የ120 የህዝብ ስልኮች ሃይል ማመንጫ መሰረቁን ተናግረዋል፡፡ ሁለተኛው የመለዋወጫ ችግር መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ መለዋወጫዎች ከውጭ ተገዝተው ስልኮቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት  እየተደረገ ነው ብለዋል። ትልቁ ችግር የአጠቃቀም መሆኑን ያሰመሩበት ኃላፊው፤ ባለሙያዎች በቀን ሁለት ጊዜ ክትትል ቢያደርጉም ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡
በመላ አገሪቱ  9ሺህ የሚሆኑ የህዝብ ስልኮች ሲኖሩ አራት ሺህ ያህሉ በአዲስ አበባ እንዳሉ የጠቀሱት ኃላፊው፤ አብዛኞቹ ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ሳቢያ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ብለዋል፡፡
የህዝብ ስልክ አገልግሎት የተቋረጠው ለመንግስት የስለላና የደህንነት ስራ ስለማይመች ነው የሚሉ አስተያየቶች እንደሚሰነዘሩ የጠቆምናቸው አቶ አብዱራሂም፤ አስተያየቱ ትክክለኛ አይደለም ብለዋል፡፡  “የህዝብ ስልክም ቁጥር ስላለው ከየት ወዴት እንደተደወለ ይታወቃል፣ ተቋሙ የአገልግሎት አቅራቢነት እንጂ ሌላ ተልዕኮ አልተሰጠውም” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የህዝብ ስልኮችን የወደፊት እጣ ፈንታ በተመለከተም  ሲናገሩ፤ አገልግሎቱ በርካታ ተጠቃሚ እንዳለው ጠቁመው፤ስልኮቹ በዋነኝነት የታለሙት  የሞባይል ስልክ ለማይጠቀሙና የቤት ስልክ ለማስገባት  አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሆነ የገለፁት  አቶ አብዱራሂም፤ በርካታ ህብረተሰብ የሚጠቀምበት አገልግሎት በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

Read 4691 times