Saturday, 07 June 2014 13:18

የቴዲ አፍሮ እና የኮካኮላ ውዝግብ በፌስቡክ ዘመቻ ተራገበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

የቴዲ ሙዚቃ ከሻኪራ እና ከሎፔዝ ጋር በዓለም ዋንጫ አልበም አልተካተተም
የቴዲ ሙዚቃ “ጥራት ይጐድለዋል አይጐድለውም” “ለህዝብ ይለቀቅ - አይለቀቅ” በሚል ውዝግብ አስነስቷል
በፌስቡክ ኮካ ኮላ ላይ ስለተጀመረው ዘመቻ ታዋቂ የፌስ ቡክ ፀሐፊዎች ምን ይላሉ?

      በብራዚል ለሚካሄደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የኮካ ኮላን መሪ ዘፈን እንዲዘፍን ተጋብዞ ዘፈኑ ከተዘጋጀ በኋላ ከደረጃ በታች ነው በሚል ኮካ ኮላ ከአርቲስቱ ጋር ውሉን በማቋረጡ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አድናቂዎች “የኮካ ኮላን ምርት አትጠጡ” የሚል ዘመቻ ጀመሩ፡፡ እንደሚጠቁመው፤ ቴዲ ዘፈኑን እንዲሰራ ከኮካ ኮላ ኩባንያ በቀረበለት ግብዣ፣ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያንና ቴዲን በዓለም ዋንጫ ተመልካቾችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በበጐ ለማስተዋወቅ ይጠቅማል በሚል ግብዣውን በደስታ እንደተቀበለው በአርቲስቱ ድረገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕ “ማንዳላ ቲቪ” በተባለውና የኮካ ኮላ የመካከለኛ፣ የምስራቅና የምዕራብ አፍሪካ ወኪል በኩል ተሰርቶ መጠናቀቁንና ለስርጭት ወደ ኮካ ኮላ መላኩን የቴዲ አፍሮ ድረገፅ ይገልፃል፡፡
የኮካ ኮላ የኢትዮጵያና የኤርትራ ብራንድ ማናጀር የሆኑት አቶ ምስክር ቪዲዮውን አምጠውት ካሳዩዋቸው በኋላ፣ በጣም ደስታ እንደፈጠረባቸው የገለጸው ድረ-ገፁ፤  ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ብራንድ ማናጀሩ መጥተው “ቴዲ በቪዲዮው ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከደረጃ በታች በመሆኑና ለክብሩ ስለማይመጥን ለህዝብ አይለቀቅ” ማለታቸውን ድረ- ገፁ አመልክቷል፡፡ ቪዲዮው የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ ለማሳመን ብንጥርም በቂ ምላሽ አልተገኘም ያለው የድረ-ገፁ መረጃ፤ የማሳመን ጥረቱ እንዲቀጥል መወሰኑን ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች በፌስቡክ ኮካ ኮላ እንዳይጠጣ የሚል ዘመቻ የጀመሩ ሲሆን በዘመቻው ዙሪያ ታዋቂ የፌስ ቡክ ፀሐፍት ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  
ኮካ ኮላ ለምን ሙዚቃው እንዳይለቀቅ እንደወሰነ ለማጣራት የኮካ ኮላ የኢትዮጵያና የኤርትራ ብራንድ ማናጀር ለሆኑት አቶ ምስክር ሙሉጌታ በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ ባለማግኘታችን ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡   
“በደፈናው ቦይኮትን ጥሩ ነው መጥፎ ነው ለማለት እቸገራለሁ”
በፌስቡክ ገፁ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመፃፍ ብዙ ተከታዮችን ያፈራውኢዮብ ምህረት አብ፤ አንድን ድርጅት ቦይኮት ማደረግ አስፈላጊ ነው አስፈላጊ አይደለም የሚለውን ጉዳይ በደፈናው ለመደምደም እንደሚቸገር ገልፆ፤ ዋና ትኩረት መደረግ ያለበት ቦይኮት እናድርግ ብለን የተነሳንበት አላማና ግብ ላይ መሆን አለበት ይላል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት ፌስ ቡክ ላይ በዛ ያሉ ሰዎች ተፅዕኖ ማምጣት ጀምረዋል” የሚለው ኢዮብ፤ እነዚህ  ሰዎች ቦይኮት እናድርግ (የአንድን ኩባንያ ምርት አንጠቀም) ብለው የሚነሱበት ሃሳብ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል ብሏል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ሴራን ለመጠንሰስና ሆን ብለው ግለሰብን ወይም ድርጅትን ለመጉዳት የሚያደርጉት ሲሆን ሌሎች ደግሞ በምክንያትና አዎንታዊ ጐኑን በማሰብ ቦይኮትን ይጠቀሙበታል ያለው አስተያየት ሰጪው፤ ቦይኮት ማድረግ ለጥሩም ለመጥፎም ጉዳይ ስለሚውል አስፈላጊ ነው አስፈላጊ አይደለም የሚል ቁርጥ ያለ መደምደምያ ላይ ለመድረስ  ያስቸግራል ብሏል፡፡
“ቦይኮትን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ስስ የሆነ ስሜት ያላቸው ግለሰቦች (ድርጅቶች) እንደሚፈሩት የተረዱ ሰዎች የሚጠቀሙበት ነው” ያለው  የፌስቡክ ፀሐፊው፤ እነዚህ ነገሮች ባሉበት ሁኔታም ቢሆን መጥፎም ጥሩም ለማለት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሞ፤ ነገር ግን ቦይኮት የሚባለው ነገር ተፅዕኖ እንዳለው እንደሆነ እያየን ነው ይላል - በቅርቡ በበደሌ ቢራ ላይ የደረሰውን በመጥቀስ፡፡
“አስደንጋጩ ነገር ሰዎች  ቦይኮትን እንደሥራ ይዘው መንቀሳቀስ መጀመራቸውና ተፅዕኖ መፍጠር መቻላቸው ነው” ይላል - ኢዮብ፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁ (ቴዲ አፍሮ) ስለ ምኒልክ የተናገረውን ጉዳይ ተከትሎ ከበደሌ ቢራ ጋር በነበረው የሙዚቃ ድግስ ስምምነት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታውሶ፤ በደሌን ቦይኮት እናድርግ በመባሉ ኩባንያው ከአርቲስቱ ጋር የገባውን ውል እንዲሰርዝ አስገድዶታል ብሏል፡፡
“ቴዲ አፍሮ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ በኦሮምኛ ተናጋሪዎችና በኦሮሚያም ክልሎች ተቀባይነት ነበረው” ያለው አስተያየት ሰጪው፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ለቴዲ ያላቸው ግምት ጥሩ እንዳልሆነ እየሰማሁ ነው፤” ሲል ቦይኮት የግለሰብ ስምና ዝና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ገልጿል፡፡ ያም ሆኖ ቦይኮት መቶ በመቶ መጥፎ ነው ለማለት እቸገራለሁ፤ አንዳንድ ጊዜ አዎንታዊ ጐንም አለው ይላል፡፡ “ላሰምርበት የምፈልገው ቦይኮት ለማድረግ የምንነሳበት ሃሳብ ነው፤ የግል ስሜታችንን ለማንፀባረቅ ነው፣ ሆን ብለን አንድን ግለሰብ (ድርጅት) ለማጥቃት ነው ወይስ ምክንያታዊ ሆነን የአገራችን ጉዳይ አንገብግብቦን? የሚለው መነሻ ሃሳባችን ቦይኮቱን በመጥፎነት ወይም በጥሩነት ለመመደብ ያስችላል - ብሏል፡፡
ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ አለ የተባለው ነገር እውነት ከሆነ፣ ያንን መናገሩ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ በደሌን ቦይኮት አድርጐ ኮንሰርቱን መሰረዝ፣ ቴዲ ስህተቱ እንዲገባውና ለወደፊቱም ጥንቃቄ እንዲያደርግ  ከስህተቱም እንዲማር ይረዳዋል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኮካ ኮላን እና የቴዲ አፍሮን ጉዳይ በተመለከተ አስተያየት ሰጪው ሲናገር፤ ኮካ ኮላ እንዲህ አይነት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ አይደለም፤  ቴዲ አፍሮ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው፤ ሆኖም ኮካ ጉዳዩን አስቦበት እና ሁሉን ነገር መርምሮ  እንደሚያደርገው ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ኮካ ኮላ ቦይኮት ቢደረግ ይሄ ነው የሚባል ተፅዕኖ ይፈጠርበታል ብዬ አላምንም፤  ለዚህም ምክንያቱ በመላው አለም ያለ ትልቅ ኩባንያ በመሆኑ ተወዳጅነቱን ጠብቆ የዘለቀ ነው ብሏል፡፡
“ህዝቡም ኮካ ኮላን ቦይኮት አድርጐ እስከመጨረሻው መዝለቅ አይችልም፤ በወረት ሆይ ሆይ ብሎ ይተወዋል እንጂ” ሲል ሃሳቡን ገልጿል፡፡ “ቦይኮት” መጥፎ ድርጊቶችን ለመቃወም ይረዳል  ለምሳሌ የህፃናት ጉልበት የሚበዘብዝ አንድ ኩባንያ ቦይኮት መደረግ አለበት” ያለው ኢዮብ፤ “አንድ ታዋቂ አርቲስት ስራህ ከደረጃ በታች ነው ስለተባለ ኮካን ቦይኮት ማድረግ ነውር ነው ወይም ፅድቅ ነው ማለት አግባብ አይደለም” ሲልም አስተያየቱን ቋጭቷል፡፡
“አንድን ድርጅት ቦይኮት ማድረግ በራሱ አፈና መፀፈም ነው”
(ደመቀ ከበደ) የሚዲያ ባለሙያ
በፌስ ቡክ ገፁ የተለያዩ ግጥሞችንና ትችቶችን እንዲሁም ሃሳቦችን በማቅረብ የሚታወቀው የሚዲያ ባለሙያው ደመቀ ከበደ በበኩሉ፤ ቦይኮት በሚለው ሃሳብ እንደማያምን ገልፆ  የአንድ ኩባንያን ምርት ከመጠቀም እንታቀብ ማለት በራሱ አፈና መፈፀም ነው ይላል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ምክንያታዊ የሆኑ ፀሐፍት የሚሰባሰቡበት መሆን አለበት የሚል ጠንካራ እምነት እንዳለው የገለፀው ደመቀ፤ የቦይኮት ምንጩ ጽንፈኝነት ነው ባይ ነው፡፡ “ለእኔ በሁለት ፅንፍ መሃል መሄድ አይመቸኝም” የሚለው ፀሐፊው፤ በሁለት ጽንፎች መሃል ተጐጂው ማህበረሰቡ ነው ይላል፡፡ በምሣሌ ሲያስረዳም ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች “ኮኮ ኮላን አትጠጡ” የሚል ቅስቀሳ መጀመሩን ይጠቅሳል፡፡
አስተያየት ሰጪው እንደሚለው፤ ኮካኮላ አለማቀፍ መጠጥ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠጣ አልተጠጣ ኩባንያውን ብዙም አይጐዳውም፤ አብዛኛው ማህበረሰብ ኮካን የሚጠጣውም የሚሰጠውን ጥቅም አስቦ እንጂ ግለሰቦች ጠጣ አትጠጣ ስላሉ አይደለም ብሏል፡፡
“ዛሬ ኮካ በቅስቀሳው መሠረት ኮካ ባይጠጣ ከኩባንያው ይልቅ ተጐጂ የሚሆኑት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርቱን በማከፋፈል የእለት ጉርሣቸውን የሚያገኙት አከፋፋዮች፣ ሬስቶራንቶችና የመሳሰሉት የንግድ ተቋማት ናቸው” ያለው ደመቀ፤ “ሃገሪቱም ከኮካ የምታገኘውን ገቢ ታጣለች፤ ይህ ማለት ግን መንግስት ይጐዳል ማለት አይደለም፤ ህዝብ ነው የሚጐዳው” ብሏል፡፡
ኮካ ኮላን ከመጠጣት እንቆጠብ (ቦይኮት እናድርግ) የሚለው ቅስቀሳ የመጣው ኩባንያው ከቴዲ አፍሮ ጋር የነበረውን ውል መሠረዙን ተከትሎ እንደሆነ ያስታወሰው አስተያየት ሰጪው፤ “ስሜታዊ ሆኖ ምርቱን ከመጠቀም እንቆጠብ ከማለት ይልቅ ለምን ውሉ ተቋረጠ፣ ስህተቱ የቱ ጋ ነው ያለው” የሚለውን መመርመር የተሻለ ነው ባይ ነው፡፡
የብሔራዊ ሚዲያው ጥንካሬ እየጎላ የሚመጣው አመዛዛኝ የሆኑ ፀሃፍት ተሳትፎ ሲያደርጉበት ነው የሚለው ደመቀ፤ አሁን ያለው አይነትን የዘመቻ ስራ የሚቀሰቅሱና የሚያካሂዱ ሰዎች ዘመቻቸው ፋይዳቢስ ከመሆኑም በላይ ማህበራዊ ሚዲያው ሊጫወት የሚገባውን በጐ ሚና የሚያዳፍን ነው ሲል ይቃወማል፡፡
ፌስ ቡክ በአሁን ሰአት በሁለት ፅንፎች መሃል ብቻ መጓዝን የሚፈቅድ ነው ያለው አስተያየት ሰጪው፤ ወይ ተቃውሞ ወይ ድጋፍ እንጂ መሃል ላይ ሚዛናዊ ለመሆን መሞከር እንደ ነውር የሚቆጠርበት መድረክ ነው ብሏል፡፡ እሱ በሚፅፋቸው ሚዛናዊ ፅሁፎች በተደጋጋሚ  ዘለፋ እንደሚሰነዘርበት ደመቀ ይናገራል፡፡ መሰል ስድቦችንና ፀያፍ ነገሮችን በመሸሽ ጥሩ ጥሩ ሃሳብ ያላቸው ብዕርተኞች ከመድረኩ እየሸሹ መሆኑንም አስተያየት ሰጪው ይገልፃል፡፡
“ቦይኮት መጥፎ ነው ጥሩ ነው ማለት ያስቸግራል”
ዳንኤል ብርሃነ
(የህግ ባለሙያና የHornaffairs.com ብሎግ ዋና አዘጋጅ)
Hornaffairs.com በተባለው ድረ - ገፁ ላይ በሚያሰፍራቸው የተለያየ ይዘት ያላቸው ጽሑፎች የሚታወቀው ዳንኤል ብርሃነ፤ ቦይኮት በድፍኑ መጥፎ ነው ጥሩ ነው ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ቦይኮት አስፈላጊ የሚሆንበትም የማይሆንበትም ጊዜ መኖሩን እንዳለ የሚገልፀው ዳንኤል፤ “ለምሳሌ “ቦይኮት በደሌ”ን ብንወስድ አርቲስት ቴዲ አፍሮ በእንቁ መጽሔት ላይ የተናገረው ተቆርጦ ቢወጣም ጥሩ አልነበረም፤ በመሆኑም ቦይኮት መደረጉ አግባብ ነው” ይላል፡፡ የኮካንና የቴዎድሮስ ካሳሁንን ጉዳይ በተመለከተ በሰጠው አስተያየትም፤ የቴዲ አፍሮ ዘፈን ከደረጃ በታች ነው ስለተባለ ቦይኮት ይደረግ ማለት ቀርቶ ለመቆጣት መነሳት አግባብነት እንደሌለው ይናገራል፡፡
“ቴዲ አፍሮ በኮካ ኮላ በደል ደርሶበታል ተበድሏል ለማለት ሙዚቃውን ማዳመጥ ነበረብን፤ ሙዚቃውን አዳምጠንና አጣጥመነው ቢሆን ኖሮ ፍርድ ለመስጠት ያመች ነበር” ብሏል-ፀሐፊው፡፡
ይህ ካልሆነም በቴዲ አፍሮም ሆነ በኮካ ኮላ በኩል ተጨባጭና አጥጋቢ መረጃ ወጥቶ ቢሆን ኖሮ ለፍርድ ያመች ነበር የሚለው ዳንኤል፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ኮካን ቦይኮት ለማድረግ በቂ መነሻ አለ ብዬ አላምንም ብሏል፡፡ ነገር ግን በኮካ ኮላ በኩል እንደ አገር ያጣነው እድል አለ ይላል፡፡
“ኮካ ኮላ መጀመሪያውኑ የቴዲን ሙዚቃ ብቻ ይዞ ከሚቀመጥ ተጠባባቂ አርቲስቶች ቢያዘጋጅ ኖሮ፣ የቴዲ ከደረጃ በታች ነው ሲባል ተጠባባቂውን ተክቶ አገራችን እድሉን መጠቀም ትችል ነበር” ብሏል፡፡ ኮካኮላ ይህን ባለማድረጉ ያጣነው እድል ያስቆጫል ሲልም አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡
“ቦይኮት አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም”
(አገኘሁ አሰግድ፤ የፌስቡክ ፀሀፊ)
በሶሻል ሚዲያው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ ተከታዮችን ያፈራው ፀሐፊ አገኘሁ አሰግድ፤ ቦይኮት አስፈላጊ ነው ብሎ እንደማያምን ይናገራል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዳም፤ ፌስ ቡክ ምሁራንና በምክንያታዊነት ታግዘው የሚፅፉም የሚያነቡም ሰዎች የሚታደሙበት ባለመሆኑ በአጠቃላይ ቦይኮት አስፈላጊ አይደለም የሚል ፅኑ እምነት እንዳለው ገልጿል፡፡ ሶሻል ሚዲያው የተለየ የእውቀት ደረጃ ያለው የማህበረሰብ ክፍል የሚታደምበት በመሆኑም አንዳንዴ ማድነቅና መውደድን እያምታታን ቦይኮት ድረስ እናደርሰዋለን ያለው አገኘሁ፤ እንዲህ አይነት ነገሮች አስተሳሰብ ላይ ችግር ስለሚፈጥሩ በአጠቃላይ ቦይኮት የሚባለውን ሃሳብ እንደማይቀበለው  ይናገራል፡፡
“ቦይኮት ከፅንፈኝነት እንደሚመጣ አምናለሁ” የሚለው ፀሐፊው፤  ቦይኮት ማድረግ ማለት የእኔ ብቻ ትክክል ነው በሚል ሀሳብ ተነሳስቶ የሌላውን መርገምና መኮነን ነው ይላል፡፡ “የራስን አሸብርቆና አዳንቆ የሌላውን ጥቁር መቀባት ደግሞ የእኔ ብቻ ትክክል ነው በሚል ሀሳብ ልዩነቶች እንዳይስተናገዱ ማነቆ ይሆናል” ሲል አስረግጦ ይናገራል፡፡ አንድ አካል አንድ ጥግ ላይ ሆኖ ሌላውን ጥግ ማንቋሸሽና ማጥላላት የፅንፈኝነት መገለጫ በመሆኑ፣ “እከሌ የተባለ ድርጅት ወይም አካል እንዲህ ስላደረገ ምርቱን መጠቀም እናቁም” ማለት ከፅንፈኝነት ውጭ ሌላ ስም የለውም ብሏል፡፡
“ቦይኮት ፈፅሞ ስህተት ነው ባልልም ጉዳቱ ግን ያመዝናል” ያለው አገኘሁ፤ ችግሮች ሲከሰቱ ያንን ቅሬታ የምንገልፅበትና ተቃውሞን የምናንፀባርቅበት በርካታ አማራጭ እያለ ቦይኮት ላይ መድረስ አይታየኝም ባይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ልዩ የሆነ ጉዳይ ሲያጋጥም ጉዳዩ በጥንቃቄ ተጠንቶ ጥቅምና ጉዳቱ ተመዝኖ ሊደረግ ይችላል ያለው አገኘሁ፤ ነገር ግን በትንሽ በትልቁ ውሀ ቀጠነ ተብሎ ቦይኮት የማድረግ ዘመቻ ለማንም ጥቅም እንደሌለው በአፅንኦት ይናገራል፡፡
ቴዲ አፍሮን ተከትለው የመጡትን “ቦይኮት በደሌን” እና “ቦይኮት ኮካ”ን በተመለከተ ሲናገር፤ “እኛ አገር ተደናቂነትና ተወዳጅነትን እናምታታዋለን” ያለው ፀሐፊው፤ “ቴዲ አፍሮ ተደናቂም ተወዳጅም አርቲስት በመሆኑ እንደ እምነት ሁሉ አድርገው ያዩታል፤ በሶሻል ሚዲያ ደግሞ በቡድን የማሰብ ነገር በመኖሩ፣ ቴዲን የነካ የእኛ ጠላት ነው በሚል ኮካን ቦይኮት የማድረግ ዘመቻ ተከፍቷል” ብሏል፡፡
“ዞሮ ዞሮ በእኔ እምነት የራስን ሀሳብና ፍላጎት ለማጉላት ሲባል፣ ሌሎችን መግፋትና ማንቋሸሽ በመሆኑ፣ እኔ ቦይኮት ባይኖር እመርጣለሁ፤  ይሄ ዓይነቱ ችግር የሚቀረፈው ግን ከስሜት ወጥተን ምክንያታዊ ሆነን ስናስብ ብቻ ነው” ያለው አገኘሁ፤ በእኛ አገር በሀሳብ ልዩነት የማመንና፣ የመቻቻል ባህላችን ደካማ በመሆኑ እነዚህን ደካማ ባህሎቻችንን ስናስወግድ ወደ ቦይኮት የምንሮጥበት አስተሳሰብ ይቀራል ብሏል፡፡
ኮካ ኮላን ቦይኮት ለማድረግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሲናገርም፤ በኮካ ኮላ ጥንካሬም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ዘመቻው በኩባንያው ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ እንደሌለ ገልጿል፡፡   

Read 14645 times Last modified on Saturday, 07 June 2014 13:26