Print this page
Saturday, 07 June 2014 13:16

አንድነት እና መኢአድ ነገ ቅድመ ውህደት ይፈራረማሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የአንድነት ዶክመንተሪ ሰሞኑን ለኢቴቪ ይላካል  
ጣቢያው  እንደሚላክ ገልጿል፡፡

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያውን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በነገው እለት የቅድመ ውህደት ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል አንድነት በፍርድ ቤት በተወሰነለት  መሰረት፣ በኢቴቪ የሚተላለፈውን ዶክመንተሪ ፊልም አዘጋጅቶ ማጠናቀቁን ጠቅሶ ሰሞኑን ወደ ጣቢያው  እንደሚላክ ገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ፓርቲው ከመኢአድ ጋር ከወር በፊት ሲያደርገው የነበረውን ውህደት ከጫፍ ደርሶ ከተጨናገፈ በኋላ በድጋሚ አዲስ የድርድር ኮሚቴ ተቋቁሞ ውይይቱ ቀጥሎ እንደነበር ያስታወሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃብታሙ አያሌው፣ ድርድሩ በጥሩ ሁኔታ በመከናወኑ የቅድመ ውህደት ስምምነቱን በነገው እለት ፓርቲዎቹ በተወካዮቻቸው አማካይነት ይፈራረማሉ ብለዋል፡፡
የቅድመ ውህደት ስምምነቱ እንደ በፊቱ ከጫፍ ደርሶ ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት የለበትም ያሉት ኃላፊው፣ በሁለቱም በኩል የሚፈራረሙት ተወካዮች አስቀድመው መታወቃቸውና ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም “የቅድመ ውህደቱ ፊርማ ይፈረም” የሚለው ውሳኔ ዋስትና ይሆናል፣ የስምምነት ፊርማውም ያለ እንከን ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢቴቪ “አኬልዳማ” የተሰኘ በሽብር እና ሽብርተኝነት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ፕሮግራም ሲያቀርብ የፓርቲዬንና የአባላቱን ስም ያለአግባብ ወንጅሏል፣ የስም ማጥፋት ስራም ሰርቷል ሲል ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ የመሰረተው ፓርቲው፣ በክሱ ኢቴቪን መርታቱን ተከትሎ ስሙን የሚያድስ ፕሮግራም ሰርቶ እንዲያቀርብ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል፡፡
ፓርቲው ለዚህ ዶክመንተሪ ስራ ኮሚቴ በማዋቀር ዘጋቢ ፕሮግራሙን ሲያዘጋጅ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ሃብታሙ፣ የስራ አስፈፃሚ በ25፣ በ15 እና በ35 ደቂቃዎች የተዘጋጁትን ዶክመንተሪዎች ገምግሞ የተስማማበትን ከመረጠና ካፀደቀ በኋላ ሰሞኑን ለኢቴቪ በመላክ  እንዲተላለፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የዶክመንተሪዎቹን ዝርዝር ይዘት ከመግለፅ የተቆጠቡት ኃላፊው፣ የሚተላለፈው ፕሮግራም “በአኬልዳማ” የጠፋውን የፓርቲውንና የአባላቱን ስም የሚጠግን ጠንካራ ይዘት ነው ያለው ብለዋል፡፡
ካሣ አጠያየቁን በተመለከተ አራት የህግ ባለሙያዎች ከህግ አንፃር አጠያየቁን እየመከሩበት መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ከፓርቲው የሚፈልጉት መረጃ ቀርቦላቸው የካሣና ጉዳት መጠኑን አስልተው ለስራ አስፈፃሚው ካቀረቡ በኋላ በይፋ የሚጠየቀው የገንዘብ መጠን ይገለፃል፤ ጥያቄውም ከዶክመንተሪው ጋር አብሮ ይቀርባል ብለዋል፡፡
ኢቴቪ የፍ/ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሎ የነበረ ቢሆንም ስለ ይግባኙ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም ብለዋል- አቶ ሃብታሙ፡፡

Read 2802 times