Saturday, 07 June 2014 13:15

የባለስልጣናቱ ሀብት መጠን በመጪው ዓመት ይፋ ይደረጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

- 80 ሺህ ባለስልጣናት እና ሰራተኞች ሃብታቸውን አስመዝግበዋል
- የተደበቀ ሃብት የጠቆመ የሃብቱን 25 በመቶ ይወስዳል
- ህንዳውያን ባለሙያዎች መረጃውን በየፈርጁ እያጠናቀሩ ነው

    የፌደራል የስነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ የመንግስት ባለስልጣናት እና ሰራተኞችን ሃብት መመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን እስከ ቀጣይ ዓመት መረጃን የማደራጀት ስራው ተጠናቆ የእያንዳንዱ ባለስልጣናትና ሰራተኛ የሃብት መጠን ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በመጋቢት 2002 የሃብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁን ተከትሎ በህዳር 2003 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የባለስልጣናትና የመንግስት ሰራተኞች የሃብት ምዝገባ በ6 ወር ውስጥ ተጠናቆ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ይህ ሳይፈፀም 3 ዓመት ከ6 ወር አስቆጥሯል፡፡  መረጃውን ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ለምን እስከዛሬ ዘገየ የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው የኮሚሽኑ የትምህርት ስልጠና ክፍል ኃላፊና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ተጠሪ አቶ ብርሃኑ አሰፋ፤ ሃብት የማስመዝገብና የመመዝገቡ ተግባር አስቀድሞ ሲታቀድ እስከ 22 ሺህ የሚደርሱ ባለስልጣናትንና ሰራተኞችን ያስመዘግባሉ ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን ቁጥሩ ከተገመተው በላይ መሆኑ፤ የልምድ እና የእውቀት ማነስ እንዲሁም መረጃው ለህዝብ በሚተላለፍበት መንገድ ላይ የተደረገው ጥናት ሰፊ ጊዜ መውሰዱ ተደማምረው ሂደቱን እንዳዘገዩት ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የፋይናንስ ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁን ወቅት የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በማድረጉም መረጃውን የማደራጀትና ለህዝብ ይፋ የሚደረገውን የማጠናቀር ተግባር ለህንዳውያን ባለሙያዎች መሰጠቱን የገለፁት ኃላፊው፤ በመጪው  ዓመት መረጃው ለህዝብ ይፋ ይደረጋል  ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የተሰበሰቡትን መረጃዎች በየፈርጁ ማደራጀት ራሱን የቻለ ጊዜ የሚወስድ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በየ2 ዓመቱ ሪፖርት ከማዘጋጀት ጎን ለጎን ስለ ባለስልጣናቱ ሃብት ለጠየቁን የህግ አካላትም መረጃ ስናቀርብ ቆይተናል ብለዋል፡፡ ከ500 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦችን የሃብት መጠን ከኮሚሽኑ የምርመራ ስራና ከህግ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች እንደተጠቀሙባቸውም  ገልፀዋል - ኃላፊው፡፡ ሃብትን በሌላ ሰው ስም በማከማቸት የመደበቅ ሙከራዎች እንደሚያጋጥሙ የሚገልፁት ኃላፊው፤ ኮሚሽኑ እንዲህ ያለውን ጉዳይ አልፎ ሄዶ የማጣራት አቅም ባይኖረው እንኳ ቆይቶ ዋጋ ያስከፍላል ይላሉ፡፡ አንድ ሰው ሃብቱን በሌላ ሰው ስም ሲያስመዘግብ በህግ የራሴ ነው ብሎ መከራከር እንደማይችል ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፤ በዚህ መሃል ንብረቱን ሊያጣ ይችላል ብለዋል፡፡
“ባለስልጣናት ንብረታቸውን በሌላ ሰው ስም ያስመዘግባሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው” ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ድርጊቱን ይበልጥ ለመከላከልና ለማጋለጥ ግለሰቡ ያስመዘገበውን የሃብት መጠን ይፋ ማድረግ አንደኛው መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡ ሃብቱ ይፋ ሲደረግ ህብረተሰቡ የሚያውቀው የተደበቀ ሃብት ካለ ጥቆማ ሊያቀርብበት እንደሚችል ጠቅሰው፤የተጠቆመው ሃብት ተጣርቶ እውነት ከሆነ ሙሉ ለሙሉ ይወረሳል፣ ከተወረሰው ሃብት ላይም ጠቋሚው 25 በመቶውን ይወስዳል  ብለዋል፡፡ አዳዲስ የመንግስት ተሿሚዎችና ሰራተኞች በየተቋማቱ ባሉ የስነ-ምግባር መኮንኖች አማካይነት እንዲመዘገቡ የሚደረግ ሲሆን ተሿሚዎችም ሆኑ ሰራተኞች ከአንድ መስሪያ ቤት ሲለቁም ሆነ በጡረታ ሲሰናበቱ መልቀቂያ የሚሰጣቸው በድጋሚ ሃብታቸውን ካስመዘገቡ በኋላ እንደሆነ አቶ ብርሃኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
በዓለም ላይ 149 ሃገሮች የመንግስት ባለስልጣናትንና ሰራተኞችን ሃብት መዝግበው የሚይዙ ሲሆን አሰራሩም ግለሰቦች ከገቢያቸው በላይ በሙስና ሃብት እንዳያካብቱ ያግዛል ተብሎ እንደሚታመንበት  መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

Read 3259 times