Print this page
Saturday, 07 June 2014 13:04

ሬሣ ለምን ከበደ? ሀሳቡን ሰው ላይ ስለጣለ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

                (ሬሣ ብምንታይ ከበደ? ሃሳቡ ኣብ ልዕሊ ሳብ ኣውዲቑ)

               አንድ የታወቀ ተረት እንዲህ ይላል፡፡ አንድ ድንቅዬ ወጣት የሰራዊት አባል የሆነ ገበሬ፤ ባህር ማዶ ተሰዶ ሳለ፤ አንድ ደብዳቤ ከሚስቱ ተልኮለት ኖሮ ይደርሰዋል፡፡ ሚስትየውን ያስጨነቃት ነገር አለ!! ግቢያቸው ውስጥ ድንች ለመትከል ፈልጋ ኖሮ፤ ምን ማድረግ እንዳለባት ልትጠይቀው ነው፡፡ “በምስራቅ በኩል ልዝራው? በደቡብ በኩል ልዝራው?” የሚል ነው የደብዳቤው ጭብጥ፡፡ “ምንም አድርገሽ ምን፤ ወደ ምሥራቅ ያለውን የቤታችንን ወገን እንዳትቆፍሪው ምክንያቱም ብዙ መሣሪያ የቀበርኩት እዚያ ጋ ነው!” ይላል ወታደር ባሏ! በዚያን ጊዜ በጦርነት ወቅት ደንብ እንደሆነው ሁሉ፣ ደብዳቤ ሁሉ ተቀዶ ተነቦ ነው ለባለቤቱ የሚተላለፈው፡፡ ስለዚህ በሳንሱር ሐላፊው ተነበበ፡፡ ስለጉዳዩ ምንም እውቀት የሌላት ሚስቱ ከጥቂት ቆይታ በኋላ፣ ተቆጥታ የፃፈችለት ደብዳቤ መጣ፡- “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወታደሮች የግቢውን ዙሪያ - ገባውን ሲቆፍሩት አመሹ! እሺ ምን ማድረግ ነው ያለብኝ?” የሚል የንዴት መለስ ደብዳቤ ነው የላከችለት፡፡ ወታደሩም፤ “በቃ ቆፍረው ከጨረሱማ፤ ድንቻችንን መትከል ጀምሪ!” አላት፡፡

                                             * * *

    የምናስበው ጠባብ መሬት (ሁዳድ) ሆና ሳለ፤ እሷኑ ማንም ሊወስድብን እንደሚችል ማመዛዘን ጤና ነው፡፡ ያለችንን ትንሽ ሊወርብን የሚችል ኃይል ሊኖር እንደሚችል ልብ እንበል፡፡ ያም ሆኖ “ሳይደግስ አይጣላም አንዘንጋ፡፡ (Blessing in disguise) በእርግጥ ምንም ዓይነት አገራዊ ጉዳይ ላይ ብንጠመድ፤ ሚስጢራዊነትን፣ ድብቅነትንና ልብ-ለልብ አለመናበብን፣ ካላስወገድን አባዜያችን ብዙ ነው፡፡ ምንም ያህል ዕቅድ ቢኖረን፣ ምንም ያህል ስትራቴጂ ቢኖረን፣ ምንም ዓይነት ልዩ ፕሮግራም ቢኖረን፣ ሚስጢራዊ ካደረግነውና ከህዝብ ካራቅነው ዞሮ ዞሮ “ቡመራንግ” ነው የሚሆነው፡፡ የተኮስነው መልሶ ሲመታን እንደማለት ነው፡፡ በዚህ አንፃር እነሱ ካረሱልሽ አንቺ ምን ቸገረሽ?!” የሚለው ወልዕክት ቀላል አይደለም፡፡ “ባልሽ አቂሞኛል ጅልሽ አቂሞኛል፤ አጋዡ ነኝ እንጂ፣ ጎባኑ አድርጎኛል!” የሚል ዘፈን ያስታውሰናል፡፡ (ጎባኑ እንግዲህ ሚስቱን የወሸመበት ሰው መሆኑ ነው፡፡አገዝኩት እንጂ ምን አጠፋሁ? ነው ነገሩ) ያም ሆኖ፣ ደብዳቤው መቀደዱ ይቅርና፣ የፃፍነው ሁሉ የሚነበብ፣ የምንተነፍሰው ሁሉ በየትንፋሹ መካከል ሊመረመር የሚችል፤ መሆኑን ማስተዋል አሊያም የዜግነት ግዴታም፣ ኃላፊነትም ወይም በሁለቱም፤ የሚያስኬድ ጉዳይ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ የሀሳብ፣ የመናገር፣ የመፃፍ ነፃነት ወገናዊነትን አያውቅም፡፡ ዲሞክራሲ ውሉን ይስታልና፡፡ ማናቸውንም ኃላፊነት ስንወጣ፤ እኛ፣ ለእኛ፣ በእኛ መሆን አለበት፡፡

ለእኛነታችን ለምናቀርበው ማስረጃ ከጀርባችን ያለ ሰው አያስፈልገንም፡፡ ለ Ghost-waiter እንዲሉ ፈረንጆች፡፡ መተጋገዝ አንድ ሃገር ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ በሌሎች ድጋፍ መኖር ግን ክፉ አባዜ ነው፡፡ የራስ ዕሴት ወይም ማንነት ከናካቴው ይጠፋልና! ይሄን ከልብ ያስተዋለ ሊቅ ነው “ሬሣ ለምን ከበደ? ሀሳቡን ሰው ላይ ስለጣለ” ብሎ የተረተው!!

Read 3907 times
Administrator

Latest from Administrator