Saturday, 31 May 2014 14:45

የዓለማችን ዝነኛ ደራስያን አስገራሚ እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(6 votes)

       ኧርነስት ሚለር ሄሚንግዌይ፡ 1899 – 1961 - አሜሪካዊው ደራሲ ሄሚንግዌይ፤ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥነፅሁፍ  ከመግባቱ በፊት በጋዜጣ ሪፖርተርነት የሰራ ሲሆን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት  ለአሜሪካ ቀይ መስቀል በአምቡላንስ ሹፌርነትም አገልግሏል፡፡ ወደ ድርሰቱ ዘልቆ ከገባ በኋላ Men without Women በሚል ርእስ  የአጭር ልብወለድ ሥራዎቹን አሰባስቦ ያሳተመ ሲሆን  በመቀጠልም A Farewell to Arms በሚል ርእስ ረዥም ልብወለዱን አሳትሟል፡፡
በልብወለድ ሥራ የፑልቲዘር ሽልማት ያሸነፈበት The Old Man and the Sea ከአስር  ዓመት በፊት በደራሲና ተርጓሚ መስፍን አለማየሁ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለአንባቢያን የደረሰ ሲሆን ብዙዎች ማራኪ ሆኖ መተርጎሙን መስክረውለታል፡፡ በነገራችን ላይ የአገራችን አንባቢያን ለብዙዎቹ የሔሚንግዌይ ሥራዎች በተለይ ለአጭር ልብወለዶቹ  እንግዳ አይደሉም፡፡ ጥቂት የማይባሉ አጭር ልብወለዶቹ ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ሲሆን የተወሰኑት በእዚሁ ጋዜጣ ላይ መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
በተሲያት በኋላው ሞቃት አየር ሳቢያ  ጠዋት ጠዋት መፃፍ እንደሚያዘወትር የገለፀው ደራሲው፤ በቀን አንድ ገፅ ከሩብ ገደማ ይፅፍ ነበር፡፡ ሥነፅሁፍ በብዛት በማምረት ትጋቱ የሚታወቀው ሄሚንግዌይ፤ መቼ መስራትና  መቼ ማቆም እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እ.ኤ.አ በ1934 ዓ.ም ለጓደኛው ለኤፍ. ስኮት ፊትዝጌራልድ በፃፈው ደብዳቤ “አንድ ገፅ ምርጥ ሥራና ዘጠና አንድ ገፆች  ዝባዝንኬ እፅፋለሁ፡፡ ዝባዝንኬውን ታዲያ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ለመጣል እሞክራለሁ” በማለት የአፃፃፍ ልማዱን ጠቁሞታል፡፡ ዝነኛው ደራሲ ሄሚንግዌይ፤ በፑልቲዘር ሽልማት ብቻ ግን አልረካም፡፡ እናም  እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም የሥነፅሁፍ የኖቤል ሽልማት ለማሸነፍ በቃ፡፡

ትሩማን ካፖቴ፡ 1924-1984 - አሜሪካዊው የረዥም ልብወለድ፣ የፊልም ፅሁፍና የቴአትር ደራሲ የነበረው ካፖቴ፤ እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም በፃፈው In Cold Blood የተሰኘ ዝነኛ ኢ-ልብወለዱ  ይታወቃል፡፡
ይሄ ሥራው ለአንባቢ በበቃ በዓመቱም ወደ ፊልም ተቀይሮ ለተመልካች ቀርቧል- በተመሳሳይ ርእስ፡፡ እውነተኛ ታሪኮችን በልብወለድ የአፃፃፍ ቴክኒክ በማቅረብ ዝነኝነት ያተረፈው ደራሲው፤ ኒው ጆርናሊዝም የተሰኘ አዲስ የአፃፃፍ ስልትን እንዳስተዋወቀ ይነገርለታል።
ካፖቴ በጀርባው ተንጋሎ በአንድ እጁ ሼሪ የተቀዳበት ብርጭቆ፣ በሌላ እጁ ደግሞ እርሳስ ከያዘ ሊፅፍ ተዘጋጅቷል ማለት ነው፡፡ በ1957 ዓ.ም ለፓሪስ ሪቪው በሰጠው ቃለ-ምልልስ፤ ካልተጋደምኩ በቀር ማሰብ አልችልም ብሏል። “አልጋ ላይ ወይም ሶፋ ላይ ሰውነቴን ዘርግቼ በእጄ ሲጋራና ቡና መያዝ አለብኝ፡፡ እያጨስኩና ፉት እያልኩ ነው ለመፃፍ የምዘጋጀው፡፡” ሲል የአፃፃፍ ልማዱን ገልጿል፡፡ እንደ አብዛኞቹ ፀሃፍት ከአዕምሮው የመጣለትን ሃሳብ በቀጥታ በመተየቢያ ማሽን ላይ መፃፍ እንደማይሆንለት የተናገረው ካፖቴ፤ የመጀመሪያ ረቂቅ ፅሁፉን በእርሳስ እንደሚፅፍ፣ ከዚያም ሙሉውን  እየከለሰ በእርሳስ ከፃፈ በኋላ ወደ ታይፕ እንደሚገባ በቃለ-ምልልሱ ወቅት አስረድቷል፡፡

ፍላነሪ  ኦ’ኮኖር፡ 1925-1964 – በ20ኛው ክ/ዘመን የአሜሪካ ሥነፅሁፍ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ምርጥ የአጭር ልብወለድ ደራሲያን መካከል  ትጠቀሳለች፡፡ የመጀመርያ የአጭር ልብወለድ መድበሏ A Good Man is Hard to Find ይሰኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም The Complete Stories በሚል ሥራዋ የናሽናል ቡክ አዋርድስ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ዘ ሃቢት ኦፍ ቢይንግ በተባለው መፅሃፍ ላይ ስለአፃፃፍ ልማዷ ስታስረዳ፤ “በየቀኑ ለሁለት ሰዓታት ብቻ ነው የምፅፈው፤ ምክንያቱም ከዚያ በላይ አቅም የለኝም፤ በእነዚህ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ግን ምንም ነገር ከሥራዬ እንዲያናጥበኝ አልፈቅድም” ብላለች፡፡  
ፍራንሲን ፕሮዝ፡  የBlue Angel መፅሃፍ ደራሲና የፔን አሜሪካ ማዕከል ፕሬዚዳንት የነበረችው ፕሮዝ  ለየት ያለ የአፃፃፍ ልማድ አዳብራለች። ምንም ጊዜም ስትፅፍ፤ የባለቤቷን ቀይና ጥቁር ስኩዌር ያለው ፒጃማ ሱሪና ቲ-ሸርት እንደምትለብስ ለዴይሊ ቢስት ተናግራለች፡፡ “በመታደልም ይሁን ባለመታደል ለየት ባለ አፓርትመንት ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ 120 ጫማ ከፍታ ያለው መስኮታችን፤ ፊቱን የሰጠው ለተንጣለለ ባህር ወይም ጥቅጥቅ ደን አይደለም፡፡ ከመስኮቱ በአንድ ጫማ ተኩል ርቀት የጡብ ግድግዳ ተገትሯል፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይንንና ቀልብን የሚሰርቅ ነገር የለም፡፡ ልፅፍ ስቀመጥ ትኩረቴ ሳይከፋፈል ልሰራ እንደምችል ይሰማኛል” ብላለች- አሜሪካዊቷ ደራሲ ፍራንሲን ፕሮዝ፡፡

Read 4915 times