Saturday, 31 May 2014 14:33

ከሞት ጋር ድርድር

Written by  ድርሰት - ውዲ አለን ትርጉም - ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(8 votes)

(ተውኔቱ የሚካሄደው የናት አኬርማን ባለ ሁለት ፎቅ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው፡፡ መጋረጃው ከግድግዳው ጥግ እስከ ጥግ ተንጠልጥሏል፡፡ ትልቅ አልጋና የመልበሻ ጠረጴዛ ይታያል፡፡ ግድግዳው ላይ  የተለያዩ ስዕሎችና እምብዛም ማራኪ ያልሆነ የነፋስ ግፊት (ባሮ ሜትር) ተንጠልጥሏል፡፡ መጋረጃው ሲገለጥ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ይንቆረቆራል፡፡ መላጣው እና ቦርጫሙ የ57 ዓመቱ ቀሚስ አምራች ናት አኬርማን፣ አልጋው ላይ ተጋድሞ ጋዜጣ ያነባል፡፡ ጊዜው እኩለ ሌሊት አቅራቢያ ነው፡፡ ድንገት ኮሽታ ይሰማል፤ ናት ከመቅፅበት ከተኛበት ተነስቶ ቁጭ ይልና ወደ መስኮቱ ትክ ብሎ ይመለከታል፡፡)
ናት፡ ምንድን ነው የማየው?
(ጥቁር ኮፍያ ያደረገ አስፈሪ ፍጡር ይታያል። ከሰውነቱ ጋር የተጣበቀ የሚመስል ጥቁር ልብስ ለብሷል፡፡ ኮፍያው አናቱን ሸፍኖታል፤ ፍፁም ነጭ የሆነ ፊቱ ግን ተጋልጦ ይታያል፡፡ የሰውየው ቁመናና መላ ገፅታው ናትን ይመስላል፡፡ ቁና ቁና እየተነፈሰ የመስኮቱን ደፍ ዘልሎ፣ ክፍሉ ውስጥ ዱብ ይላል፡፡)
ሞት፡ በኢየሱስ ስም! አንገቴ ተሰብሮ ነበር እኮ!
ናት፡ (ግራ በመጋባት እያየው) አንተ ማን ነህ?
ሞት፡ ዘና ብሎ ሞት ነኝ፡፡
ናት ፡ ማን?
ሞት፡ ሞት ነኝ፡፡ ስማኝ ይልቅ…ትንሽ ቁጭ ልበል? አንገቴን ልሰብረው ነበር‘ኮ፡፡ እንደ ቅጠል እየተርገፈገፍኩ ነው የወረድኩት፡፡
ናት ፡ (ግራ እንደተጋባ) ማን ነህ ግን አንተ?
ሞት፡ ሞት ነኝ አልኩህ እኮ! እስቲ ውሃ አጠጣኝ?
ናት ፡ ሞት ነኝ? ምን ማለት ነው ሞት ነኝ ማለት?
ሞት፡ ያምሃል እንዴ? ጥቁር ልብሴና ነጭ ፊቴ አይታይህም?
ናት ፡ ይታየኛል፡፡
ሞት፡ ቆይ ዛሬ የቅዱሳን ዝክረ በዓል (ሀሎዊን) ነው እንዴ?
ናት ፡ ኧረ ይደለም፡፡
ሞት፡ ስለዚህ ሞት ነኝ ማለት ነው፡፡ እሺ አሁንስ ውሃውን አትሰጠኝም? ለስላሳም ቢሆን ግዴለኝም፡፡
ናት ፡ እየቀለድክ ነው አይደል?
ሞት፡ የምን ቀልድ ነው? ዕድሜህ - ሃምሳ ሰባት፣ ስምህ ናት አኬርማን፣ የቤት ቁጥርህ…አንድ መቶ አስራ ስምንት አይደል? መቼም እንዳልተሳሳትኩ እርግጠኛ ነኝ …የታለ ያ የመጥሪያ ወረቀት? (ከኪሱ ውስጥ አድራሻ የተጻፈበት ወረቀት አወጣና አረገገጠ፡፡)
ናት ፡ እሺ ከእኔ ምንድን ነው የምትፈልገው?
ሞት፡ ምን የምፈልግ ይመስልሃል?
ናት፡ አትቀልድ ሰውዬ! እኔ ፍፁም ጤናማ ሰው ነኝ፡፡
ሞት፡ (በመሰልቸት ስሜት) ምን ታደርገዋለህ እንግዲህ፡፡ (ዙሪያ ገባውን እየቃኘ) በጣም ደስ የሚል ቤት አለህ፡፡ ራስህ ነህ ያበጃጀኸው?
ናት፡   አይ፤ ለባለሙያ ከፍለን ነው ያሠራነው፤ ግን አግዘናታል!
ሞት፡  (ግድግዳው ላይ ያለውን ስዕል እያየ) ትልልቅ ዐይኖች ያላቸው ሕጻናት እንዴት እንደምወድ…
ናት፡   እኔ ግን አሁን መሄድ አልፈልግም፤ ገና ነኝ፡፡
ሞት፡   መሄድ አትፈልግም? በናትህ ክርክር እንዳትጀምረኝ፡፡ መውጣት መውረዱ ራሱ እንዴት እንዳጥወለወለኝ አልነግርህም!
ናት፡    የምን መውጣት መውረድ?
ሞት፡    አሸንዳው ላይ ተንጠላጥዬ ነበር፡፡ ወደ ቤትህ በተለየ መንገድ ለመግባት ነበር ያሰብኩት። እንቅልፍ እንዳልወሰደህ ሳይ ሃሳቤን ለመተግበር ወሰንኩ፡፡ እላይ ወጥቼ አለ አይደል…ድንገት ዱብ ልል ፈልጌ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው፤ የሆነ ሀረግ ነገር እግሬን አስሮ ያዘኝ፤ አሸንዳውም ተሰበረ፤ አንዲት ሰበዝ ብቻ ናት አንጠልጥላ የያዘችኝ፡፡ ከዚያ ኮፍያዬም መቀደድ ጀመረ፡፡ አሁን እሱን ተወው በቃ! ይልቅ ተነሳና እንሂድ!
ናት፡  አሸንዳዬን ሰበርከው ማለት ነው?
ሞት፡  አልተሰበረም‘ኮ፡፡ አጠፍ ነው ያለው። አንተ ግን ስፈጠፈጥ ግን ምንም ድምፅ አልተሰማህም?
ናት፡   እያነበብኩ ነበር…
ሞት፡  በጣም ተመስጠህ ነበር ማለት ነው፡፡ (ናት እያነበበው የነበረውን ጋዜጣ አንስቶ ይመለከታል) “አደንዛዥ ዕፅ በቡድን ሲያጨሱ የነበሩ ተማሪዎች ጋማ ተባሉ” እስቲ አውሰኝ?
ናት፡  ገና አንብቤ አ ልጨረስኩም፡፡     
ሞት፡   እ…እንዴት ብዬ እንደምነግርህ አላውቅም፤ ጓደኛዬ አንተኮ…
ናት፡   ቆይ ለምንድን ነው በስነ ስርዓቱ የበሩን ደወል ያልደወልከው? በህገ ወጥ መንገድ መግባቱ ለምን አስፈለገ?
ሞት፡   እየነገርኩህ፤ እንደዛ ማድረግ እችል ነበር እኮ! ግን ሰርፕራይዝ ላደርግህ ፈልጌ ነው፡፡ አየህ በዚህኛው መንገድ የሆነ ድራማ ነገር አለው፡፡ “ፎውስት”ን አንብበሃል?
ናት፡    ምን?
ሞት፡   ቆይ እሺ ከእንግዶች ጋር ብትሆን ኖሮስ? እዚህ አንተ ከትልልቅ ሰዎች ጋር ቁጭ ብለሃል እንበል፡፡ እኔ ደግሞ ሞት ነኝ…የበር ደወል ደውዬ እየተንከራፈፍኩ ልግባልህ? እንዴት እንዴት ነው የምታስበው?
ናት፡    ስማ ሰውዬ፤ በጣም መሽቶብሃል
ሞት፡   ልክ ነህ፡፡ ተነሳ እንሂዳ?
ናት፡  የት ነው የምሄደው?
ሞት፡    ወደ ሞት ነዋ! እዚያ…ወንዞቹ ወተት፤ ድንጋዮቹ ዳቦ ወደሆኑበት፡፡ ታውቃለህ፤ (ጉልበቱን እያየ) በጣም ነው የቆሰለው፡፡ ገና በመጀመሪያ ሥራዬ ጋንግሪን ሳይዘኝ አይቀርም፡፡
ናት፡   እኔ ትንሽ ጊዜ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ለመሄድ ዝግጁ አይደለሁም፡፡  
ሞት፡   በጣም አዝናለሁ፡፡ ምንም ልረዳህ አልችልም፡፡ በቃ ጊዜው ደርሷል፡፡
ናት፡   እንዴት ነው ጊዜው የደረሰው? ከሞዲስት ኦሪጂናልስ (ቀሚስ አምራች ድርጅት) ጋር ሽርክና የገባሁት አሁን አይደል እንዴ?
ሞት፡  የተወሰነ ተጨማሪ ገንዘብ መጣ ቀረ …ምን ለውጥ አለው ብለህ ነው?
ናት፡    አንተን ይመለከትሃል?
ሞት፡   አሁን እሺ ትሄዳለህ አትሄድም?
ናት፡    (በአትኩሮት እያየው) በጣም አዝናለሁ፤ ሞት መሆንህን አምኜ ለመቀበል አቅቶኛል፡፡
ሞት፡   ምን? ማንን ጠብቀህ ነበር…ሮክ ሃድሰንን? (ሮክ ሃድሰን በኤድስ የሞተ አሜሪካዊ አክተር ነው)
ናት፡    አይ፤ እንደዚያ አይደለም፡፡
ሞት፡   ያልጠበከው ዓይነት ሞት ከሆንኩብህ ይቅርታ፡፡
ናት፡  ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ ሁልጊዜ በሀሳቤ …ረጅም ሆነህ ነበር የምትታየኝ…  
ሞት፡ ሜትር ከሰባ ነኝ፡፡ ከክብደቴ ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡
ናት፡    እኔን ትመስላለህ ልበል?
ሞት፡   እና ማንን ልምሰል? ያንተ ሞት ነኝ‘ኮ!
ናት፡   እሺ በቃ ትንሽ ጊዜ ስጠኝ፡፡ የአንድ ቀን ጊዜ እፈልጋለሁ፡፡
 ሞት፡  እሺ እንድልህ ነው? አልችልም!
 ናት፡   አንድ ተጨማሪ ቀን፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ብቻ!
ሞት፡   ምን ትሠራበታለህ? ሬዲዮው ነገ ዝናባማ ቀን እንደሚሆን ተናግሯል፡፡
ናት፡    ቆይ ቼዝ ትችላለህ?
ሞት፡   አይ፤ አልችልም፡፡
ናት፡  ፎቶ ላይ ግን ቼዝ ስትጫወት ያየሁ መሰለኝ፡፡
ሞት፡ ተሳስተሃል እኔ ቼዝ መጫወት አልችልበትም፡፡ ባይሆን ካርታ ጨዋታ እችላለሁ፡፡
ናት፡     ካርታ ትችላለህ?
ሞት፡   መጠየቁስ!
ናት፡    በደንብ ትችላለሃ?
ሞት፡   አሳምሬ!
ናት፡    ምን ለማድረግ እንዳሰብኩ ልንገርህ…
ሞት፡ ከእኔ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር ለማድረግ ግን እንዳታስብ!
ናት፡  ካርታ እንጫወትና አንተ ካሸነፍከኝ ወዲያውኑ ተነስተን እንሄዳለን፡፡ እኔ ካሸነፍኩ ግን ትንሽ ጊዜ ትሰጠኛለህ፡፡ የአንድ ቀን ጊዜ!
ሞት፡    እስቲ አሁን በየትኛው ጊዜ ነው ካርታ የምንጫወተው?
ናት፡   ግዴለህም፡፡ በደንብ የምትችል ከሆነ እንጫወት፡፡
ሞት፡    ግን ከአንድ ጨዋታ ……
ናት፡    በእኔ ይሁንብህ… ፈታ በል፡፡ ለግማሽ ሰዓት ያህል እንጫወት፡፡
ሞት፡   ግዴለህም ይቅርብኝ፡፡
ናት፡    ይሄው ካርታው… ለምን ታካብዳለህ?
ሞት፡    እሺ ይሁን… ትንሽ እንጫወትና… ለነገሩ እኔንም ዘና ያደርገኛል
ናት፡   (ካርታ፣ ማስታወሻ ደብተርና እርሳስ እያመጣ) ግዴለህም ምንም አትቆጭበትም!
ሞት፡   ባክህ ጅንጀናህን ተወኝ፡፡ ካርዱን አምጣውና ለስላሳ ነገር ስጠኝ፤ እሚበላ ነገርም አምጣ፡፡ ኧረ በእግዚአብሔር… እንግዳ ሲመጣ የምታቀርበው ቺፕስ ምናምን እንኳን  የለህም?
ናት፡    ታች ቤት ከረሜላዎች አሉኝ፡፡
ሞት፡   ከረሜላ? ቆይ ድንገት ፕሬዚዳንቱ ቢመጡስ… ከረሜላ ልትሰጣቸው ነው?
ናት፡   አንተ ፕሬዚዳንቱ አይደለህማ!
ሞት፡  ና እሺ ጀምር…
ናት፡   ጨዋታው እንዲያምር በሳንቲም ቢሆንስ?
ሞት፡  አሁን አያምርም?
ናት፡   በሳንቲም ሲሆን የተሻለ ስለምጫወት ነው፡፡
ሞት፡   እንዳልክ ይሁንልህ፤ ኔውት፡፡
ናት፡    ናት ነው ስሜ፡፡ ናት አኬርማን፡፡ ስሜን ሳታውቅ ነው እንዴ…?
ሞት፡   ኔውት…ናት…ባክህ ተወኝ…ራሴን አሞኛል።
ናት፡    አምስት ቁጥርን ትፈልገዋለህ?
ሞት፡   አይ፡፡  
ናት፡   እና ሳብ እንጂ፡፡
ሞት፡  (እየሳበ እያለ በእጁ ያሉትን ካርታዎች እያየ) በኢየሱስ ስም፤ ምንም የረባ ነገር የለኝም፡፡
ናት፡   ቆይ ግን ምን ይመስላል?
ሞት፡  ምኑ?
 (ከዚህ ቀጥሎ ብዙ ካርታ ያነሳሉ፤ ይጥላሉ)
ናት፡   ሞት?
ሞት፡   ምን እንዲመስል ትፈልጋለህ? በቃ ጋደም ማለት ብቻ ነው!
ናት፡    ከዚያ በኋላስ ምን አለ?
ሞት፡  አሃ…ሁለትን አነሳህ?
ናት፡   እየጠየኩህ እኮ ነው፡፡ ከዚያስ በኋላ ምን አለ?
ሞት፡ (በተከፈለ ልብ) ራስህ ታየዋለህ ምን አስቸኮለህ?
ናት፡   ስለዚህ የሚታይ ነገር አለ ማለት ነው?
ሞት፡ ምናልባት እንደዚያ ብዬ መግለፅ አልነበረብኝም፡፡ አሁን ጣል?
ናት፡ ውይ፤ አንተን ጠይቆ መልስ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡
ሞት፡   ካርታ እየተጫወትኩ እኮ ነው፡፡
ናት፡    እሺ፤ ያዝ፤ ተጫወት፡፡   
ሞት፡ ቀስ በቀስ ካርዶቼን በሙሉ ሰጥቼህ ልጨርስ ነው፡፡
ናት፡    የተጣሉትን ካርታዎች አትይ እንጂ!
ሞት፡ ኧረ አላየሁም፡፡ እያስተካከልኳቸው ነው። ማሸነፊያው ስንት ነበር?
ናት፡  አራት፡፡ ልትጨርሰው ነው?
ሞት፡ ማን ልጨርስ ነው አለ? የጠየቅሁት ማሸነፊያው ስንት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡
ናት፡   እኔ ደግሞ የጠየኩህ በተስፋ ልጠብቀው የሚገባኝ ነገር መኖር አለመኖሩን ነው፡፡
ሞት፡  ተጫወት፡፡
ናት፡  በቃ አንዳንድ ነገር እንኳን አትነግረኝም? ቆይ ግን እኛ ወዴት ነው የምንሄደው?
ሞት፡ እኛ? እውነቱን ንገረኝ ካልክ አንተ እጥፍጥፍ ብለህ ወለሉ ላይ ነው የምትዘረረው፡፡
ናት፡  ኦ፣ እስኪደርስ በጣም ቸኮልኩኝ፡፡ ህመም ይኖረው ይሆን?
ሞት፡  ኧረ አፍታም አይቆይ፡፡
ናት፡   በጣም ደስ ይላል፡፡ (በእፎይታ ይተነፍሳል)
ሞት፡  በተሰቀለው፤ ስድስት የሳብክ መስሎኝ?
ናት፡ አይ፤ በል ሂድ፡፡ እና ወለሉ ላይ ነው የምሞተው ማለት ነው? ሶፋው ላይስ አልችልም?
ሞት፡  አይቻልም፡፡ ይልቅእየተጫወትክ….
ናት፡  ለምንድን ነው የማይቻለው?
ሞት፡  ምክንያቱም ወለሉ ላይ ነው የተፈቀደው! እስቲ አሁን ተወኝ፡፡ ጨዋታው ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ፡፡
ናት፡   የግድ ወለሉ ላይ መሆን አለበት? ይሄንን ብቻ ነው የምጠይቅህ! ሶፋው ላይ ብሆን ምን ችግር አለው?
ሞት፡  ባክህ ቀጥል…
ናት፡ የጠየቅኩህ ይሄን ብቻ ነው፡፡ ሞ ሌፍኮዊትዝን (ኮሜዲያን) አስታወስከኝ፡፡ እሱም እንዳንተ ግትር ነበር፡፡ …ቅድም ግን በመጀመሪያ ሥራዬ ምናምን ስትል ምን ማለትህ ነበር?
ሞት፡   ምን ማለቴ ይመስልሃል?
ናት፡    ማንም ሰው ከዚህ በፊት ሄዶ አያውቅም ማለት ነው?
ሞት፡ ብዙ ሰው ሄዷል እንጂ፡፡ ግን እኔ አይደለሁም የወሰድኳቸው፡፡
ናት፡   እና ማን ነው?
ሞት፡  ሌሎች!
ናት፡   ሌሎችም አሉ እንዴ?
ሞት፡  ታዲያስ! እያንዳንዱ ሰው የሚሄድበት የራሱ የሆነ ሞት አለው፡፡
ናት፡   አላውቅም ነበር፡፡
ሞት፡ እንዴት ልታውቅ ትችላለህ? አንተ ማነህና ነው?
ናት፡   እንዴት ማነህ ትለኛለህ? እኔ…ምንም ነኝ እንዴ?
ሞት፡  ምንምማ አይደለህም፡፡ ቀሚስ አምራች ነህ፡፡ ስለ ዘላለማዊነት ምስጢራት ግን የት ታውቅና?
ናት፡   ምን እያልክ ነው? ጥሩ ገቢ አለኝ፡፡ ሁለት ልጆቼ ኮሌጅ በጥሰዋል፡፡ አንዱ ማስታወቂያ ሠራተኛ ነው፤ ሌላኛው ትዳር ይዟል፡፡ የራሴ ቤት አለኝ፡፡ ውሃ የመሰለች መኪና እነዳለሁ፡፡ ለሚስቴ የፈለገችውን ሁሉ አደርግላታለሁ፡፡ ደንገጡሮች፣ ውድ ልብሶች፣ ሽርሽር፡፡ አሁን ራሱ መዝናኛ ቦታ ነው ያለችው፡፡ በቀን ሃምሳ ዶላር ነው የሚከፈልበት፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት እኔም እሄዳለሁ…እና ምን ይመስልሃል…ማንም ተራ ሰው ነኝ?
ሞት፡   እሺ በቃ፡፡ ብዙ አይሰማህ!
ናት፡   ተሰማኝ አልኩህ?
ሞት፡  ቆይ እኔም ልክ እንዳንተ ቱግ ብል ምን ትላለህ?
ናት፡   እኔ ሰድቤሃለሁ እንዴ?
ሞት፡   እንዲህ ሆነህ ትመጣለህ ብዬ አልጠበኩም ነበር አላልከኝም?
ናት፡  ምን ጠብቀህ ነበር? ድግስ ደግሼ፣ በሆታና በእልልታ እንድቀበልህ?
ሞት፡ እንደዛ አይደለም፡፡ እኔን…አጭር ነህ፤ እንዲህ ነህ፤ እንዲያ ነህ…ያልከውን ማለቴ ነው፡፡
ናት፡  እኔን ትመስላለህ ነው ያልኩት፡፡ ራሴን በመስታወት እንደማየት እኮ ነው፡፡
ሞት፡ እሺ በቃ ይሁን፡፡
(ጨዋታቸውን ሲቀጥሉ ሙዚቃው እየጨመረና ብርሃኑ እየደበዘዘ መጥቶ ጨለማ ይሆናል፡፡ ቆይቶ መብራቱ ቀስ እያለ ይበራና ጨዋታው አልቆ ይታያሉ፡፡ ናት ውጤት ይቆጥራል፡፡)
ናት፡ ስድሳ ስምንት…ለአንድ መቶ ሃምሳ…በቃ፤ ተሸንፈሃል!
ሞት፡  (ካርታዎቹን በድብርት እየተመለከተ) ያቺን ዘጠኝ ቁጥር መጣል አልነበረብኝም፡፡ እናቷን!
ናት፡  በቃ ነገ እንገናኝ፡፡
ሞት፡ ነገ እንገናኝ ስትል ምን ማለትህ ነው?
ናት፡ አሸነፍኩህኮ …አንድ ተጨማሪ ቀን አገኘሁ ማለት ነው፡፡ አሁን ተነስተህ ሂድ፡፡
ሞት፡ የምርህን ነበር እንዴ?
ናት፡  ተስማምተን እኮ ነው የተጫወትነው?
ሞት፡ አዎ፤ ግን….
ናት፡ ግን… አትበለኝ ባክህ፡፡ ለሃያ አራት ሰዓት አሸንፌሃለሁ፡፡ ነገ ጠዋት ተመልሰህ ና!
ሞት፡  የምር ግን ለዚህ እየተጫወትን እንደነበር አላወቅሁም፡፡
ናት፡   በጣም ያሳዝናል፤ ልብ ብለህ ማዳመጥ ነበረብህ፡፡
ሞት፡  እና ለሃያ አራት ሰዓታት የት ልሄድ ነው?
ናት፡  የፈለግህበት! ዋናው ጉዳይ እኔ ተጨማሪ ሃያ አራት ሰዓት ማግኘቴ ነው፡፡
ሞት፡ መንገድ ለመንገድ ልንገላወድ ነው?
ናት፡  አልቤርጐ ተከራይ፤ ፊልም ወይም ሳውና ግባ…ነገሩን አታካብደው ባክህ!
ሞት፡ ውጤቱ ከእንደገና ይቆጠር፡፡
ናት፡  ደሞ ሃያ ስምንት ዶላር አለብህ፡፡
ሞት፡ ምን?
ናት፡  ሃያ ስምንት ዶላር! ይሄው የተፃፈውን …አንብበው፡፡
ሞት፡ (ኪሱን እየበረበረ) የተወሰነ ነገር አለኝ…ሃያ ስምንት ግን አይሞላም፡፡
ናት፡ ቼክም እቀበላለሁ፡፡
ሞት፡ ከየትኛው አካውንቴ?
ናት፡ ኧረ እዩልኝ… ከማን ጋር እንደምደራደር…?
ሞት፡ ብትፈልግ ክሰሰኝ፡፡ ቼክ የሚያስጽፍ አካውንት የት አለኝና?
ናት፡ እሺ፤ ያለህን ስጠኝ፤ ይበቃኛል፡፡
ሞት፡ ይሄንማ እፈልገዋለሁ፡፡
ናት፡  ምን ያደርግልሃል?
ሞት፡ ምንድን ነው የምታወራው፡፡ ወደማይቀርበት ልትሄድ አይደል እንዴ?
ናት፡ እና?
ሞት፡ ምን ያህል ሩቅ እንደሆነ አታውቅም?
ናት፡ እና ቢርቅስ?
ሞት፡ ለነዳጅ ከየት ላመጣልህ ነው? ድልድዩን ለመሻገር የሚከፈለው ገንዘብስ?
ናት፡  በመኪና ነው እንዴ የምንሄደው?
ሞት፡ እሱን ሲደርስ ታየዋለህ! ስማ ነገ ተመልሼ ስመጣ ይሄን ገንዘብ የማሸንፍበት ዕድል ትሰጠኛለህ። ካልሆነ ግን ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የምገባው፡፡
ናት፡   የፈለግኸውን ያህል ጊዜ እንጫወታለን። ለቀጣዩ አንድ ሳምንት ወይም ወር ብንጫወትም ማሸነፌ አይቀርም፡፡ እንዳንተ አያያዝማ ለአመታት ጭምር አሸንፍሃለሁ፡፡
ሞት፡  አሁን ግን መድረሻ ቢስ ሆኜልሃለሁ፡፡
ናት፡  በቃ ነገ እንገናኝ፡፡
ሞት፡ (ወደ በሩ እያመራ) ጥሩ ሆቴል ያለው የት ነው? የምን ሆቴል ነው የማወራው?…ለካ ምንም ገንዘብ የለኝም፡፡ በቃ የሆነ ምግብ ቤት ውስጥ ቁጭ እላለሁ፡፡ (ጋዜጣውን አነሳ)
ናት፡  ውጣ! ውጣ! ጋዜጣዬን ደግሞ ቁጭ! (ጋዜጣውን ቀማው)    
ሞት፡ (እየወጣ ያጉተመትማል) መቼም ዝም ብዬ ልወስደው አልችልም ነበር፡፡ የግድ ካርታ መጫወት ነበረብኝ፡፡
ናት፡ (ጮክ ብሎ) ደረጃውን ስትወርድ ደግሞ ጠንቀቅ በል…ምንጣፉ እንዳያደናቅፍህ፡፡
(ከፍተኛ የመጋጨት ድምፅ ይሰማል፡፡ ናት በእፎይታ ይተነፍስና አልጋው አጠገብ ያለችውን ጠረጴዛ ተሻግሮ ስልክ ይደውላል፡፡)
ናት፡  ሄሎ፤ ሞ? እኔ ነኝ፡፡ ስማኝማ፤ የሆነ ሰው ሲፎግረኝ ይሁን ምን አላወቅሁም፤ ብቻ ሞት አሁን እዚህ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ትንሽ ካርታ ተጫወተ…አይደለም አይደለም፤ ሞት ነው ያልኩህ። ራሱ በአካል፡፡ ወይም ደግሞ ራሱን ሞት ነኝ ብሎ የሚጠራ ሰው፡፡ የሚገርመው ግን ሞ፤ እንዴት ያለ ደደብ መሠለህ!
(መጋረጃው ይወርዳል)

Read 4184 times