Print this page
Saturday, 31 May 2014 14:29

ነፍሰጡሯ ፍ/ቤት በራፍ ላይ ቤተሰቦቿ በድንጋይ ገደሏት

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ፋርዛና በአደባባይ ለ40 ደቂቃ በቤተሰቦቿ ስትደበደብ ፖሊስ በዝምታ አይቷል
ያለኔ ፈቃድ ባል በማግባት ስላዋረደችኝ ገደልና፤ አይፀፅተኝም - አባት
ፋርዛናን ለማግባት ብዬ ነው የመጀመሪያ ሚስቴን አንቄ የገደልኳት - ባል
የመጀመሪያ ሚስቱን ገድሎ ያልታሰረው ልጆቹ ይቅርታ ስላደረጉለት ነው - ፓሊስ

ባለፈው ማክሰኞ በፓኪስታን ላሆር ከተማ የተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ ከቀን ወደ ቀን እየተወሳሰበ ነው፡፡ አጀማመሩ ግን እንዲህ ነው፡፡ “በፍቅር ግንኙነት ከአመት በላይ አሳልፈናል” በማለት የተናገሩት ፋርዛና ፓርቪን እና ኢቅባል መሐመድ፤ ተጋብተው አብረው ለመኖር ከወሰኑ ቆይተዋል፡፡ የፋርዛና ቤተሰብ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ፓርዛና የ25 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ኢቀባል በእድሜ ይበልጣታል፤ ልጆችንም ወልዷል፡፡ ለፋርዛና ቤተሰብ ግን፤ ይሄ አላስጨነቃቸውም፡፡ ኢቅባል 1000 ዶላር ጥሎሽ አልከፍልም በማለቱ የተቆጡ የፋርዛና ቤተሰቦች፤ ለሌላ ባል ሊድሯት ተነጋግረው ጨርሰዋል፡፡ በዚህ መሃል ነው ባለፈው ጥር ወር ፋርዛና ያለ ቤተሰቧ ፈቃድ ከኢቅባል ጋር ተጋብታ የሄደችው፡፡ ቤተሰቦቿ ደግሞ ኢቅባልን ከሰሱት-“ልጃችንን ጠልፎ ወስዷል” በሚል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ እለት ፋርዛና ከኢቅባል ጋር ወደ ፍ/ቤት የመጣችው፣ “እኔ አልተጠለፍኩም” የሚል ምስክርነት ለመስጠት ነው፡፡ ኢቅባልን የከሰሱት ቤሰቦቿ… አባቷ፣ ወንድሞቿ፣ የአክስትና የአጐት ልጆች ሁሉ ተሰብስበዋል፡፡ ሃያ ይሆናሉ፡፡ ከፍርድ ቤት ስትወጣ ጠብቀው፤ ጠልፈው ሊወስዷት ቢሞክሩም እሺ አላለችም፡፡ ያኔ ነው ዙሪያዋን በመክበብ የድንጋይ መዓት ያወረዱባት - በአባቷ መሪነት፡፡
ባለቤቷ ኢቅባል እንደሚለው፤ ከፍ/ቤቱ በራፍ ላይ አደባባይ መሃል በጠራራ ፀሐይ በድንጋይ ሲወግሯት አላፊ አግዳሚ ሁሉ ከሩቅ ሆኖ ከመመልከት በስተቀር ለመገላገል የሞከረ ሰው የለም፡፡ ፖሊሶችም ነበሩ፡፡ የሦስት ወር እርጉዝ የነበረችው ፋርዛና ቶሎ አልሞተችም፡፡ ለ40 ደቂቃ በቤተሰቦቿ የድንጋይ ውርጅብኝ እንደተደበደበች የገለፀው ቢቢሲ፤ ይህንን የግድያ ጥቃት ለማስቆም ፖሊስ እንዳልሞከረ ዘግቧል፡፡ ፋርዛና በአሰቃቂ ስቃይ ህይወቷ ካለፈ በኋላ የታሰሩት አባቷ፤ ያለፈቃዳችን በማግባቷ አዋርዳናለች፤ ለክብራችን ስንል ገድለናታል፤ የሚፀፅተኝ ነገር የለም ብለዋል፡፡ በግድያው የተሳተፉ ወንድሞቿና ዘመዶቿ አልታሰሩም፡፡ ግን እነሱም በግድያው አልተፀፀቱም፡፡
እንዲያውም፤ ካሁን ቀደም ተመሳሳይ ግድያ እንደፈፀሙ ከመናገር ወደኋላ አላሉም፡፡ የዛሬ አራት አመት በተመሳሳይ የጋብቻ ውዝግብ ሰበብ ታላቅ እህቷን መግደላቸው በሲኤንኤን ተዘግቧል፡፡ ለነገሩ በፓኪስታን እንዲህ በቤተሰብ የሚፈፀም ግድያ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የፓኪስታን ምድር፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተወካይ ዛህራ ዮሱፍ እንደሚሉት በየአመቱ አንድ ሺ ገደማ ሴቶች ያለ ቤተሰብ ፈቃድ አግብተዋል ተብለው ይገደላሉ፡፡
ዘግናኙ የግድያ ታሪክ በዚህ አልተቋጨም፡፡ የፋርዛና ባለቤት ኢቅባል ንፁሕ ሆኖ አታገኘም፡፡ ለካ፣ የዛሬ ስድስት አመት የመጀመሪያ ሚስቱን ገድሏል፡፡ ከፋርዛና ጋር ለመጋባት በማሰብ ነው የመጀመሪያ ሚስቴን አንቄ የገደልኳት ብሏል - ኢቅባል፡፡ አስገራሚው ነገር ከአንድ አመት በላይ አልታሰረም፡፡ ከመነሻውም በፖሊስ የታሰረው፤ “እናታችንን ገደላት” በማለት ልጆቹ በመመስከራቸው ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ፤ ልጆቹ “ይቅርታ አድርገንለታል” ብለው ስለተናገሩ ከእስር መለቀቁን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ የሴት ህይወት የረከሰባት ፓኪስታን፤ የቅዠት አገር አትመስልም?

Read 8107 times
Administrator

Latest from Administrator