Saturday, 31 May 2014 14:29

ሳይንቲስት ስቴፈን ሃውኪንግ፣ የአለም ዋንጫ “ፎርሙላ” ሰጠ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሃውኪንግ ለቀመሩ ክፍያ ተቀብሏል - ፓዲ ፓወር ከተሰኘው የቁማር ኩባንያ

      ከዩኒቨርስ አፈጣጠር እስከ አቶሞች ባሕርይ፣ በበርካታ የምልዐተ ዓለሙ ሚስጥራት ላይ የሚመራመር ታዋቂው የፊዚክስ ጥበበኛ ስቴፈን ሃውኪንግ፤ ሰሞኑን በእግር ኳስ ዙሪያ የምርምር ግኝቶቹን አቅርቧል።
በዘንድሮው የአለም ዋንጫ የእንግሊዝ ቡድን እንዴት ውጤታማ ሊሀን እንደሚችል ምክር የለገሰ ሲሆን፣ የ50 ዓመታት መረጃዎችን በመተንተን ለአሸናፊነት የሚያበቃ ቀመር (ፎርሙላ) አዘጋጅቷል። የተጫዋቾች አሰላለፍና የማሊያ ቀለም፣ የውድድር ሰዓትና የሙቀት መጠን፣ የፍፁም ቅጣት አመታትና የዳኞች ማንነት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ተለዋዋጭ (variable) ነገሮችን ያካትታል - ቀመሩ።
በእርግጥ፤ የሃውኪንግ ቀመር ለሂሳብ ጠበብት እንጂ ለአብዛኛው ሰው ሊገባ የሚችል አይደለም። እንዲያውም፣ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስብባቸዋል። ግን ችግር የለም። ስቴፈን ሃውኪንግ፣ ውስብስቡን ቀመር፣ በቀላል ቋንቋ ለማስረዳት ሞክሯል። ለምሳሌ፣ ለእንግሊዞች የሚስማማቸው መካከለኛ የሙቀት መጠን እንደሆነ ሳይንቲስቱ ጠቅሶ፤ የሙቀት መጠን በ5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲጨምር የቡድኑ ውጤታማነት በ59% ይቀንሳል ብሏል። በዚያ ላይ፣ እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከፍታ ቦታ ላይ የእንግሊዝ ቡድን ማሸነፍ አይሆንለትም። የቦታው ከፍታ ከ500 ሜትር በታች ከሆነ ግን፤ የማሸነፍ እድሉ በእጥፍ ይጨምራል። ጨዋታው የሚጀመረው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከሆነም፣ ቡድኑ ይቀናዋል።
ምን ዋጋ አለው? የሙቀት መጠን፣ የአካባቢው ከፍታና የውድድር ሰዓት፣ በምርጫ የሚወሰኑ ነገሮች አይደሉም። ነገር ግን የእንግሊዝ ቡድን የተጨዋቾቹን አሰላለፍና የማሊያውን ቀለም በትክክል ከመረጠ፣ የማሸነፍ እድሉን ማሻሻል እንደሚችል የሃውኪንግ ቀመር ያስረዳል። 4-4-2 አሰላለፍ ለእንግሊዝ እንደማይበጅ የገለፀው ሃውኪንግ፣ ቡድኑ ስኬታማ የሚሆነው በ4-3-3 አሰላለፍ እንደሆነና ቀይ ማሊያ መልበስ እንዳለበት ተናግሯል። ቀይ ማሊያ፤ በተቀናቃኝ ቡድን ላይ የስነልቦና ተፅእኖ ያሳድራል፤ እናም የእንግሊዝ ቡድን የአሸናፊነት እድሉን በ20% ያሻሽላል።
ሃውኪንግ እንደሚለው፤ ውድድሩ የሚካሄደው ቅርብ በሆነ አገር ቢሆን መልካም ነበር፤ ብራዚል ድረስ አትላንቲክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ የሚደረገው በረራ፣ በተጫዋቾች ላይ ድካምን ይፈጥራል፤ የማሸነፍ እድላቸውንም በ22 በመቶ ይቀንሳል። ዳኞቹ አውሮፓውያን ሲሆኑ የእንግሊዝ ቡድን ይቀናዋል፤ አለበለዚያ ግን የማሸነፍ እድሉ በ25% ይወርዳል።
የቲፎዞና የአጃቢ ሴቶች ጉዳይስ? ይሄ በቡድኑ ውጤታማነት ላይ ምንም ለውጥ ስለማያመጣ በቀመሩ ውስጥ እንዳልተካተተ ሃውኪንግ ገልጿል።
ወደ ፍፁም ቅጣት የሚያመራ ውድድር ሲያጋጥምስ? የሃውኪንግ ምርምር፣ ሶስት ነባር ጉዳዮችን በድጋሚ ያረጋገጠ ሆኗል። አንደኛ፣ ፍጥነት ወሳኝ ነው። ፍፁም ቅጣት የሚመታ ተጫዋች፣ ቢያንስ ቢያንስ አራት እርምጃ መንደርደር አለበት።
ከዚህ ባነሰ እርምጃ ከተንደረደረ፣ ግብ የማስቆጠር እድሉ በግማሽ ይቀንሳል። ሁለተኛ፣ ከግራ ወይም ከቀኝ በኩል ከፍ አድርጎ መምታት ያስፈልጋል። 84 በመቶ ያህል ይሳካለታል። ኳሷን በደንብ ለመቆጣጠር በጎን እግር መምታት ነው። ሦስተኛ፣ ከተከላካይና ከመሃል ተጫዋቾች ይልቅ አጥቂዎች እንዲመቱ ማድረግ ያዋጣል ብሏል ሃውኪንግ።
ሳይንቲስቱ፣ ለእንግሊዞች ምክሩን ቢለግስም፣ ያሸንፋሉ የሚል ተስፋ የለውም። በቀመሩ መሰረት፣ ዋንጫውን የሚወስደው ብራዚል ነው። ግን የሳይንቲስቱ ምርምር ቀልጦ አይቀርም።
ከመነሻው፣ የፊዚክስ ባለሙያው ስቴፈን ሃውኪንግ፣ በእግር ኳስና በአለም ዋንጫ ላይ ጥናትና ምርምር ያካሄደው፣ ለእንግሊዝ ቡድን የማሸነፊያ ቀመር ለመፍጠር አይደለም። የሃውኪንግ ቀመር ለማንኛውም ቡድን ይሰራል። ያንን ቀመር የሚያሟላ ቡድን ያሸንፋል። ቀመሩን በእጅጉ ተፈላጊ የሚሆነው ግን፣ ሜዳ ውስጥ ገብተው በአለም ዋንጫው ለሚሳተፉ ቡድኖች አይደለም። ከዳር ሆነው ቁማር ለሚያጫውቱ ኩባንያዎች እንጂ። ስቴፈን ሃውኪንግም ቀመሩን ያዘጋጀው፣ ፓዲ ፓወር ለተሰኘ የቁማር ኩባንያ ነው - በክፍያ። እውነትም፣ የቁማር ኩባንያ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው፣ በአንዳች የቀመር ስሌት የትኞቹ ቡድኖች ምን ያህል የማሸነፍ እድል እንዳላቸው የሚያውቅ ከሆነ ነው። አለበለዚያ ከፍተኛ ኪሳራ ሊደርስበት ይችላል። እናም፤ የሃውኪንግ ቀመር፣ የጊዜ ማሳለፊያ ጨዋታ አይደለም፤ የቢዝነስ መሳሪያ ነው።

Read 7842 times