Saturday, 31 May 2014 14:22

የ2014 ዳይመንድ ሊግ በዩጂን አሜሪካ ይቀጥላል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

          የ2014 ዳይመንድ ሊግ ትናንት በ3ኛዋ ከተማ በአሜሪካ ዩጂን፤ በፕሮፎንታይኔ ክላሲክስ ውድድር የቀጠለ ሲሆን ዛሬ የሚካሄዱት የወንዶች 800 ሜትር፤ 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ትኩረት ስበዋል። ዘንድሮ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዳይመንድ ሊጉ በውድድሩ ዘመኑ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት መሆኑን የተለያዩ መረጀዎች ገልፀዋል፡፡ የዳይመንድ ሊጉ የመክፈቻ ውድድር ከ2 ሳምንት በፊት በኳታር ዶሃ የነበረ ሲሆን በዚሁ ጊዜ በ800 ሜትር አሸንፎ ሙሉ ነጥብ ያስመዘገበው ኢትዮጵያዊው መሃመድ አማን ነበር፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት ደግሞ ሁለተኛው ውድድር በቻይናዋ ከተማ ሻንጋይ ሲካሄድ የኔው አላምረው በ5ሺ ሜትር ድል በማድረግ መሪነቱን ይዟል፡፡
ፕሮፎንታይኔ ክላሲክስ  ትናንት  በሴቶች ረጅም ዝላይ፤  800 ሜትር፤ ዲስከስ ውርወራ እና በወንዶች አሎሎ ውርወራ የተጀመረ ሲሆን  በዛሬው እለት ከሚካሄዱ 14 ውድድሮች መካከል ደግሞ የወንዶች 10ሺ ሜትር፤ በሴቶች 3ሺ መሰናክል እና 1500 ሜትር፤ የወንዶች 5ሺ ሜትር እና 800 ሜትር ውድድሮች ይገኙበታል፡፡
በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በተለይ የ1500 ሜትር፣ የ800 ሜትር እንዲሁም የሌሎች የአጭር ርቀት ውድድሮች የዓለም ሪከርዶች የመስበር ዕድል አላቸው ተብሏል፡፡ ዛሬ በሚደረገው በወንዶች 800 ሜትር ለ1 ዓመት በጉዳት የቆየው ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ መሳተፉ ከባድ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በዚሁ ውድድር ከኢትዮጵያዊው መሃመድ አማን፤ ከቦትስዋናው ኒጄል  አሞስ ከእንግሊዙ አንድሪው ኦሳጄ እና ከአሜሪካው ድዋኔ ሶሎሞን ጋር በሚደረግ ፉክክር ሪከርድ ሊሰበር ይችላል ተብሏል፡፡ በኬንያዊው አትሌት ዴቪድ ሩዲሻ  ከ2 ዓመት በፊት በለንደን ኦሎምፒክ የተመዘገበው የ800 ሜትር የዓለም ሪኮርድ 1 ደቂቃ ከ41.54 ሰኮንዶች ነው፡፡የ20 ዓመቱ መሃመድ አማን እና የ25 አመቱ ዴቪድ ሩዲሻ ከ2010 ጀምሮ በ7 ውድድሮች ተገናኝተው አምስቱን ያሸነፈው ሩዲሻ ሲሆን ሁለት ጊዜ መሃመድ አማን ቀድሞታል፡፡
በሴቶች 1500 ሜትር የመጀመርያ ውድድሯን ሻንጋይ ላይ ያሸነፈችው የስዊድኗ አበባ አረጋዊ ለሁለተኛው ድል የምትሰልፍ ሲሆን አትሌት ገንዘቤዲባባ ስለሚኖራት ተሳትፎ ግልፅ መረጃ ባይገኝም ሌላዋ የ19 ዓመት ኢትዮጵያዊት አክሱማይት አምባዬ ትወዳደራለች፡፡ በ5000 ሜትር ወንዶች የመጀመርያ ውድድሩን ከሁለት ሳምንት በፊት በሻንጋይ ያሸነፈው ኢትዮጵያዊው የኔው አላምረው 24ኛ ዓመት ልደቱን በማክበር ሲሳተፍ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሃጎስ ገብረህይወት ጨምሮ አሜሪካዊው በርናንድ ላጋት እና ሞ ፋራህ በክብር ተጋባዥነት ይፎካከራሉ፡፡
 ባለፉት 4 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት ከ18 አገራት የተውጣጡ አትሌቶች በየውድድር መደባቸው የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ በአንደኛነት በመጨረስ የዳይመንድ ዋንጫዎች እና የ43ሺ ዶላር ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በ4 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት 30 አሸናፊዎች በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ ያላት አሜሪካ ስትሆን፤ ኬንያ 21፤ ጃማይካ 10 እንዲሁም ኢትዮጵያ 7 ተሸላሚዎችን በማግኘት ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ በ5ሺ ሜትር ዳይመንድ ሊጉን ለሁለት ጊዜያት ያሸነፈው ኢማና መርጋ በ2010 እና በ2011 እኤአ ሲሆን በ2013 እኤአ ደግሞ የኔው አላምረው ተሸላሚ ነበር፡፡ በወንዶች 800 ሜትር ደግሞ አትሌት መሃመድ አማን  በ2012 እና በ2013 እኤአ ዳይመንድ ሊጉን አሸንፏል። በሴቶች 1500 ሜትር አበባ አረጋዊ በ2012 እኤአ በኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲሁም በ2013 እኤአ በስዊድናዊ ዜግነት የዳይመንድ ሊግ ተሸላሚ የነበረች ሲሆን መሰረት ደፋር በ5ሺ ሜትር  በ2013 እኤአ ያሸነፈች ሌላዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ናት፡፡

Read 3610 times