Saturday, 31 May 2014 14:20

የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድርን የባህርዳር ስታድዬም ያስተናግዳል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በ2007 ‹‹ሱፕርናሽናል ሊግ›› ይጀመራል
በ2007 ወደ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያድጉ ሁለት ክለቦችን የሚለየው የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድርን የባህር ዳር ስታድዬም እንደሚያስተናግድ ታወቀ፡፡
ስታድዬሙ ውድድሩን እንዲያስተናግድ የተመረጠው ባለው ዓለም አቀፍ የብቃት ደረጃ የተሻለ ፉክክር ይስተናገድበታል በሚል ግምት ሲሆን በየክልሉ የሚገኙ አዳዲስ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን  መጠቀም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት ነው፡፡ የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር 16 ክለቦችን ያሳትፋል፡፡ በ2006 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ 69 ክለቦች በሰባት ምድቦች ተከፍለው ሲፎካከሩ ቆይተዋል፡፡ ከብሄራዊ ሊጉ 7 ምድቦች  አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኙት 14 ክለቦች እና ሁለት ምርጥ ሶስተኛ ቡድኖች  በባህርዳር ስታድዬም ለሚካሄደው የ16 ክለቦች ማጠቃለያ ውድድር የሚያልፉ ይሆናል፡፡ ውድድሩ ተቀራራቢ ነጥብ በያዙ ክለቦች ጠንካራ ፉክክር ሲታይበት ቆይቷል፡፡  
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በተለያዩ ዞኖች ተካፋፍሎ በሚደረገው የብሄራዊ ሊግ እና የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር መካከል ሱፕር ናሽናል ሊግ የሚባል አዲስ ውድድር ሊካሄድ ታቅዷል፡፡ ሱፕር ናሽናል ሊጉ 16 ክለቦችን በማሳተፍ ዓመቱን ሙሉ በዙር ውድድር ተካሂዶ ወደ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያልፉ ሁለት ክለቦች የሚወሰኑበት ይሆናል። ለብሄራዊ ቡድን የሚሆኑ ተጨዋቾችን ለመመልመል ሱፕር ናሽናል  ሊጉ  አመቺ መድረክ መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም  ወደ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያልፉ ክለቦችን ከአድካሚ ውድድሮች በኋላ  ከመለየት ከ16 ቡድኖች ምርጡን ማግኘት የሚሻል በመሆኑ ነው

Read 1642 times