Print this page
Saturday, 31 May 2014 14:12

የኢትዮጵያ የቡና ምርትና ግብይት ዘመናዊ አይደለም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

         ኢትዮጵያ የቡና ምርት ሂደትና ግብይት ስርአትን ዘመናዊ ባለማድረጓ፣ ከአለማቀፍ ገበያ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ከትናንት በስቲያ በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልኡክ ጽ/ቤት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ደሳለኝ ሆቴል በተከናወነው የ1ቀን ሴሚናር ላይ፣ የቡና ላኪዎችና አምራቾችን ጨምሮ በቡና ላይ የሚሰሩ አለማቀፍ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ የቡና ምርትና ግብይት ስርአት ላይ ጥናት ያደረጉት ገንተር ሄላወስ የተባሉ ኤክስፐርት፤ ሃገሪቱ በቡና ምርት ግብይት እያጋጠሟት ያሉትን ተግዳሮቶች ከጠቆሙ በኋላ፣ በአለማቀፍ ደረጃ በዘርፉ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል በርካታ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል፡፡
ጥናት አቅራቢው፤ በኢትዮጵያ የቡና አመራረት ስርአት ዘመናዊነት እንደሚጎድለው ማስረጃዎችን ያቀረቡ ሲሆን ምርታማነትን በሚያሳድጉ ምርምሮች እምብዛም የማይታገዝ መሆኑ፣ የቡና ችግኞችን በተገቢው መንገድ ከበሽታ መከላከል አለመቻሉ፣ በአምራቹ እና በምርምር ማዕከላት መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ አለመሆኑ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ ስርአቱ ደካማ መሆኑ ለምርታማነቱ አለመዳበር አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡
ከግብይት አንፃር ክፍተቶች ተብለው በጥናት አቅራቢው ከተጠቆሙት መካከልም፤ ግልፅነት የሌለው የተወሳሰበ የንግድ ሰንሰለት መኖር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተደራሽነት አለመኖር፣ ደካማ የጥራት መመዘኛ በስራ ላይ መዋሉ፣ ትክክለኛ የገበያ መረጃ አለመኖር የሚሉ እና ተለዋዋጭ ህግና መመሪያዎች በየጊዜው መውጣታቸው… ተግዳሮት ሆነዋል ተብሏል፡፡  በቀጣይ ቢተገበሩ ለሃገሪቱ የቡና ምርታማነትና የገበያ ተደራሽነት አጋዥ ናቸው ተብለው በኤክስፐርቱ ከተጠቆሙት መካከልም፤ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የአረቢካ ቡና ምርታማነት ማሳደግና የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር እንዲሁም ሰፊ የማስተዋወቅ ስትራቴጂ መንደፍ የሚሉት ይገኙበታል፡፡  

Read 2316 times