Saturday, 31 May 2014 14:05

የህዋ ዓለም ህይወት አስገራሚ እውነታዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(21 votes)

በኅዋ ላይ ጠፈርተኞች የሚገጥሟቸው ህመሞች
ወደ ኅዋ ከሚጓዙ መቶ ጠፈርተኞች መካከል 45ቱ በህመም ወይም በበሽታ ምልክቶች ይሰቃያሉ። እነዚህ ምልክቶች የማስመለስ፣ የራስ ምታት ወይም ማንኛውንም ነገር ለመስራትም ሆነ ለመደሰት ከመጠን ያለፈ አቅም ወይም ኃይል ማጣት (ሌተርጂ) ሊሆን ይችላል፡፡ ደግነቱ ግን ምልክቶቹ ከጥቂት ሰዓት በላይ አይቆዩም፡፡
እንባና ኅዋ
ኅዋ ወይም ጠፈር ላይ ያለ ሰው እጅግ መሪር ኀዘን ቢሰማው እንኳ ማዘን እንጂ እንባ አውጥቶ ማልቀስ አይችልም፡፡ ለምን ይመስልዎታል? መልሱን ፅሁፉ ሲጠናቀቅ ያገኙታል፡፡
ኅዋና ቁመት
በጀርባ በአጥንት ወይም አከርካሪ መካከል የሚገኙ ዲስኮችን፣ የስበት ኃይል (ግራቪቲ) ብዙ ጊዜ ወደታች ስለሚስባቸው መጠነኛ መጠጋጋት ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ጠፈርተኞች የሚኖሩትና የሚሰሩት ስበት በሌለበት ዜሮ ግራቪቲ አካባቢ ስለሆነ፣ በአከርካሪ አጥንታቸው መካከል የሚገኙት ዲስኮች መጠነኛ መስፋፋት ያደርጋሉ፡፡ ይህም ሁኔታ አከርካሪን ስለሚያስረዝም ጠፈርተኞቹ ቁመት እንዲጨምሩ ያደርጋል፡፡ የሚጨመረው ቁመት ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም 3 በመቶ የተለመደ ነው፡፡ ሰውየው ወይም ሴቲቱ በነበራቸው ቁመት ላይ ከ5-8 ሳ.ሜ ይጨምራሉ፡፡ ይህ ርዝመት ግን ቋሚ አይደለም፡፡ ጠፈርተኞቹ ወደ ምድር ሲመለሱ ግራቪቲ ስለሚጠብቃቸው ወደ ቀድሞ ቁመታቸው ይመለሳሉ፡፡
ሰዎች ስበት በሌለበት ዜሮ ግራቪቲ አካባቢ ሲቆዩ፣ ሌሎች የሚፈጠሩ አካላዊ ለውጦችም አሉ። እነሱም:- የአጥንት ክብደት መቀነስ፣ የጡንቻ መድከም (ቀደም ሲል መሸከም ይችል የነበረውን ክብደት ያህል ያለመቻል) የሰውነት ፈሳሽ ክፍፍል መለወጥና የልብ አሰራር (የካርዲዮቫስኩላር ሲስተም) ከተለመደው ውጭ መሆን ናቸው፡፡
ፀሐይ
ፀሐይ፤ በሚልኪ ዌይ (milky way) ውስጥ ከሚገኙ 200 ቢሊዮን ያህል ኮከቦች አንዷ ናት። እያንዳንዱ ኮከብ በአማካይ 16 መሬት መሰል ፕላኔቶች እንዳሏቸው ይገመታል፡፡
ንቦች ሁሉ ከምድረ ገጽ ቢጠፉ በሕይወት መኖር እንችላለን?  
እንዴታ! እኛ ሰዎች ንቦች ደግሞ በራሪ ነፍሳት፡፡ ምን አገናኘን? ዘር ማንዘራቸው ጥርግ ብሎ ቢጠፋ እንኳ እኛ እንኖራለን ይሉ ይሆናል፡፡ በእርግጥ እንኖራለን፡፡ ነገር ግን እንደተባለው ቀላል አይሆንም። ንቦች ትዝ የሚሉን ጣፋጭ የሆነውን ማራቸውን፣ ስንበላ ወይም በመድኃኒትነት ስንጠቀም አይደለም፡፡ ሲነድፉንና ኃይለኛ ህመሙ ሲሰማን ነው፡፡ ንቦች ግን ለበርካታ ዝርያዎች መኖር በጣም አስፈላጊ ናቸው። አንዳንድ ሰብሎችና ተክሎ ያለንቦች ዝርያቸውን አይተኩም፡፡
በምሳሌ እንይ፡፡ አየር ጤና አካባቢ ያለች ዘመዴ ግቢ ውስጥ አንድ የማንጎ ተክል ነበረች፡፡ ያቺ የማንጎ ተክል ወቅቷ ሲሆን በደንብ ታብባለች። ነገር ግን ፍሬ ወይም የሚበላ ማንጎ አታፈራም፡፡ ሶስት አራት ዓመት አይተው ምንም ቢያጡ “ሴቷ ናት አታፈራም” ብለው ነቅለው ጣሏት፡፡ ለምን መሰላችሁ ያላፈራችው? በሌላ አካባቢ ካለ ወንዴ የማንጎ ተክል አበባ ጣፋጭ ሲቀስም የተሸከመውን የወንድ ዘር ወደ ሴቷ የሚያደርስ (የሚያዳቅል) ንብ ስለጠፋ ነው፡፡
እንግዲህ ንቦች አዳቃይ (ፖሊኔተር) ናቸው ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሦስት ዝርያዎች የአንዱ አዳቃይ ንቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ ንቦች ከምድረ ገጽ ቢጠፉ በጣም የምንወዳቸው ፖምና ብሮኮሊን.. ጨምሮ ከ130 በላይ ፍራፍሬና አትክልቶች በፍጥነት የመጥፋት አደጋ ያንዣብብባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለመዳቀል፣ ንቦችን የማይፈልጉት እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ… እና ጥቂት ያህል እህሎች ብቻ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡
የንብ መንጋ ቁጥር በአስደንጋጭ ፍጥነት በመቀነስ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ሳይንቲስቶች ምክንያቱን ለማወቅ ትግል ይዘዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ገበሬዎች ንቦች እንደሚያደርጉት ለማዳቀል፣ የአንዱን ሰብል አትክልት ወይም ፍራፍሬ አበባ (የዘር ፍሬ) በእጅ በሌላው ላይ መነስነስ ጀምረዋል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ ወጪው በጣም ብዙና አድካሚ ነው፡፡ ዓለም ያላትን የንብ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ ብታጣ መኖራችን አይቀርም፡፡ ነገር ግን ዓለም አሁን ያሏትን ጣፋጭ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ይዛ አትቀጥልም። የተለያዩ ሰብሎች ይዛ እንደምንኖርባት ዓለም የምትጥም ምድር አትሆንም፡፡
መልስ - ግራቪቲ
ዋቢ - (Science Uncovered July 2014)  

Read 9818 times