Saturday, 31 May 2014 13:50

መንግሥት ያለ ሥራው ሲገባ የትም ሀገር ሃብት ይባክናል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የመንግስት ፕሮጀክቶችና የሃብት ብክነት
መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ ሲያቦካና ኢኮኖሚው ውስጥ ድርሻው እያበጠ ሲመጣ፤ የዚያኑ ያህል የሃብት ብክነትና ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም። ድሃ አገራት ውስጥ የሚፈጠረውን ብክነት ለመቁጠር መሞከር አስቸጋሪ ነው። ከብልፅግና ርቀው በድህነት የሚሰቃዩት ለምን ሆነና? ብዙ ሃብት ስለሚባክን ነው። መንግስት በገነነባቸው ድሃ አገራት ይቅርና፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ውስጥም የመንግስት ብክነት ቀላል አይደለም። አንዳንድ ምሳሌዎችን ልጥቀስ-  ከአገራችን የመንግስት ብክነት ጋር እያያዝኩ፡፡ ቀለል ባሉት ብክነቶች እንጀምር፡፡
ጣሊያን እና ኢትዮጵያ
የጣሊያን መንግስት ከተመሳሳይ የአውሮፓ አገራት የሚለይበት ነገር ቢኖር፤ በመኪና ግዢ የሚስተካከለው አለመኖሩ ነው። ተመሳሳይ የሕዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው አገራት ጋር ሲነፃፀር፤ የጣሊያን መንግስት በ10 እጥፍ የሚበልጡ መኪኖች እንዳሉት የዘገበው ዘ ኢኮኖሚስት፤ የመኪኖቹ ቁጥር 630ሺ ገደማ እንደሆነ ገልጿል። ከ10 ቢ. ዶላር በላይ ገንዘብ የባከነውና መኪኖች በገፍ የተገዙት በቂ ገንዘብ ስላለ አይደለም። ግን፤ መንግስት ገንዘብ መበደር ይችላል። የጣሊያን መንግስት እዳ፤ ከአመት አመት ሲከማች፣ አሁን 2.8 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል (2800 ቢሊዮን ዶላር!)። የመንግስትን የገንዘብ ብክነት እቀንሳለሁ በማለት ቃል የገቡት አዲሱ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለመነሻ ያህል 1500 የመንግስት የቅንጦት መኪኖችን ለመሸጥ ወስነዋል።
የኢትዮጵያ የሃብት ብክነት በጣም በጣም ይለያል። የተገዙ መኪኖች አገልግሎት ሳይሰጡ ይበላሻሉ፤ ሳይጠገኑ ይቆማሉ፡፡ ከትልልቅ የመንግስት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የውሃ ስራዎች ድርጅትን ማየት ይቻላል፡፡ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑትን ሳይቆጠሩ 900 ገደማ ትልልቅ የኮንስትራክሽን መኪኖችና ማሽኖች አሉት፡፡ ነገር ግን ግማሾቹ ያለ አገልግሎት ቆመዋል፡፡
አብዛኞቹ ግማሽ አመት ገደማ ጋራዥ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እናም የተለያዩ የግንባታ መኪኖችን ይከራያል፡፡ በአመት ለኪራይ ምን ያህል እንደሚያወጣ ታውቃላችሁ? አምና የድርጅቱ ጠቅላላ በጀት 1.8 ቢሊዮን ገደማ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ አምና ወደ 700 ሚሊዮን ብር የወጣው ለተሽከርካሪዎች ኪራይ ነው፡፡ በእያንዳንዷ ቀን 1.9 ሚ. ብር መሆኑ ነው፡፡
በየቀኑ አንድ ገልባጭ መኪና ለመግዛት የሚያስከፍል ገንዘብ ለኪራይ ይከፍላል፡፡ በመንግስት አማካኝነት ከቻይና ተገዝተው የመጡ በመቶ የሚቆጠሩ “ሃይገር ባሶች” ንም መመልከት ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ  በሁለት አመት እድሜ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡ በድሃ አገር አቅም የሃብት ብክነቱ ከአውሮፓም ይብሳል፡፡   
ፈረንሳይ እና ተንዳሆ
በፈረንሳይ መንግስት ትዕዛዝ የተሰሩ ባቡሮች፣ ሰሞኑን መወዛገቢያና መሳለቂያ ሆነው ሰንብተዋል። የባቡሮቹ ስራ የተጀመረው ከሶስት አመት በፊት ቢሆንም፤ የጎን ስፋታቸው ከብዙዎቹ የባቡር ፌርማታዎች እንደሚበልጥ የተወራው ሰሞኑን ነው። ዎልስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ከስምንት ሺ በላይ ፌርማታዎች መካከል፣ 1300 ያህሉ አዳዲሶቹን ባቡሮች ማሳለፍ አይችሉም። ሚኒስትሮችና የፓርላማ ፖለቲከኞች፣ የባቡር ድርጅት ባለስልጣናትና ቢሮክራቶች፣ አንዱ በሌላው ላይ ጣት እየቀሰሩ ቢወዛገቡም፣ መሳለቂያ ከመሆን አላመለጡም። ባቡሮቹን ደፍጥጦ ማሳነስ አይቻል ነገር! ፌርማታዎቹን ከጎንና ከጎን እየሸራረፉ ትንሽ ሰፋ ለማድረግ፣ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ይመደባል ተብሏል - 1.4 ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ነው።
በኤልፓ የተገዙ መአት ትራንስፎርመሮች፣ ምን ሆነው እንደተገኙ ታውቁ ይሆናል፡፡ በጣም ያረጁና በየእለቱ የሚበላሹ የሃብት ብክነት ሆነው አረፉት፡፡ በየከተማው የቄራ ድርጅት እንሰራለን ተብሎ ሲሞከርስ ምን ተፈጠረ? የቄራው የጣሪያ ከፍታ፣ ለከብት እርድ እንደማይበቃ የተረጋገጠው ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡
የአገሪቱን የስኳር ምርት ከሁለት እጥፍ በላይ ያሳድጋል ተብሎ ከ10 አመት በፊት የተጀመረውን የተንዳሆ እቅድ ብንተወው ይሻላል፡፡ ቢሊዮን ብሮች የፈሰሰበት ፕሮጀክት ምን ያህሉ ለብክነት እንደተዳረገ አስቡት፡፡
አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስላችሁ፡፡ ለብዙ አመታት ከተጓተተ በኋላ ለስኳር ፋብሪካው የሚውል የሸንኮራ አገዳ በ5ሺ ሄክታር  መሬት ላይ ተተከለ፡፡ ፋብሪካው ግን ገና ነው፡፡ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ ሸንኮራው ባከነ - የ100ሚ ብር ብክነት፡፡
እንግሊዝ፡
የአገሪቱ አቃቤ ሕጎች፣ የወረቀት መዛግብት ከሚሸከሙ፣ በዘመኑ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ተብሎ ነው 4600  ታብሌቶች (ጠፍጣፋ ሚኒኮምፒዩሮች) የተገዙት። ፍርድ ቤት ውስጥ ክርክር ሲያካሂዱም ሆነ ምስክሮችን ሲያፋጥጡ፣ ወረቀቶችንና ፋይሎችን መያዝ አያስፈልጋቸውም - ታብሌት ተሰጥቷቸዋል። አቃቤ ህጎቹ “ጥሩ ሃሳብ ነበር፤ ግን በታብሌቶቹ ክብደት እጃችን ዛለ” የሚል ቅሬታ ማሰማታቸውን የዘገበው ዋየርድ መፅሄት፤ የታብሌቶቹ ክብደት ወደ 2 ኪሎ ግራም ገደማ መሆኑን ገልጿል። እንደ ላባ የቀለሉ ታብሌቶችን ትቶ፣ እንደ ብረት የከበዱ ታብሌቶችን የገዛው ማን ይሆን? ያው የመንግስት ቢሮክራት ነዋ። እና ምን ተሻለ? የታብሌት ማስቀመጫ አትሮንስ በብዛት ለመግዛት ተወሰነ። ይሄ ትንሹ ብክነት ነው።
የእንግሊዝን የጤና ኢንሹራንስና አገልግሎት፣ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል አዲስ ፕሮጀክት የተጀመረው በ2007 ነው። ከዚያ ወዲህ ለፕሮጀክቱ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ፈስሷል። ውጤቱስ? የጤና ኢንሹራንስና አገልግሎት ትርምስምሱ ወጣ። ለማስተካከል እንዳይሞከር ደግሞ፤ ቴክኖሎጂው ጊዜው ያለፈበት ሆኖ ተገኘ። እናም፤ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ፕሮጀክት ሊለወጥ ይገባል ተብሏል። 15 ቢ. ዶላር ቀለጠች (300 ቢሊዮን ብር?)
ስኩል ኔት፣ ወረዳ ኔት፣ የዩኒቨርስቲዎች ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማዕከላት እየተባለ ስንት ቢሊዮን ብር እንደወጣ ይታወቃል። አንዳንዶቹ ከአስር አመት በላይ አስቆጥረዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አምስት አመት። እነዚህ ፕሮጀክቶች ምን አገልግሎት እየሰጡ ይሆን? ስኩል ኔት እና ወረዳ ኔት ለምን አገልግሎት ሊውሉ እንደሚችሉ እየታሰበበት ነው። የዩኒቨርስቲ ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማዕከላት፣ በወር አንዴ ለዚያውም ለጥቂት ደቂቃዎች ነው አገልግሎት የሚሰጡት። አንዳንዶቹማ ፣ በአመት አንዴ ከተከፈቱም ድንቅ ነው።
አሜሪካ እና ጀርመን ከአገራችን ጋር
የአሜሪካ መንግስት፣ አገልግሎት የማይሰጡ 50ሺ ቤቶች እንዳሉት የገለፀው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን፣ ለእነዚህ ቤቶች እድሳት በየአመቱ 25 ቢሊዮን ዶላር በጀት ይመደባል ብሏል። (በኢትዮጵያ አቅም፣ ስንት ሺ ቤቶች ናቸው፣ ሳይከራዩ ወይም ለሽያጭ ሳይቀርቡ ለአምስት አመታት ሲበላሹ የቆዩት?)
ለስልጠና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለማቋቋሚያ... ለምናምን እየተባለ በየአመቱ 125 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በጀት ይመደባል - በአሜሪካ። አብዛኛው በጀት በከንቱ እንደሚባክን የገለፁት ጥናት እንዲያካሂዱ የተመደቡ የመንግስት ኦዲተሮች ናቸው። ወደ ሩብ ያህል የሚጠጋው በጀት ግን ሙሉ ለሙሉ ያለ አንዳች ውጤት የሚባክን ነው ብለዋል ኦዲተሮቹ - ወደ 30 ቢ. ዶላር በየአመቱ።
በአገራችንም እንዲሁ፣ ለምግብ ዋስትናና ለስልጠና፣ ለጥቃቅንና ለአነስተኛ ተቋማት፣ ለብድርና ለገበያ ትስስር በሚሉ እልፍ ሰበቦች ብዙ ብር ይባክናል፡፡
በየአመቱ ለግብርና ዘርፍ ከሚመደበው የብዙ ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ገሚሱ፣ “የምግብ ዋስትና” ተብሎ ለሚታወቀው የድጐማና የእርዳታ ፕሮጀክት የሚውል ነው፡፡ 7.5 ሚሊዮን ያህል የገጠር ተረጂዎችንና ተደጓሚዎችን በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ አደርጋለሁ የሚለው መንግስት፤ በዚህ አመት ቁጥራቸውን ወደ 2 ሚሊዮን ዝቅ ለማድረግ አቅዶ ነበር - የዛሬ አራት አመት። ነገር ግን የተረጂዎቹና የተደጓሚዎቹ ቁጥር አሁንም ወደ 7 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ የውጭ እርዳታ የሚቀበሉ 6.5 ሚሊዮን ሰዎች መኖራቸውን አትዘንጉ፡፡ በድምር 13 ሚሊዮን ተረጂ ማለት ነው፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ የምርት ተቋማትን በስልጠናና በብድር በመደገፍ በየአመቱ ከ15 በመቶ በላይ እንዲያድጉ የወጣው እቅድስ? በአንድ በኩል እቅዱ ሙሉ ለሙሉ…ከዚያም በላይ ተሳክቷል። ከታቀደው በላይ ለብዙ ወጣቶችና ተቋማት ስልጠና ተሰጥቷል - ብዙ ገንዘብ ተመድቦላቸው፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ብድርም ተከፋፍሏል፡፡ ተሳክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን እቅዱ በጭራሽ አልተሳካም፡፡ እንዲያውም ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማት አመታዊ እድገታቸው፤ ባለፉት ሦስት አመታት እየቀነሰ አምና ወደ 3 በመቶ ወርዷል፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት በከንቱ ባከነ አትሉም?




Read 4435 times