Saturday, 31 May 2014 13:49

ኢትዮጵያ የ“WTO” አባል የመሆን ዕቅዷን ታራዝማለች ተባለ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

አባል ለመሆን፤ በቴሌኮም፣ በባንክና በኤሌክትሪክ ሃይል ኢንዱስትሪው የመንግስትን ድርሻና ቁጥጥር መቀነስ ግዴታ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት በቴሌኮምና በባንክ ዘርፎች ላይ ያለውን ከፍተኛ ድርሻና ቁጥጥር በማቆም ዘርፎቹን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት እንዲከፍት የሚገደድ ከሆነ በመጪው አመት የአለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን እቅዱን እንደሚያራዝም የንግድ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ባለፈው ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት፣ የአለም የንግድ ድርጅት አባል አገራት የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት  ለአለማቀፍ ውድድር ክፍት የሚያደርግበትን ጊዜ በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እያቀረቡ ነው፡፡
“የአገልግሎት ዘርፉን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ፡፡ የቴሌኮም፣ የባንክ እና የኤሌክትሪክ ሃይል ኢንዱስትሪዎችን ለግል ባለሃብቶች ክፍት የምናደርግበትን ጊዜ በግልጽ እንድናሳውቅ በተደጋጋሚ እንጠየቃለን” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከማጠናቀቃች በፊት፣ የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ የአገልግሎት ዘርፉን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንድናደርግ ጫና እየተደረገብን ይገኛል” ብለዋል፡፡
መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ እንደሚይዘው ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከአለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች የሚቀርቡ ከሆነ፣ አገሪቱ በ2015 አባል ለመሆን የያዘችውን ዕቅድ ልታራዝም ትችላለች ብለዋል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት የጸደቀው የአለም የንግድ ድርጅት አዲስ ህግ፣ የእድገት ደረጃቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ የአለም አገራት የድርጅቱ አባል ለመሆን የሚችሉበትን መስፈርት በመጠኑ ቀለል እንዳደረገ የዘገበው ሮይተርስ፤ ድሃ አገራት የተለያዩ ዘርፎችን ቀስ በቀስ ወደ ግል ኢንቨስትመንት እንዲያዘዋውሩና ደረጃ በደረጃ ለአለማቀፍ ውድድር ክፍት እንዲያደርጉ የሚፈቅድ መሆኑን አስታውሷል፡፡
“የትኞቹ የአገሪቱ ህጎች ከአለም የንግድ ድርጅት ጋር እንደሚጣጣሙና፣ የትኞቹ እንደሚጣረሱ እየገመገምን ነው” ያሉት አቶ ከበደ፤ “እ.ኤ.አ በ2015 የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን የያዝነው ዕቅድ ሊራዘም ይችላል” ብለዋል፡፡
አሁን ባለበት ሁኔታ አገሪቱን የአለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ኢኮኖሚው አነስተኛ እንደሆነና የበለጠ ማደግ እንደሚገባው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና፣ የአለም የንግድ ድርጅትን አባል  ለመሆን በርካታ አመታት ወስዶባታል ብለዋል፡፡
በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው የአገሪቱ ገበያ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ አገራት ባለሃብቶችን መሳብ በመቻሉ፣ በርካታ የስዊድን፣ የቻይና እና የቱርክ ባለሃብቶች በዘርፉ ሰፊ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆመው የሮይተርስ ዘገባ፤ የአገሪቱ ህጎች የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎት በመሳሰሉ ፖለቲካዊ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ዘርፎች የውጭ ኢንቨስትመንትን ያግዳሉ ብሏል፡፡

Read 3840 times