Saturday, 31 May 2014 13:37

የ40/60 ቤቶች ግንባታና የተመዝጋቢዎች ፍላጐት አይጣጣምም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

    የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሚያስገነባቸው የ40/60 ቤቶች አይነትና የተመዝጋቢው ፍላጐት እንደማይጣጣም መረጃዎች ያመለክቱ ሲሆን፤ የኢንተርፕራይዙ እቅድ በተለይ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤት የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎችን ማስተናገድ አይችልም ተባለ።  
ቀደም ብሎ በተዘጋጀው እቅድ ላይ ባለ አንድ፣ ባለሁለት እና ባለ ሶስት መኝታ ቤቶችን ጨምሮ ንግድ ቤቶች የተካተቱ ሲሆን ባለ 1 መኝታ ቤት ፈልገው የተመዘገቡት ከተገመተው በታች ሆኗል። ባለ ሁለት እና ባለ ሶስት መኝታ ቤት ፈልገው የተመዘገቡት ደግሞ፤ ከተገመተው ከእጥፍ በላይ ይበልጣል፡፡ ለንግድ ቤቶች ግን አንድም ተመዝጋቢ አልተገኘም፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር እቅዱ ላይ ከአጠቃላይ ተመዝጋቢ መካከል 35 በመቶ የሚሆነው ባለ አንድ መኝታ ቤቶችን ምርጫው ያደርጋል ተብሎ የተጠበቀ አስር በመቶ ቢሆንም (ወደ 17ሺ ገደማ) ቤት ፈላጊዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት፡፡ ከአጠቃላይ ተመዝጋቢው 25 በመቶው ደግሞ በባለ ሁለት መኝታ ቤት ይመዘገባል ተብሎ ቢጠበቅም ከተገመተው በላይ 46 በመቶ (76ሺ ገደማ እንደተመዘገበ ታውቋል፡፡ ለባለ ሶስት መኝታ ቤትም እንዲሁ 20 በመቶ የተጠበቀ ሲሆን የተመዘገበው ግን 44 በመቶ (73ሺ ገደማ) ናቸው፡፡  
ፕሮጀክቱን የሚመሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የተመዝጋቢውን ቁጥር ከቤቶቹ አይነት ጋር ለማመጣጠን በሚል፣ ቀደም ሲል የወጣው የቤቶች ዲዛይን እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል ባለ 12፣ ባለ 9 እና ባለ 7 ፎቅ ቤቶች ይሰራሉ ተብሎ የታቀደ ቢሆንምበአሁን ሰአት ባለ 18 እና 24 ፎቅ አዳዲስ ዲዛይን መዘጋጀቱን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በሰንጋተራ ሳይት በግንባታ ላይ ያሉት ቤቶች ቀደም ሲል ቤት ፈላጊዎች ከተመዘገቡበት እና በስትራቴጂክ እቅዱ ከተቀመጠው የስፋት መጠን የተለዩ መሆናቸውንም ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡ በባለ 12 እና ባለ 9 ፎቅ ቤቶች ግንባታ ላይ ቀደም ሲል ቤት ፈላጊዎች ባለ አንድ መኝታ ቤት 55 ሜትር ስኩየር ስፋት ይኖረዋል ተብለው የተመዘገቡ ቢሆንም በዲዛይን ላይ የተቀመጠው የቤቶቹ ስፋት 96.72 ሜትር ስኩየር ሲሆን በምርመራው ሂደትም በመሬት ላይ የሰፈረው 85.4 ሜትር ስኩየር ሆኖ መገኘቱን ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ ባለ 2 መኝታ ቤት ቤት ፈላጊዎች ሲመዘገቡ 75 ሜትር ስኩየር ስፋት ይኖረዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዲዛይኑ ላይ 115.81 ሜትር ስኩየር ሆኖ በተግባር የተሰራው ደግሞ 116.2 ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ባለ ሶስት መኝታ ቤትን በተመለከተም 100 ሜትር ስኩየር ይኖረዋል የተባለው ቤት በዲዛይኑ ላይ 128 ሜትር ስኩየር ሆኖ መሬት ላይ ተሰራው በ129.5 ሜትር ስኩየር ሆኖ መገኘቱን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ በሌሎች ቤቶች ላይም ተመዝጋቢው በሚያውቀው ስፋት፣ በዲዛይኑ ላይ ባለው እና መሬት ላይ በወረደው ስፋት መጠን መካከል ልዩነቶች መኖራቸውን ምንጮቻችን ጨምረው ጠቁመዋል፡፡ ይህ መሆኑም የግንባታ ወጪው ስለሚጨምር ምናልባት የቤቱን የማጠናቀቂያ ስራዎች ወጪ ለባለ እጣዎች ሊተው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በአንድ ህንፃ ላይ በአማካይ ወደ 1ሺህ ሰው የሚጠጋ ይኖራል ተብሎ የሚገመት ሲሆን እነዚህን ሁሉ ያመላልሳል ተብሎ ለታሰበው ሊፍት የተተወው ክፍተት ቢበዛ 8 ሰዎችን ብቻ በአንድ ጊዜ ማመላለስ ለሚያስችል ሊፍት መሆኑን በማመልከት ህንፃው የነዋሪውን ምቾት የማሟላቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ብለዋል፡፡ ህንፃዎቹ ከሚይዙት የነዋሪ ብዛት እንዲሁም የነዋሪውን የተለያዩ ቁሳቁሶች ከማጓጓዝ አንፃር በሌሎች ሃገሮች በታየው ተሞክሮ መሰረት በአንድ ጊዜ እስከ 20 ሰው ማጓጓዝ የሚችሉ ሊፍቶች መገጠም ይገባቸው ነበር ሲሉ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡
በአጠቃላይ ለ40/60 የቤት ፕሮግራም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 164 ሺህ 779 ቤት ፈላጊዎች የተመዘገቡ ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ እድለኞች በቀጣይ ዓመት ቤታቸውን እንደሚረከቡ ተናግሯል፡፡
ከጥር 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የ13ሺህ 881 ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት የ15ሺህ ቤቶች ግንባታ ይጀመራል ተብሏል፡፡  

Read 6271 times