Saturday, 31 May 2014 12:25

እናቱ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የከተተችው ህፃን ከሞት ተረፈ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(3 votes)

በሐረር ከተማ “ማሳደግ አልችልም” በሚል ሰበብ የወለደችውን ህፃን በፌስታል አድርጋ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የከተተች እናት በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ህፃኑ ከ6 ሰዓት በኋላ ከጉድጓዲ ወጥቶ ህይወቱ ተርፏል፡፡
በሐረሪ ክልል በቀበሌ 19 ልዩ ስሙ አማሪሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነችው የ20 ዓመቷ ወጣት፤ ባለፈው ሐሙስ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ የተገላገለችውን ህፃን በፌስታል አድርጋ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ እንደከተተችው የክልሉ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ወደ ሽንት ቤት ያመራ ጎረቤት የህፃኑን ለቅሶ ሰምቶ ለፖሊስ መጠቆሙንና ህፃኑ በመፀዳጃ ቤቱ ጉድጓድ ውስጥ ተንሳፎ በህይወት መገኘቱን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በቀን ሥራ የምትተዳደረው እናት ቤቷ ውስጥ ተኝታ መገኘቷን የገለፀው ፖሊስ፤ ህፃኑን መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተተችው የማሳደግ አቅም ስለሌላት እንደሆነ በመናገር ድርጊቱን መፈፀሟን አምናለች ብሏል፡፡ህፃኑ በሐረር ከተማ በሚገኘው የህይወት ፋና ሆስፒታል በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ ጠቁሞ፤ እናትየው ምርመራ እየተደረገባት እንደሆነ ገልጿል፡፡  

Read 4838 times