Saturday, 31 May 2014 12:23

የ “ዕንቁ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ በ30ሺ ብር ዋስ ተፈታ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(2 votes)

በዕንቁ መጽሔት ላይ ባለፈው መጋቢት ወር “እየተገነቡ ያሉ ሃውልቶች የማንና ለማንስ ናቸው?” በሚል ርዕስ ከወጣ ፅሁፍ ጋር በተገናኘ ከፖሊስ ጥሪ ደርሶት ወደ ማዕከላዊ ፖሊስ የሄደው የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ አልያስ ገብሩ፤ ከ3 ቀን እስር በኋላ ከትናንት በስቲያ  በ30ሺ ብር ዋስ ተለቀቀ፡፡
በመጽሔቱ ላይ የወጣው ጽሑፍ፤ ከሁለት ወር በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለግጭት ማነሳሳቱን የጠቆመው ፖሊስ፣ ግጭቱን ተከትሎ በሰውና በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት መጽሔቱን  ተጠያቂ አድርጐታል፡፡
ዋና አዘጋጁ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ማዕከላዊ ፖሊስ ቀርቦ የተለያዩ ጥያቄዎች ከቀረቡለት በኋላ፣ “ጀርባውን ማጥናት ያስፈልጋል” በሚል የዋስትና መብቱ ተከልክሎ፣ በእስር እንዲቆይ መደረጉን ተናግሯል፡፡ በነጋታው ማክሰኞ ፍ/ቤት ቀርቦ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ፍ/ቤቱ የሰባት ቀን ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ የዋስ መብቱን ተከልክሎ ለተጨማሪ ሁለት ቀን በእስር መቆየቱን የገለፀው የመፅሄቱ ዋና አዘጋጅ፤ ከትላንት በስቲያ በ30 ሺ ብር ዋስ መፈታቱን ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል፡፡ ሐሙስ ዕለት ፖሊስ ጠርቶ እንዳነጋገረው ጠቅሶ፤ “ከአሁን በኋላ እንዲህ አታደርጉ፤ የሚከፋፍል ሳይሆን አንድነትን የሚያጠናክር ነገር ፃፉ” የሚል ምክር እንደሰጠውና ዋስ ጠርቶ መለቀቁን ተናግሯል - ዋና አዘጋጁ፡፡
ከፅሁፉ ጋር በተገናኘ ቀድሞ የተጠየቀውም ሆነ የደረሰው መረጃ አለመኖሩን የገለፀው ኤልያስ፤ የዋስ መብት ተከልክዬ መታሰሬ የፕሬስ ህጉን ይፃረራል ብሏል።
“ከፅሁፍ ጋር በተገናኘ ለሚመጣ ቅሬታ ዋና አዘጋጁ ለምርመራ ፖሊስ ጋ መቅረቡ የተለመደ ነው፤ ነገር ግን በእስር አይቆይም፤ በዋስ ተለቆ ጉዳዩን ውጪ ሆኖ ይከታተላል” ያለው ዋና አዘጋጁ፤ የዋስ መብት ተከልክዬ መታሰሬ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡

Read 3066 times Last modified on Saturday, 31 May 2014 12:30