Saturday, 31 May 2014 11:41

የሲኖዶስ ጉባኤ በፓትርያርኩና ጳጳሳቱ ፍጥጫ ተቋጨ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጳጳሳት የፓትርያርኩን የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ቅድመ ኹኔታ አልተቀበሉትም
‹‹ቅድመ ኹኔታው የማኅበሩን አገልግሎት የሚያቀጭጭና በሒደትም የሚያስቆም ነው›› /ታዛቢዎች/

የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅን እንደ አንድ አጀንዳ የያዘው የዘንድሮው የሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ጉባኤ ከረቂቁ ጋር በተያያዘ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል በተፈጠረ ፍጥጫ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
የፍጥጫው መንሥኤ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴ ያዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ በዝርዝር ከመታየቱ አስቀድሞ ፓትርያርኩ ለውይይቱ እንደ ቅድመ ኹኔታ ያቀረቧቸው ነጥቦች በአብዛኛው የጉባኤው አባላት የገጠመው ተቃውሞ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩት ፓትርያርኩ፤ በአጀንዳው ላይ የሚካሔደውን ውይይት ቀጣይነት ይወስናል በሚል ካቀረቧቸው ቅድመ ኹኔታዎች ውስጥ÷ ለአጥኚ ኮሚቴው መመሪያ የሰጡባቸው ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› አንድም ሳይቀነሱ በደንቡ እንዲካተቱና ረቂቁ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከጸደቀ በኋላ እንዲታይ የሚሉ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ አስቀምጠዋቸዋል በተባሉት ነጥቦች ስምምነት ላይ ከተደረሰ ስብሰባው ሊቀጥል እንደሚችል በመጥቀስ፣ ኃይለ ቃልም ተማኅፅኖም በተቀላቀለበት አኳኋን መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
ይኹንና የሚበዙት ሊቃነ ጳጳሳት በቀጥታ እንደተቃወሟቸው፣ የተቀሩትም ድጋፍ ከመስጠት እንደተቆጠቡ ታውቋል፡፡ ፍጥጫው ቀጥሎ አቡነ ማትያስ ‹‹አቋሜ ይኽው ነው፤›› በሚል አጀንዳውን መዝጋታቸውን ሲያስታውቁም፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ እንዲህ ተብሎ የሚተው አይደለም፤›› በሚል ከኹሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ምንጮች ይገልፃሉ፡፡
የቅ/ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ የሚካሔደው ምልዓተ ጉባኤው ከጅምሩ ተስማምቶ ባጸደቃቸው የመነጋገርያ አጀንዳዎች መሠረት እንደኾነ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቃውሞ ተጠቅሷል፡፡
የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ እንዲቀርብ ከታዘዘበት ከጥቅምት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እየተንከባለለ ለኹለት ዓመታት መዘግየቱን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ የተጓተተው አጀንዳ ‹‹የማኅበሩን አገልግሎት ያቀጭጫሉ፣ በሒደትም ያስቆማሉ›› በሚል በተተቹት የፓትርያርኩ ቅድመ ኹኔታዎች ሊዘጋ እንደማይችልና ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ ቅ/ሲኖዶሱ ሊወያይበት እንደሚገባ በአጽንዖት በመናገራቸው፣ ጉዳዩ ሳይቋጭ ለቀጣዩ ቀን በይደር ተላልፏል፡፡
አጀንዳው ሰኞ፣ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ጥዋት መታየት ሲጀምር፣ አጥኚ ኮሚቴው በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አሻሽሎ ያዘጋጀው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብና የኮሚቴው ቃለ ጉባኤ በንባብ መሰማቱም ታውቋል፡፡ ፓትርያርኩ ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› በሚል ራሱን በቻለ ርእስ በደንቡ እንዲካተት ለአጥኚ ኮሚቴው ጥብቅ መመሪያ የሰጡበት ባለ24 አንቀጽ ሰነድም አብሮ እንዲነበብላቸው መጠየቃቸው የመጀመሪያው ቀን የፍጥጫ መነሻ እንደነበር ታውቋል፡፡
በ24 አንቀጾችና በአምስት ገጾች የተዘረዘሩት የፓትርያርኩ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች÷ በአባላቱ በጎ ፈቃድ ተቋቁሞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘውን ማኅበር፤ ከሕገ ተፈጥሮው ውጭ የሚያደርግ፣ በቅ/ሲኖዶሱ ፈቃድ ከሚመራበት ደንብ በተፃራሪ ተቋማዊ ህልውናውን፣ የአመራር ምርጫውን፣ የአባላት አያያዙንና የሥራ ቦታውን ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥና አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ፣ በአርኣያነት የሚጠቀሰውን የፋይናንስ አሠራሩን ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን እንደተረዱ ያብራሩ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፣ ‹‹ቀጣዩ ቀንም የከበደ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ፡፡
በይደር የተያዘው አጀንዳ በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ጥዋት ተጀምሮ ለግማሽ ቀን የቀጠለ ቢኾንም ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያውን በዝርዝር ለመመልከት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡
‹‹ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ ያስቀመጧቸውን ነጥቦችና በአጀንዳው ቀጣይነት ላይ የያዙትን አቋም አልቀየሩም፤ ሊቃነ ጳጳሳቱም ባጸደቅነው አጀንዳ መሠረት ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሠየምነው አጥኚ ኮሚቴ አዘጋጅቶ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ነው፤ መካተት ያለበት ነገር ካለም ማኅበሩን በሚያሠራ መልኩ እያገናዘብን በሒደት እናየዋለን እንጂ አጀንዳው በቅድመ ኹኔታ መታሰር የለበትም በሚል ለማስረዳት ጣሩ፤ በመጨረሻም ፓትርያርኩ “እንግዲያውስ ስብሰባውን ለመምራት አልችልም” በማለታቸው የስብሰባው መቋጫ ኾኗል፤›› ይላሉ- ሒደቱን ለአዲስ አድማስ የገለጹ የስብሰባው ምንጮች፡፡
የማኅበሩ ደንብ በመጀመሪያ ረድፍ ከሰፈሩት የቅ/ሲኖዶሱ መነጋገርያ ነጥቦች አንዱ እንደነበር ያስተዋሉ ሌሎች የስብሰባው ተከታታዮች በበኩላቸው፤ አጀንዳው ከቅደም ተከተሉ ወጥቶ እየተገፋ በመጨረሻ መነሣቱ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ይህ ዓይነቱ አለመግባባት ሊነሣ እንደሚችል ጠቋሚ ነበር ብለዋል፡፡  
ተከታታዮቹ አክለውም፣ ፓትርያርኩ ስብሰባውን ለመምራት ፈቃደኛ ባይኾኑም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በተደነገገው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ ምልዓተ ጉባኤው በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያዎች ላይ የጀመረውን ውይይት ቀጥሎ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚችልባቸው አግባቦች እንደነበሩ ገልጸው፣ ቅ/ሲኖዶሱ በግለጫው የመጨረሻው አጀንዳው ባደረገው የማኅበሩ ደንብ ላይ “ውይይት ተደርጎበታል” ከማለት በስተቀር ስብሰባውን የቋጨበት አኳኋን ያልተለመደና አደናጋሪ ነው ብለዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ አደራጅቶ ማንነቱን የሚያውቅበትንና በግብረ ገብ የሚታነፅበትን ትምህርተ ሃይማኖት ከማስተማር ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት አገልግሎታቸውን በብቃት የሚወጡበትን ኹለገብ ሞያዊ ድጋፍ የመስጠት ሓላፊነት እንዳለበት በደንብ አጥኚ ኮሚቴው ማሻሻያ ረቂቅ ላይ መስፈሩ ታውቋል፡፡
ይኹንና ‹‹ጥበቃና ጥንቃቄ›› በሚል ፓትርያርኩ እንደ መመሪያ ያቀረቧቸው ድንጋጌዎችና ግዴታዎች እንዲሁም ከልዩ ጽ/ቤታቸው ማኅበሩን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች የማኅበሩን አገልግሎት የማቀጨጭ፣ በሒደትም አዳክሞ የማስቆም ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፣ ቅ/ሲኖዶሱ የማኅበሩ ደንብ እንዲሻሻል ግንቦት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ÷ ማኅበሩ ከጊዜው ጋር የሚሔድ፣ አገልግሎቱና አደረጃጀቱ የደረሰበትን ስፋትና ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ልማት የሚጠቅም ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚያስፈልገው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገለልተኛ የሕግ ባለሞያዎችና የማኅበሩ አባላት በታከሉበት አጥኚ ኮሚቴ የጋራ ጥናት የተዘጋጀ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም. በበጎ ፈቃድ በተሰበሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተመሠረተው ማኅበሩ፤ እየተመራ ያለው ቅ/ሲኖዶስ በ1994 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ አሻሽሎ በሰጠው መተዳደርያ ደንብ ሲኾን አሁን የተሻሻለው ረቂቅ ተመርምሮ ባለመጽደቁ በነባሩ ደንብ እየተመራ ለመቀጠል እንደሚገደድ ተመልክቷል፡፡

Read 2389 times