Saturday, 24 May 2014 15:23

“ኤል ደርቢ ማድሪሊያኖ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ዛሬ በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝበን በሚገኘው  ኢስታድዮ ዳ ሉዝ ስታድዬም ለ59ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ  ዋንጫ  ሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች ሪያልና አትሌቲኮ ማድሪድ  ይፋጠጣሉ፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ለፍፃሜ ጨዋታ የአንድ ከተማ ክለቦች ሲገናኙ  ለመጀመርያ ጊዜ  ነው፡፡ የዋንጫ ጨዋታው በ200 አገራት የቀጥታ ቴሌቭዢን ስርጭት ሲኖረው እስከ 1 ቢሊዮን ተመልካች እንደሚያገኝ ተገምቷል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ዋንጫውን ለሚያሸንፈው ክለብ 10.5 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ለሁለተኛው ክለብ ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ዩሮ ያበረክታል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ የማድሪድ ክለቦች እስከ ፍፃሜው በነበራቸው ግስጋሴ ከቴሌቭዥን ስርጭት መብት፤ ከሜዳ ገቢ እና ከተለያዩ ንግዶች በነፍስ ወከፍ እስከ 55 ሚሊዮን ዩሮ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከዋንጫው ጨዋታ በፊት በተደረጉት 124 ጨዋታዎች 357 ጎሎች ሲመዘገቡ፤ ኮከብ ግብ አግቢነቱን የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ16 ጎሎች እየመራው ነው፡፡
ሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች እርስ በራስ የሚገናኙበት ጨዋታ “ኤል ደርቢ ማድሪሊያኖ” በሚል መጠሪያ ሲታወቅ ከዛሬው የዋንጫ ጨዋታ በፊት  264 ጨዋታዎች ተደርገውበታል፡፡  በ143 ሪያል ማድሪድ ሲያሸንፍ በ64  ጨዋታዎች ያሸነፈው  አትሌቲኮ ማድሪድ ነው፡፡ በ57 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ኤልደርቢ ማድሪሊያኖ አንድ ክፍል ዘመን ያስቆጠረ የእግር ኳስ ትንቅንቅ ነው፡፡  ባለፉት አስር ዓመታት ይህን ታላቅ ደርቢ ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና የሚገናኙበት ኤልክላሲኮ ሸፍኖት  ቆይቷል፡፡
 የዓለም ሃብታሙ ክለብ ሪያል ማድሪድ ዛሬ ዋንጫውን ካነሳ በውድድሩ ታሪክ ለ10ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ለፍፃሜ ቀርቦ 9 ዋንጫዎችን ወስዷል፡፡ የመጨረሻው ድሉ ከ12 ዓመት በፊት ነው፡፡ በአንፃሩ አትሌቲኮ የሚያገኘው ድል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ  ነው፡፡ ከ40 ዓመት በፊት ብቸኛውን የፍፃሜ ጨዋታ አድርጎ  በባየር ሙኒክ 5ለ0 ተሸንፎ ዋንጫውን አልምጦታል፡፡ ሪያል ማድሪድ ኮፓ ዴ ላሬይን ቢያሸንፍም የውድድር ዘመኑን ውጤታማ ለማለት የግድ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያስፈልገዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት   ከ18 ዓመት በኋላ  የላሊጋ ዋንጫን ላገኘው አትሌቲኮ የማድሪድ ከተማ በ200ሺ ደጋፊዎች ተጥለቅልቃ ነበር ፡፡ የአውሮፓን ክብር ደርቦ ካሸነፈ  ደግሞ በከተማዋ የሚኖረው ፌሽታ ሚሊዮኖችን ያሳትፋል ተብሏል፡፡
ሪያል ማድሪድ በአገር ውስጥ ውድድሮች ከ60 በላይ፤ በአውሮፓ ደረጃ ከ11 በላይ ዋንጫዎችን የሰበሰበ ሲሆን አትሌቲኮ  በአገር ውስጥ ውድድሮች 24 በአውሮፓ ደረጃ ደግሞ 5 ዋንጫዎች አሉት፡፡
በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ሪያል ማድሪድ  32 ጊዜ ሻምፒዮን ሲሆን አትሌቲኮ ዘንድሮ 10ኛውን የሻምፒዮናነት ክብር አግኝቷል፡፡ በኮፓ ዴላሬይ ሪያል ማድሪድ 19 ዋንጫ ሲወስድ አትሌቲኮ ማድሪድ 10 አለው፡፡ሪያል ማድሪድ ለውድድር ዘመኑ የነበረው በጀት 515 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን በ4 እጥፍ የሚያንሰው የአትሌቲኮ በጀት 120 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
ሪያል ማድሪድ ማልያውን ከፍተኛ ስፖንሰርሺፕ ሲያገኝበት አትሌቲኮ ማድሪድ ለ2 የውድድር ዘመን ስፖንሰር አጥቶ የአዘርባጃን መፈክር ላንድ ኦፍ ፋየርን ለጥፎ ቅናሽ ገቢ አለው፡፡
ሪያል ማድሪድ  የተመሰረተው ከ112 ዓመታት በፊት ሲሆን በዘንድሮ አጠቃላይ የተጨዋቾች ስብስቡ በትራንስፈር ማርኬት 505 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ሲኖረው  ከተመሰረተ ከ111 ዓመታት የሚሆነው የአትሌቲኮ ማድሪድ የተጨዋቾች ስብስብ ተመኑ 282 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡

Read 1829 times