Saturday, 24 May 2014 15:18

የግብፁ ጄ/ል አልሲሲ ለፕሬዚዳንትነት በ94% እየመሩ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሃይማኖት አክራሪነቱ ምክንያት ተቃውሞ የገጠመውን “የሙስሊም ብራዘርሁድ መንግስት” በመገልበጥ ስልጣን የያዙት ጄ/ል አልሲሲ፣ በግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያለ ብዙ ፉክክር በሰፊ ልዩነት ያሸንፋሉ ተብሏል።
በእርግጥ ምርጫው የሚጀመረው  ሰኞ ነው። ነገር ግን፤ በውጭ የሚኖሩ ግብፃዊያን ከወዲሁ ድምፅ ሰጥተው ቆጠራ ተካሂዷል። በዚሁ ቆጠራ፤ ጄ/ል አልሲሲ፣ 94.5% ድምፅ ሲያገኙ፣ ወደ ሶሻሊዝም የሚያዘነብሉ ተቀናቃኛቸው 5.5% ድምፅ ማግኘታቸውን ዎልስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
ሰኞ በሚጀመረው የአገር ውስጥ ምርጫም አልሲሲ አብዛኛውን ድምፅ እንደሚያገኙ ከመራጮች የተሰበሰበሰ አስተያየት ይጠቁማል። በእርግጥ፤ በጭራሽ ድምፅ ላለመስጠትና ላለመምረጥ የወሰኑ ግብፃዊያን ብዙ ናቸው። ከፊሎቹ ጄነራሉን በጠላትነት የሚቃወሙ የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች ናቸው። ከፊሎቹ ደግሞ፤ የተሻለ አማራጭ የያዘ ደህና ፓርቲና ደህና ፖለቲከኛ በማጣት ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል። ከእነዚህ ውጭ የሆነው አብዛኛው ግብፃዊ መራጭ፤ ለጊዜው ለአገሪቱ የሚበጃት ጄነራል አልሲሲን የመሰለ ጨከን ያለ መሪ ነው ብለው ያምናሉ።
በሌላ በኩል፤ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ይዘው ከሰላሳ አመት በላይ ግብፅን የገዟት ሆስኒ ሙባረክ፣ 3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የመንግስት ገንዘብ አጭበርብረዋል በሚል ሰሞኑን የሶስት አመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ልጃቸው ደግሞ የአራት አመት እስር። ከዚሁም ጋር የ14 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

Read 1921 times