Saturday, 24 May 2014 15:18

በሊቢያም፣ ጡረተኛ ጄነራል ስልጣን ለመያዝ ተነስቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

         ጡረተኛው ጄነራል ካሊፋ ሂፍጠር ከሁለት ወር በፊት አስቀድመው ተናግረዋል። “የሊቢያ መንግስት የሃይማኖት አክራሪዎችንና አሸባሪዎችን መቆጣጠር ካልቻለ፤ የራሴን እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት በይፋ የተናገሩት በየካቲት ወር ነው። አንዳንድ ሊቢያውያን፤ “ምነው እንደአፋቸው ባደረጉት!” በማለት ተመኝተዋል። አንዳንዶች ደግሞ፤ “ጦር ሰራዊት የሌለው የጦር ጄነራል!” በማለት ተሳልቀዋል። ከአርባ አመት በላይ ሊቢያን አንቀጥቅጠው የገዟት ሶሻሊስቱ ሙዐመር ጋዳፊ በአመፅ ከስልጣን ወርደው ከተገደሉ በኋላ ለጥቂት ወራት የተስፋ ጭላንጭል ቢታይም፤ ብዙም ሳይቆይ አገሪቱ ወደ ግጭትና ትርምስ ተንሸራትታለች።
ፓርላማው፤ በአክራሪዎች እና አክራሪነትን በሚቃወሙ በርካታ ፓርቲዎች ለሁለት ተከፍሏል። አክራሪዎቹ እርስበርስ ይቀናቀናሉ - በጭካኔ ብዛት ይፎካከራሉ። አክራሪነትን የሚቃወሙት ፓርቲዎችም ቢሆኑ፤ በጎሳ እየተቧደኑ ይሻኮታሉ። ፉክክሩና ሽኩቻው፣ በንግግርና በፅሁፍ ብቻ አይደለም። ዘ ጋርድያን እንደዘገበው፤ እያንዳንዱ ፓርቲና ቡድን፤ የየራሱ ጦርና ታጣቂ ቡድን አለው። አንዳንዶቹ በታንክና በከባድ መሳሪያ የተደራጁ፤ በሺ የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን ያሰለፉ ናቸው። የታጣቂ ቡድኖቹ ብዛት በመቶ ይቆጠራል። በሊቢያ የጦር መሳሪያ እጥረት የለም። አንዳንዶቹ  እንደአቅሚቲ በወረዳ፣ ከዚያም አልፎ በመንደርና በሰፈር ግዛታቸውን ለማስፋፋት የታጣቂ ቡድን ያንቀሳቅሳሉ። ገሚሶቹ ግን ወደቦችንና የነዳጅ ማውጫ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ይዘምታሉ። ሌት ተቀን፣ ግድያ፣ ተኩስ፣ ፍንዳታ፣ ውጊያ ነው። የሊቢያ የነዳጅ ምርት፣ በቀን 1.4 ሚሊዮን በርሜል እንደነበረ የገለፀው ዎልስትሪት ጆርናል፤ አሁን በታጣቂዎች ግጭት የተነሳ የአገሪቱ የነዳጅ ምርት ወደ 200ሺ እንደወረደ ዘግቧል።
ባለፈው የካቲት ወር በትሪፖሊ በርካታ ነዋሪዎች በታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ ከፍተኛ ተቃውሞ በመነሳቱ፤ ዋና ከተማዋን ተቀራምተው የነበሩ ታጣቂ ቡድኖች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። ግን ብዙም አልራቁም። ዙሪያውን በተለያዩ ከተሞች ካምፕ ሰርተው ተከማችተዋል። ትሪፖሊ የተወሰነ እፎይታ ብታገኝም፤ እንደ ቤንጋዚና ሚዝራታ የመሳሰሉ ከተሞች ግን የታጣቂ ቡድኖች መፈንጫ ሆነዋል። በየሳምንቱ፤ በደርዘን የሚቆጠሩ ፖሊሶች፣ ምልምል ወታደሮችና ዳኞች በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ይገደላሉ - በተለይ ደግሞ ከአልቃይዳ በማይተናነሱ አክራሪ ቡድኖች። አነስተኛ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ደግሞ፣ በጎሳ በተቧደኑ ታጣቂዎች ይታመሳሉ።
በጎሰኝነት እና በሃይማኖት አክራሪነት የተቃወሱ አገሮች ውስጥ፤ እንደ ሞሶሎኒና ሂትለር፤ ወይም እንደ ግብፁ ጄነራል አልሲሲ፤ “እናት አገር” ወይም “አባት አገር” የሚል መፈክር ይዞ የሚመጣ ብሔረተኛ መች ይጠፋል? በሊቢያ ደግሞ ጄነራል ካሊፋ ሂፍጠር።
ከአርባ አመት በፊት የጋዳፊ ወዳጅ የነበሩት ጄ/ል ሂፍጠር፤ ጎረቤት አገር ላይ የወረራ ዘመቻ እንዲመሩ ተመድበው ስላልተሳካላቸው ነው የጋዳፊ ጥርስ ውስጥ የገቡት። እንደምንም አምልጠው በስደት ወደ አሜሪካ የገቡት ጄ/ል ሂፍጠር፤ ተቃዋሚዎችን ለማደራጀት ለበርካታ አመታት ቢጣጣሩም የጋዳፊን መንግስት ሊያነቃንቁት አልቻሉም። የዛሬ 3 አመት በአረብ አገራት ሰፊ የተቃውሞ አመፅ የተቀሰቀሰ ጊዜ ነው፤ ወደ ሊቢያ ተመልሰው የወታደራዊ አመፅ መሪ የሆኑት። ከድል በኋላ የመከላከያ ሃይል ዋና አዛዥ የመሆን እድል አላገኙም። ምክትል ዋና አዛዥ ሆነው ትንሽ ከቆዩ በኋላ፤ ያንኑም ትተው የወጡት ጄ/ል ሂፍጠር፤ ለሁለት አመታት ያህል ድምፃቸው አልተሰማም። ድምፃቸውን ሊያሰሙ ቢሞክሩም፤ ያን ያህልም ሰሚ አልነበራቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ በጎሳ የተቧደኑ ታጣቂዎች እና በተለይም የሃይማኖት አክራሪ ቡድኖች የሚፈፅሙት ግድያ፣ ግጭትና ፍንዳታ እየተባባሰ፣ በሰላም ወጥቶ መመለስ እየጠፋ ሲመጣ አብዛኛው ሊቢያዊም ሲማረር ግን ሰሚ ተገኘ።
ለጄነራሉ ጆሯቸውን ለመስጠት ቀዳሚ ከሆኑት መካከል፣ ፖሊሶችና ወታደሮች ናቸው። የታጣቂ ቡድኖች የግድያ ዘመቻ፤ በፖሊሶችና ወታደሮች ላይ ይበረታልና። በጎሳ የተቧደኑ አንዳንድ ታጣቂዎችንም ለማግባባት ሞክረዋል ጄ/ል ሂፍጠር። እንዲህ አይነት ዝግጅቶችን ለሁለት ወራት እንዳካሄዱ የሚገልፁት ጄ/ል ሂፍጠር፤ ባለፈው ሳምንት በቤንጋዚና በትሪፖሊ ከተሞች ወታደሮችን በማሰማራት ወደ ጥቃት ዘመቻ እንደተሸጋገሩ አውጀዋል። ያሰባሰቡትን ወታደራዊ ሃይል፤ “የሊቢያ ብሔራዊ ጦር” ሲሉ ሰይመውታል። “አባት አገር ተደፍሯል” የሚሉት ጄ/ል ሂፍጠር፤ የዘመቻው መጠሪያ ስም፤ “የሊቢያን ክብር የማስመለስ ዘመቻ” የሚል እንደሆነ ተናግረዋል። ቤንጋዚ ከተማ ውስጥ፤ ባለፈው አርብ ሶስት አክራሪ ቡድኖች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ፤ እሁድ እለት በትሪፖሊ ፓርላማ ላይ ታጣቂዎችን አዝምተዋል።
የፓርላማው የስልጣን ዘመን ካበቃ ሁለት ወር ስላለፈው ህጋዊ ስልጣን የለውም የሚሉት ጄ/ል ሂፍጠር፤ “አክራሪዎች ፓርላማውን ተቆጣጥረውታል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአክራሪ ቡድን ተወካይ ናቸው፤ ብሔራዊ ጦርና ብሔራዊ ፖሊስን ከማደራጀት ይልቅ አክራሪ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ያጠናክራሉ” በማለት ፓርላማ ላይ የፈፀሙት ጥቃት ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ። አክራሪ ቡድኖችና ታጣቂዎች በድርድርና በውይይት አያምኑም፤ ስለዚህ እስክናጠፋቸው ድረስ እንዋጋለን ብለዋል ጄነራሉ።
የጄነራሉን ድርጊት ለማውገዝ እንደማይፈልጉ የገለፁ አንዳንድ ሚኒስትሮችና የፓርላማ አባላት፤ አክራሪ ቡድኖችን መቃወም ተገቢ ነው ብለዋል። የተወሰኑ ሚኒስትሮች ደግሞ፤ የጄነራሉ ጥቃት አደገኛ ነው፤ በቋፍ ያለችውን አገር ወደ ለየለት ጦርነት ሊያስገባት ይችላል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና በርካታ ባለስልጣናት ግን፤ የጄነራሉ ዘመቻ ከመፈንቅለ መንግስት ተለይቶ አይታይም ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በትሪፖሊ ዙሪያ የሰፈሩ ታጣቂ ቡድኖች ወደ ዋና ከተማዋ በመግባት የጄነራሉን ጥቃት እንዲከላከሉ ጥሪ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የቤንጋዚ አየር ማረፊያ አገልግሎት እንዳይሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። የአገሪቱ መከላከያ ሃይል፤ በጡረተኛው ጄነራል ላይ እርምጃ እንዲወስድም በይፋ አዘዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ነገር ግን ትዕዛዛቸው አልሰራም። በሁለት ከተሞች የሚገኙ የአየር ሃይል ካምፖች በጡረተኛው ጄነራል ስር ለመመራት በመወሰናቸው፤ ሄሌኮፕተሮችና የጦር አውሮፕላኖች በቤንጋዚ ዘመቻ ላይ ተካፍለዋል። የመከላከያ ሃይል ወታደራዊ ፖሊስ አዛዥ በበኩላቸው፤ በጄነራል ሂፍጠር መሪነት የአገሪቱ መንግስት ከስልጣን መታገዱን በማወጅ፤ ጊዜያዊ መንግስት እንደሚመሰረት ገልፀዋል።
ለሁለት አመት ተረስተው የነበሩት ጡረተኛ ጄነራል፤ አሁን ወታደራዊ ልብስ ከነማዕረጋቸው ለብሰው በሳምንት ውስጥ ገናና ለመሆን ቢችሉም፤ የመንግስት ስልጣን ለመቆጣጠር አቅም ይኑራቸው አይኑራቸው ገና አልታወቀም። ለእርስ በርስ ጦርነት የሚሆን አቅም እንዳላቸው ግን አያጠራጥርም። ለዚህም ይመስላል፤ የአልጄሪያ መንግስት ልዩ ወታደራዊ ሃይል በመላክ ዲፕሎማቶቹንና ዜጎቹን ከሊቢያ ሲያስወጣ የሰነበተው። የሞሮኮ መንግስትም አምስት ሺ ወታደሮችን ወደ ድንበር አሰማርቷል። የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ፤ ዜጎቻቸውን በአፋጣኝ ለማስወጣት መጣደፍ ጀምረዋል። በአጠቃላይ በግጭት የምትታመሰው ሊቢያ፤ አሁን እንደገና መጨረሻው በማይታወቅ የጦርነት ውጥረት ውስጥ ገብታለች።

Read 1568 times