Saturday, 24 May 2014 15:04

የተከፈተው መስኮት

Written by  ድርሰት - H.H MUNRO (Saki) ትርጉም - ፈለቀ የማርውሃ አበበ filmethiopia@yahoo.com
Rate this item
(3 votes)

‹‹አክስቴ አሁን ትመጣለች›› አለች፤ ፍፁም ረጋ ያለችው የአስራ አምስት ዓመቷ ኮረዳ፡፡ ‹‹እስከዚያው ብቻዎትን እንዳይሆኑ ደግሞ ከእኔ ጋ ብንጨዋወት አይከፋም እ?››
እንግዳው፤ቅንነት ለተመላበት ንግግሯ አፀፋ የሚሆን ርዕሰ ጉዳይ ፈጥሮ እያወጉ ቢቆዩ፤ ወዲያውም አክስቷን በማስጠራት ከማስቸገር፤ በራሷ ጊዜ ተመልሳ እስክትመጣ ለመጠበቅም ጥሩ ይሆናል ሲል አሰበ፡፡ ወደዚህ የገጠር መንደር የመጣው፤ ስቃዩ እረፍት ለነሳው የነርቭ በሽታው መድኃኒት ፍለጋ ነበር፡፡ አሁን ግን፤ በዚህ ማንንም በማያውቅበት ስፍራ፤ የተመኘው እቅዱ መሳካቱን መጠራጠር ጀምሯል፡፡
‹‹ምን ሊፈጠር እንደሚችል አውቃለሁ!›› ብላው ነበር እህቱ፤ ወደ ገጠር ለመጓዝ አቅዶ ሲዘገጃጅ። ‹‹አንድም ሰው በማታውቅበት ሀገር፤ በባዳ ተከብበህ፤ የሚያናግርህ ፍጡር እንኳ አጥተህ፤ ይኼ ቁም ስቅልህን የሚሳይህ የነርቭ በሽታህ ባይተዋርነት ተጨምሮበት የባሰውን አንዘርዝሮ ነው የሚደፋህ!... ስለዚህ፤ እዚያ ስኖር ከምቀርባቸው ሰዎች ላንዳንዶቹም ቢሆን የአደራ ደብዳቤ ፅፌልህ እሱን ይዘህ ብትሄድ ነው የሚሻለው፡፡ አ…ዎ! መቸም እኔ እስከማውቃቸው፤ ድረስ በዚያ ከሚኖሩት ሰዎች መሀል ጥሩ ጥሩ ሰዎች አሉ፡፡››
እንግዳው፤ አሁን ቤቷ ውስጥ ቁጭ ብሎ የሚጠብቃትና እህቱ የአደራ ደብዳቤ ከፃፈችላቸው የመንደሩ ነዋሪዎች አንዷ የሆነችው ሴትም፤ ከነዚሁ ጥሩ ጥሩ ከተባሉት ሰዎች መካከል የምትመደብ ስለመሆኗ እርግጠኛ ሆኗል፡፡
‹‹በዚህ መንደር የሚኖሩ ብዙ ሰዎችን ያውቃሉ?›› አለችው የሴትዮዋ የእህት ልጅ፤ ለረዥም ሰዓት የነገሰውን ፀጥታ ለመስበር፡፡
‹‹ኧረ ማንንም! አንድ ብቻ!›› አለ እንግዳው ‹‹እርሷም እህቴ ናት፡፡› እህቴም ብትሆን አሁን ከተማ ነው የምትኖረው፡፡ ከአምስት አመት በፊት ግን እዚህ ነበረች፡፡ እናም አሁን ስመጣ፤ እዚህ ስትኖር በቅርበት ታውቃቸው ለነበሩ ሰዎች የአደራ ደብዳቤ ፅፋ…እሱን …አስይዛ…ነው የ.ላ.ከ.ች.ኝ፡፡››
የንግግሩ መጨረሻ አሳዛኝ ቅላፄ ነበረው፡፡
‹‹እንዲያ ከሆነማ ስለ አክስቴም ምንም ነገር አያውቁም ማለት‘ኮ ነው እ?›› አለች ረጋ ያለችዋ ጉብል፡፡
‹‹ከስምና አድራሻዋ በቀር አዎ›› አረጋገጠላት እንግዳው፡፡ አክስትየው ባለትዳር ሴት ልትሆን እንደምትችል ገመተ፡፡ ምናልባትም ባሏ የሞተባት ሴት፡፡ ግን ደሞ ላይሆንም ይችላል፤ በቤቱ ውስጥ የአባወራ አልባሳት ይታያሉ፡፡
‹‹አክስቴ፤ መከራ የመጣባት የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነበር፡፡ የእርስዎ እህት ከዚህ ወደ ከተማ ከሄዱ ከሁለት አመት በኋላ ማለት ነው፡፡››
‹‹የምን መከራ በሞትኩት?!›› አለ እንግዳው፡፡ በዚህ ሰላማዊ የገጠር ቀዬ፤ መከራ ምን ቢከብድ፤ በእኛ በከተማ ሰዎች ላይ የሚፈራረቀውን ያህል አይሆንም፤ ብሎ እየገመተ፡፡
‹‹መቼም እንዲህ ሥጋና አጥንትን በሚሰረስር የክረምት ቁር ይህን መስኮት ክፍቱን መተዋችንን ሲያዩ ሳይገረሙ አልቀረም፡፡›› አለችው የተረጋጋችዋ ትሁት፤ እጇን ዘርግታ፤ ልክ እንደ በር ተበርግዶ ክፍቱን የተተወውን፤ ከቤቱ ባሻገር ያለውን የለምለም ሳር ሜዳ በሩቁ የሚያሳየውን ሰፊ መስኮት እየጠቆመችው፡፡
‹‹አዎን…እሱስ ልክ ነሽ… ክረምቱ አውሎ ነፋስና ወጨፎ የቀላቀለ ዝናብ አለው፤ በጣምም ይበርዳል!›› አለ እንግዳው፡፡ ‹‹ግን ያልገባኝ ነገር፤ የመስኮቱ ክፍቱን መተው አክስትሽ ላይ ከደረሰው መከራ ጋር ምን እንደሚያገናኘው ነው?››
‹‹ልክ የዛሬ ሦስት አመት፤ የአክስቴ ባልና ሁለቱ ወንድሞቿ ለአደን ሲወጡ፡፡ ከዚህ መስኮት ስር ቆማ ነበር እርቀው ሲሄዱ በአይኗ የሸኘቻቸው፤ እናም አልተመለሱም፡፡ እንደወጡ ቀሩ፡፡ ለአደን ወደሚሰማሩበት ጥቅጥቅ ያለ ደን ለመድረስ የገጠሩን የድጥ መንገድ እያቋረጡ ሳለ፤ ሦስቱም ባንድ ላይ በአንድ ጥልቅ ማጥ ውስጥ ሰምጠው ቀሩ! ማጥ ዋጣቸው! አዩ እንግዲህ በዚያ ክረምት ብዙ ዘንቦ ነበርና፣ በሌሎች ክረምቶች ሲመላለሱ የኖሩባቸው ደረቅ ስፍራዎች ሁሉ ያለወትሯቸው በውኃና ደለል ተሞልተው፤ የላይኛው ሽፋናቸው ብቻ ርጥበቱ በነፋስ ተመጥጦ የደረቀ መስሎ ይታይ ነበር፡፡ ሬሳቸውም አልተገኘም፡፡ ከሁሉ የሚያሰቅቀውም ደግሞ ይኼ ነው፡፡›› ልጅቱ፤ ይኼን የሰቆቃ ታሪክ ስትተርክ፤ እስካሁን የነበራት መረጋጋትና የልጅነት ባህርይ ሁሉ ከፊቷ ላይ በንኖ ጠፍቶ፤ የአዋቂ ሰው ባህርይ ተላብሳ በፅኑ እየቆዘመች ነበር፡፡
‹‹ሌት ተቀን በሀዘን ተቆራምዳ የምትብከነከነው ምስኪኗ አክስቴ ታዲያ፤ ‹አንድ ቀን ከሄዱበት ተመልሰው ይመጡ ይሆናል› ብላ ተስፋ ታደርጋለች። ‹አንድ ቀን፤ እንደወትሯቸው፤ ግዳይ ጥለው ሲመጡ እንደሚደርጉት፤ ከማዶ ከጉብታው ማሳበሪያ ጀምረው እየፎከሩና እያቅራሩ፤ በኩራት እየተንጎማለሉ፤ ተከትሏቸው ሄዶ ከቀረው ዥንጉርጉር ውሻ ጋር መንደሩን አቋርጠው ወደ ቤት ሲቃረቡ፤ እኛም ስናደርገው እንደኖርነው፤ ተሯሩጠን መጥተን፤ በዚሁ መስኮት አሻግረን እናያቸዋለን› ትላለች፡፡ እናም ይኼ መስኮት፤ በየቀኑ ሳይዘጋ፤ ከንጋት አንስቶ እርጭ ያለ አስፈሪ ጭለማ እስከሚነግስበት እኩለ ሌሊት ድረስ እንዲሁ አፉ እንደተንቦረቀቀ የሚቆየው በዚህ የተነሳ ነው፡፡የፈረደባት አክስቴ፤ እየደጋገመች፤ ባሏ ነጭ የጥጥ ካፖርቱን እንዴት ክንዱ ላይ ጣል እንዳደረገ፤እንደ አይኗ ብሌን የምትሳሳለት ትንሽዬው ወንድሟ፤ ዘወትር ‹ተው! የነርቭ በሽታዬን ትቀሰቅስብኛለህ!› እያለች ስትቆጣው፤ ሆን ብሎ እሷን ለማናደድ የሚዘፍነውን ዘፈን እንዴት ጮክ ብሎ ያንጎራጉር እንደነበር፤ በቃ፤ ወደ አደን ሲወጡ የነበራቸውን አኳኋን አንድም ሳታስቀር እየዘረዘረች ሳትሰለች ታወራልኛለች፡፡ እና ታዲያ አሁን አሁን በእኔም ላይ ምን እየተፈጠረብኝ እንዳለ ልንገርዎት? ልክ እንዲህ ፀጥ ባለ አመሻሽ ላይ ብቻዬን ስሆን፤ ‹እውነትም፤ ተመልሰው ሲመጡ፤ በዚህ ሰፊ ክፍት መስኮት በሩቁ አያቸው ይሆናል‘ኮ!› የሚል፤ ዝብርቅርቅ ያለ የማይጨበጥ ሀሳብ ይሰፍርብኝ ጀምሯል፡፡ እናልዎት…››
ልጅቱ፤ በድንገት ንግግሯን አቋርጣ መንቀጥቀጥ ያዘች፡፡ አክስቷ፤  በቤቱ የጓሮ በር በኩል እየተጣደፈች ገብታ፤ እስካሁን ስለመዘግየቷ ይቅርታ ጠይቃው ስታናግረው፤ በጭንቀት የተለጎመው እንግዳ ውጥረቱ ረገብ አለለት፡፡
‹‹የኔ ነገር! ጠፋሁ አይደል፤ ቢጡ ስላለች ብቻህን አልቦዘንክም መቸም፤ አይደል?››
‹‹እ አዎን፤ በጣም ጨዋታ አዋቂ ልጅ ነች!›› አለ እንግዳው፡፡
‹‹ይኼ መስኮት ክፍቱን መሆኑስ አውኮህ ይሆን?›› አለች፤ ሴትዮዋ ፈገግ ብላ፡፡ ‹‹ባለቤቴና ሁለቱ ወንድሞቼ ለአደን ከሄዱበት ይመጣሉ፡፡ ዛሬ፤ ማዶ ማጡ አካባቢ ካለው ደን ጅግራና ቆቅ ሲያድኑ ነው የሚውሉ፡፡ እንግዲህ በጭቃ ተልኮስኩሰው መጥተው ምንጣፌን ሊያቆሽሹብኝ ነው ኤዲያ! እንዲያው ወንዶች ስትባሉ፤ እኛ ሴቶች ምን ያህል ለፍተን ቤት እንደምናፀዳ አይገባችሁምኮ! አይደል?››
ሴትየዋ፤ ስለ አደን ውሎ፤ በተለይ ቆቅና ጅግራን ማደን ስላለው አስቸጋሪ ውጣ ውረድ እየተፍነከነከች ያለማቋረጥ አወራች፡፡ ለእንግዳው ግን፤ የሚሰማው ነገር ሁሉ ፍርሀት የሚነዛ ጉዳይ ሆኖበታል፡፡ አቅሙ በፈቀደው መጠን፤ ርዕሰ ጉዳዩን ወደ ሌላ ሰላማዊ ወግ ለማስቀየር ቢሞክርም እንዳሰበው አልተሳካለትም። አንድ በደንብ የተረዳው ነገር ቢኖር፤ ይህቺ በአደራ ደብዳቤ የተቀበለችው ሴትዮ፤ ለእሱ ትኩረት ሰጥታ በእንግድነት ከማስተናገድ ይልቅ፤ ቀልቧ የተጠመደው፤ አስር ጊዜ ቀና እያለች በምታጨነቁርበት መስኮት ባሻገር በሚታየው ሰፊ የሳር ሜዳ ላይ መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ባለ የሀዘን ድባብ ባጠላበት ስፍራ በእንግድነት መገኘቱ የዕድለቢስነት ስሜትን ያጭራል፡፡
‹‹ሀኪሞቹ፤ ተሰብስበው በተስማሙት መሰረት፤ የፃፉልኝ ትዕዛዝ፤ ሙሉ ለሙሉ እረፍት ማድረግ እንዳለብኝ የሚያስገድድ ነው፡፡ ማለትም፤ አንዳችም አይነት ጭንቀት፣ ሁከትና ግርግር ካለበት አካባቢ ገለል ብዬ፤ እንዲሁም ከማንኛውም አይነት ከበድ ያለ የሰውነት እንቅስቃሴን ከሚጠይቅ ተግባር ሁሉ ተቆጥቤ እንድቆይ ነው ያሳሰቡኝ፡፡›› አለ ሰውዬው፤ ማንኛውም እንደሱ ያለ እንግዳ ሰው፤ የበሽታው መንስኤ ታውቆለት መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ማድረግ የሚጠበቅበትን፤ የህመሙን ደረጃ ተንትኖ ለማስረዳት፡፡ ‹‹አመጋገቤን በተመለከተ ግን፤ ሁሉም ሀኪሞች ገና በአንድ አይነት ውሳኔ ላይ አልደረሱም›› ሲል ቀጠለ፡፡
‹‹ገና?›› አለች ሴትዮዋ በተሰላቸ ድምፅ፡፡ ወዲያውም በፈገግታ ተሞልታና ቀልቧን ገዝታ ሙሉ ለሙሉ ወደ እሱ ዞረች፡፡ ግን እርሱ ለተናገረው ምላሽ ልትሰጠው አልነበረም፡፡
‹‹ይኸዋ መጡ!!›› ብላ ጮኸች፡፡ ‹‹ልክ በእራት ሰአት! እንዴት በጭቃ እንደቦኩ እዩዋቸው እስቲ በሞቴ?! መቃብር ፈንቅለው የወጡ አስከሬኖች አይመስሉም እናንተዬ?››
እንግዳው፤ በሽብር እየተንዘፈዘፈ፤ የሚያየው ነገር ሁሉ የፈጠረበትን ጥልቅ ሀዘን እንድታውቅለት ለማሳየት ቀ….ስ ብሎ ወደ ትንሷ ጉብል ዞር አለ። ልጅቱ ግን፤ በፍርሀት ተጎልጉለው የወጡ በሚመስሉት አይኖቿ፤ በተከፈተው መስኮት አሻግራ እያየች ነበር፡፡ እንግዳው፤ በተቀመጠበት ብርክ እየናጠው፤ ተንጠራርቶ፤ ሴትዮዪቱና ልጅቷ ወደሚያዩበት አቅጣጫ እሱም አብሯቸው አፈጠጠ።
ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ በጠቆረው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሦስት፤ የሚንቀሳቀስ ጥላ መሳይ ገፅታዎች፤ ባሻገር የሚታየውን የለምለም ሳር ሜዳ እያቋረጡ፤ በቀጥታ ወደ ሰፊው መስኮት አቅጣጫ እየመጡ ነው፡፡ ሦስቱም፤ በየትከሻቸው ላይ ጠብመንጃ አንግተዋል፡፡ ከመካከላቸውም አንዱ፤ ነጭ የጥጥ ካፖርት ትከሻው ላይ ጣል አድርጓል። ለሀጩን የሚያዝረበርብ ዥንጉርጉር ውሻ፤ እያለከለከ እግር እግራቸው ስር ይከተላቸዋል፡፡ ሦስቱም በፀጥታ እስከ መኖሪያ ቤቱ ድረስ ከመጡ በኋላ፤ ልክ ወደ መስኮቱ ደፍ ሲጠጉ፤የጎረምሳው ጎርናና ድምፅ  የጨለማውን እርጭታ ጮክ ባለ ዘፈኑ ደበላለቀው፡፡
እንግዳው፤ አውልቆ በእጁ ይዞት የነበረውን ባርኔጣውን በሀይል ጨምድዶ ይዞ ድንገት ብድግ አለና እየተደነባበረ የቤቱን ዋና መግቢያ በር በርግዶ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ በአየር ላይ የበረረ እንጂ በእግሩ የሚሮጥ አይመስልም ነበር፡፡
‹‹ቤት እንደ ምን አመሻችሁ? እነሆኝ መጣንልሽ ውዴ!›› አለ ከሦስቱ በእድሜ ጠና ያለው፤ ነጭ የጥጥ ካፖርቱን ትከሻው ላይ ጣል እንዳደረገ፤ በመስኮቱ በኩል ብቅ ብሎ ከወገቡ በላይ እየታየ፡፡ ‹‹የረገጥነው ሁሉ ድጥ ብቻ ነበር፡፡ ገላጣ ገላጣው በነፋስ መድረቅ እየጀመረ ነው ብለን ስንረግጠው እያንሸራተተ ዱብ!... ማነው እሱ አሁን ከቤት ወጥቶ ሲሮጥ ያየነው ሰው?››
‹‹በጣም ግራ የሚያጋባ እንግዳ!›› አለች ሴትዮዋ ለባሏ፡፡ ‹‹ያደራ ደብዳቤ ይዞ ቤታችን ከደረሰ ጀምሮ የተናገረው አንድ ነገር ቢኖር፤ ያደረበት በሽታ እንዴት እንደሚያደርገው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ልክ እናንተ ስትመጡ፤ ደህና እደሩም ሆነ ይቅርታ መሄዴ ነው ሳይል ድንገት ብርግግ ብሎ ሩጫውን አስነካው!ልክ እኮ ጣዕረ ሞት ያየ ነው የሚመስለው አሯሯጡ! ሆ!››
‹‹እኔ እንደሚመስለኝ ውሻውን ስላየ ነው›› አለች ረጋ ያለችዋ የሴትዮዋ የእህት ልጅ፡፡ ‹‹የውሻ ዘር የሚባል ሁሉ ክፉኛ እንደሚያስፈራው ሲነግረኝ ነበር። አንድ ምሽት ብቻውን ጭር ያለ የመቃብር ስፍራ ሲያቋርጥ፤ የውሾች መንጋ እጅብ ብለው ጥርሳቸውን እያፋጩ ሊነክሱት ኋላ ኋላው ሲከተሉት የሞት ሞቱን አመለጣቸው! ከእነሱ ለመሸሽ ሲሮጥ፤ ወዲህም ወዲያም እሚሸሸግበት ጥግ አጥቶ፤ ‹በቃ ዛሬ አለቀልኝ፤ ስጋዬን ቦጫጭቀው፣ አጥንቴን ቆረጣጥመው፣ ቅርጥፍጥፍ አድርገው አነከቱኝ!› ብሎ በሲቃ ሰቆቃ እያነባ፤ትረፍ ሲለው፤ፊት ለፊቱ አዲስ የተቆፈረ ትኩስ የቀብር ጉርጓድ አጋጠመውና ዘልሎ እዛ ውስጥ ገባ! ከዚያ በኋላ፤ እሱ ከታች ጠባቡ ጉርጓድ ውስጥ ሆኖ በስቃይ እየተወራጨ፤ ውሾቹ በጉርጓዱ አፍ ዙሪያ ከብበው ላዩ ላይ ሲጮኹና ላሀጫቸውን እያዝረበረቡ ሲያላዝኑበት መንጋት አይቀርም ነጋ! ነው ያለኝ፡፡ ታዲያ እንግዲህ አንድ ሰው ይህን አይነት መከራ ገጥሞት ለነርቭ በሽታ አይደለም ከዚያስ ለባሰ ልክፍት ቢጋለጥ ምን ይደንቃል?››
ቢጡ፤አንድን ታሪክ እሷ በፈለገችው መንገድ ቅልብጭ አድርጋ በማቅረብና በማስደመም በእጅጉ የተካነች ጉብል ናት - ፍፁም ረጋ ያለች ጨዋ፡፡

Read 3388 times