Print this page
Saturday, 24 May 2014 14:51

ኢትዮጵያዊው ዶ/ር በአሜሪካ “የላቀ አገልግሎት ሽልማት” ተቀበሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በአሜሪካ ፊላዴልፊያ ውስጥ በሚገኘው የቴምፕል ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያዊው ዶክተር ኤልያስ ሲራጅ፣ በሙያቸው ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ከአሜሪካ ክሊኒካል ኢንዶክሪኖሎጂስትስ ማህበር የላቀ አገልግሎት ሽልማት አገኙ፡፡
በኢንዶክሪን ህክምናና በአጠቃላይ ጤና መስፋፋት ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱና በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገራት የሚገኙ በቂ የጤና ግልጋሎት ያላገኙ ህዝቦችን በአመራር ሰጪነት፣ በማያሰልስ ቁርጠኝነት፣ በራዕይ፣ በፈጠራና ተጽዕኖ በሚፈጥር መልኩ በማገልገል፣ ብቃታቸውን ላሳዩ የተመረጡ ባለሙያዎች የሚሰጠው ይህ ሽልማት፣ ባለፈው ሳምንት ላስ ቬጋስ ውስጥ ለዶክተር ኤልያስ ተበርክቷል፡፡
“በቂ የህክምና ግልጋሎት ያላገኙ በርካታ ዜጎች ካሉባት አገር እንደመውጣቴ፣ በቻልኩት መንገድ ሁሉ ህብረተሰቡን የማገልገል ሃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል። ማህበሩ በአገሬ በኢትዮጵያና በአሜሪካ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ላከናወንኳቸው ተግባራት እውቅና ሰጥቶ ሽልማቱን ስላበረከተልኝ ክብርና ኩራት ይሰማኛል።” ብለዋል ዶ/ር ኤልያስ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ፡፡ ዶ/ር ኤልያስ የህክምና ተማሪዎችን፣ ማህበረሰቡንና በኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት የህክምና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነበሩ ተለማማጆችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን ማከናወናቸውና በአገሪቱ የመጀመሪያውን የኢንዶክሪኖሎጂ ስልጠና ፕሮግራም በማስጀመር ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ይነገራል፡፡  
በአሁኑ ሰዓት በቴምፕል ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት በመምህርነትና በዩኒቨርሲቲው የኢንዶክሪኖሎጂ ፌሎውሺፕና የዲያቤቲስ ፕሮግራሞች ዳይሬክተርነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶ/ር  ኤልያስ፤ ለታካሚዎች ነጻ እንክብካቤ በመስጠት፣ በኢትዮጵያ ያለውን የስኳር በሽታ በተመለከተ ጉልህ ምርምር በማካሄድና በኢትዮጵያና በአሜሪካ የህክምና ተቋማትና ባለሙያዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚሰሩ ድርጅቶችን በመምራት ይታወቃሉ፡፡
በጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከጨረሱ በኋላ፣ ነጻ የምርምርና የስልጠና ዕድል አግኝተው ወደ ጀርመን በማምራት ሊፕዚንግ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉት ዶ/ሩ፤ በመቀጠልም ወደ አሜሪካ በማቅናት በክሌቭላንድ ክሊኒክ በተግባር የታገዘ ስልጠና ወስደዋል፡፡
በኢንዶክሪኖሎጂና የውስጥ ደዌ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው እኒህ ዶ/ር፣ በተለያዩ የሙያ ማህበራት ውስጥ በአባልነትና በቦርድ አባልነት ንቁ ተሳትፎ በማድረግና በተለያዩ አለማቀፍ መድረኮች ላይ እየተጋበዙ ሙያዊ ንግግሮችን በማቅረብ ይታወቃሉ። በርካታ የህክምና ምርምር ጽሁፎችን ለህትመት ያበቁ ሲሆን በቴምፕል ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በመምህርነት ባበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ የመምህርነት ሽልማት ከዩኒቨርሲቲው ተቀብለዋል፡፡

Read 2883 times
Administrator

Latest from Administrator