Saturday, 24 May 2014 14:30

የጎንደር ገጠመኞቼ

Written by  ከጉማራ ዙምራ
Rate this item
(7 votes)

ክፍል ሁለት
“አቅላይ ሰፈር”፤ “ቋያ” “እሳቱ ሰ” እና “ቤርሙዳ”

ውድ አንባቢያን:- ባለፈው ሳምንት ጽሁፌ ለመስክ ሥራ ወደ ጎንደር በተጓዝኩ ጊዘዜ ያስደመሙኝን ገጠመኞችና ስለደብረ ታቦር ከተማ አንዳንድ ነገሮችን ጣጥፌ የነበረ ሲሆን በዛሬው ጽሁፌ ቀጣዩን ክፍል አስነብባችኋለሁ፡፡
ወደ ፍሬ ነገሬ ከመግባቴ በፊት ግን እስኪ እዚያው ደብረ ታቦር ስለገጠመኝ አስቂኝ ነገር አንድ ልንገራችሁ፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ከስራ ባልደረባዬ ጋር ሻይ ቡና ስንል በሞባይል ያነሳችውን ፎቶዬን አሳየችኝ፡፡
“ኦው! በጣም ያምራል ለፌስቡኬ (ፌዝቡክ) ይሆነኛል እባክሽ… በብሉቱዝ ላኪልኝ!?”
“እሺ፤ ብሉቱዝህን ክፈት?”
“ተከፍቷል ሰርች አርጊው?”
“ስልክህ ቴክኖ ነው እንዴ?”
“ኧረ በፍፁም ሳምሰንግ ነው”
“ታዲያ ፈልግ ስለው እኮ ወደ ስድስት ቴክኖ ነው ተከታትሎ የገባው፡፡ ቴክኖ! ቴክኖ! ቴክኖ! ቴክኖ! ቴክኖ!ቴክኖ!”
ቀና ብለን አካባቢውን ስንቃኝ ካፌ ውስጥ ካሉት ተጠቃሚዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ስልካቸውን ይጎረጉራሉ፡፡ ግማሹ ጌም ቢጤ ይጫወታል፣ ግማሹ ጥሪ ያስተላልፋል/ይቀበላል፤ እኩሉ ደግሞ የጎንደር ዘፈን ያለጆሮ ማዳመጫ ከፍቶ እሽክም….. እሽክም…. እሽክም ይላል፡፡ የቴክኖ ስልክ በአዲስ አበባ ገበያ ከሌሎች ስልክ አምራቾች ጋር እንዴት ይፎካከር ይሆን? የሚል ጥያቄ ሁሌም በአእምሮዬ ይመላለስብኝ ነበር፡፡ ለካስ እነ አጅሬ የት እንደሚሸጥ በደንብ አውቀውበታል፡፡ ይመቻችሁ ቴክኖዎች!! (ይሄ ግን አደራ - በማስታወቂያነት እንዳይወሰድብኝ።)
የስልክ ነገር ከተነሳ ግን አዲስ አበባስ ቢሆን እንደው በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ ያለ ጆሮ-ማዳመጫ ሁከት የሚፈጥሩ ሞልተው የለም እንዴ! አንዱ ለመስማት እንኳን ሰቅጣጭ በሆነ ጢዝትዝታ ስፖርት ላይ ስልኩን ጥዶ፣ ስለ ጆዜ ሞሪኖና አርሰን ቬንገር ንትርክ ይሰማል፤ ሌላው መዝሙር ቢጤ ከፍቶ “ሰረገላዎችህ የእሳት ናቸው” ይኮመኩማል፤ ደግሞ ፍሪክ መሳዩ “የም ዮ! የም ዋ!”  እያዘፈነ ሲሄድ፣ የተሳፋሪ ያለመረበሽ መብት በትንሹ እንኳን ሳያሳስባቸው ሲቀር ይገርመኛል፡፡ ጭራሽ ከሰሞኑ ደግሞ አንድ የሞባይል ስልክ ማስታወቂያ “እገሌ ሞባይል ዋዛ እንዳይመስልዎት … ሙዚቃ ወይም ራዲዮ ያለ ጆሮ ማዳመጫ የሚያደምጡበት” ሲል ነበር፡፡ (ያለ ጆሮ ቢል ልዩ ፈጠራ ይሆን ነበር!) እሱ ስልክ ሲመጣ ደግሞ አምላኬ ምን ታደርገን ይሆን?! ማለቴ አልቀረም፡፡
ወደ ገደለው ጉዳዬ ስሻገር፤ የጥናታችን ማጠንጠኛው ኤችአይቪኤድስ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ አንዱ ክፍል የሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡ ከምናከናውናቸው ተግባራት ውስጥም የከተማዋ ሴተኛ አዳሪዎችን ቁጥር መገመት፤ ዓይነታቸውን መለየትና፤ በብዛት ሰፍረው የሚገኙባቸውን ቦታዎች (ሆትስፖትስ) ማወቅ ይገኙበታል፡፡
አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማዘጋጀት ከከተማው የጤና ባለሙያ ጋር ውይይት በምናደርግበት ወቅት ግን፤ አንድ አስቂኝና አስገራሚ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
“በከተማው ውስጥ ስንት ‘ሆትስፖቶች’ አሉ?”
ትንሽ አሰበና፤ “አራት ናቸው”
“ማን ማን ይባላሉ?”
“አንዱ ‘አቅላይሰፈር’፣ ሁለተኛው ‘ቋያ’፤ ሶስተኛው ‘እሳቱ ሰ’ እና አራተኛው ‘ቤርሙዳ’ ይባላሉ፡፡”
በስያሜዎቹ ፈገግ ተሰኘሁ፤ በህዝቡ ቅኔ ዘራፊነት ተደነቅሁ፡፡ ነገር ግን ከዚሁ ዓይነት ተመሳሳይ ስራ ጋር በተያያዘ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ተዘዋውሬ ለመታዘብ እንደሞከርኩት፣ ከእምነትና ባህል አንፃር የሴተኛ አዳሪዎችን ተግባር በይፋ እውቅና ሰጥቶ፤ ተቀብሎና የኔ ብሎ የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ባላገኝም ወይም ደግሞ ድርጊቱን የሚኮንን ባይታጣም እንደ ደብረታቦር ከተማ ህዝብ አይነት ለሆትስፖቱ አስከፊ ስያሜዎች የሰጠና ለሴተኛ አዳሪዎች እጅግ የተሳሳተ እይታ ያለው ህዝብ ይኖር ይሆን? የሚል መጨነቅ መጠበብ ውስጥ ከተተኝ፡፡ እኔም ልሁን እነሱ የአስተሳሰብ ብዥታ አንዳችን ላይ አለ፡፡ አንባብያን እንዲረዱልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣ ተግባሩ ሊበረታታ ይገባዋል ወይም እንደ አንድ የስራ መስክ ሴቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሳተፉበት ይገባል እያልኩ አለመሆኔን ነው፡፡ ነገር ግን ሴቶች ወደ ሴተኛ አዳሪነት ስራ የሚገቡት በጥጋብ ወይም የጠና የዘማዊነትና ሴሰኛነት ፍቅር ኖሮባቸው ነው ከሚል ድምዳሜ ብቻ ተነስቶ፣ ተግባሩን የሀጢያቶች ሁሉ ስር አድርጎ ማቅረብና መፍረድ ተገቢ መስሎ ስለማይሰማኝ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አድልዎና ማግለሉ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች ተባብሶም ስለሚታይ ጭምር ነው እንዲህ ያልኩት፡፡
በግብረ ሰዶማዊነቱም ዙሪያስ ቢሆን ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የኃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ያገባናል ባዮች፣ ግብረሰዶማዊነትን እናወግዛለን! ድርጊታቸውንም እንቃወማለን ከማለት ባለፈ ግብረ ሰዶማዊነት በሀገራችን ውስጥ ምን ህል ስር ሰዶ ይገኛል? ቁጥሩ እየጨመረ ወይስ እየቀነሰ ነው? እየጨመረ ከሆነስ እንዴት? ለምን? ሰዎች ግብረ ሰዶማዊ ለምን ይሆናሉ? የስነ ልቦና ተመራማሪዎችና ሳይንስ ምን ይላሉ? ተታለውና ተገደው በመደፈራቸው ምክንያት ግብረ ሰዶማዊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዴት እንታደጋቸው? (በከተማችን ውስጥ በመምህራኖቻቸውና በርዕሰ መምህራቸው የተደፈሩትንና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ህፃናትን ጉዳይ ልብ ይሏል!) የኃይማኖት ተቋማት፤ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት፣ በስነ ምግባርና በሞራል የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ምን እየሰሩ ነበር? ወደፊትስ ምን ሊሰሩ አቅደዋል?
ለእነዚህና የመሳሰሉት ቁልፍ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሳንሻ ወይም ሳንተጋ ተግባሩን ብቻ መቃወም ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡ ህብረተሰቡን ስለድርጊቱ አስከፊነትና መነሻ ምክንያት ካላስተማርነውና ካላነቃነው ችግሩ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ አይመስለኝም፡፡  በጉዳዩ ላይ ገንቢ ሃሳቦችን ለመቀበል እየፈቀድኩ፣ የጎንደር ገጠመኞቼን ለዛሬ ልቋጭ፡፡  

Read 10161 times