Saturday, 24 May 2014 14:14

ከባንኩ ደንበኞች ግማሾቹ የሙስና አሰራር ገጥሞናል አሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

የ99 ጄነሬተሮች ግዢ ጨረታ፣ በፀረ ሙስና ባይስተካከል 6.4ሚ. ብር ይባክን ነበር

ከኢትዮጵያ የቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ደንበኞች መካከል ግማሽ ያህሉ የሙስና ብልሹ አስራር እንዳጋጠማቸው የተናገሩ ሲሆን፤ የብድር ጠያቂዎች ምላሽ ለማግኘት አንድ አመት ያህል እንደሚጉላሉ ገለፁ፡፡ ባንኩ 99 ጄኔሬተሮችን ለመግዛት ባወጣው ጨረታ ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበ ተወዳዳሪ አላግባብ አሸናፊ እንዲሆን ተደርጓል በማለት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለፓርላማ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ጨረታው ተሰርዞ በመመሪያ መሰረት በድጋሚ እንዲካሄድ መደረጉን የገለፀው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ ጨረታው በመስተካከሉ 6.4 ሚ. ብር ከብክነት ድኗል ብሏል፡፡
የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኤጀንሲ ባደረገው ጥናት፤ ባንኩ በሙስና ብልሹ አሰራር እንደተጠቃ ያመለክታል፡፡ ከባንኩ ደንበኞች መካከል 47 በመቶ ያህሉ የሙስና ብልሹ አሰራሮች እንዳጋጠሟቸው ገልፀዋል ይላል፤ ጥናቱ። ደንበኞች እንደገለፁት፤ በአብዛኛው ከፍተኛና እጅግ ከፍተኛ የሙስና ብልሹ አሰራር ነው የሚያጋጥማቸው፡፡
የባንኩ አሰራር የተንዛዛና ደንበኞችን በአክብሮት የማያስተናግድ መሆኑ ለብልሹ የሙስና አሰራር እንዳጋለጠው የሚናገሩ ደንበኞች፤ ብድር ለመጠየቅ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በግልጽ አይነገረንም ብለዋል፡፡ “ያላሟላኸው ነገር አለ” ተብለን ስንሟላ፤ ከወር በኋላ እንደገና “የጐደለ ነገር አለ” ይሉናል ብለዋል፤ ደንበኞች፡፡
ስርዓት በሌለው በዚህ አሰራር፣ የብድር ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት አንድ አመት ገደማ እንደሚፈጅ ጥናቱ ገልጿል።    
የብድር ዋስትና የሚሆን ንብረት ለማስመዝገብና በመሃንዲሶች የንብረት ዋጋ ለማስገመትም ከአራት ወራት በላይ እንደሚፈጅ ጥናቱ ጠቅሶ፤ ገማች መሃንዲሶች ከዋና መስሪያ ቤት እየተላኩ የሚሰሩ መሆናቸው ስራውን ያጓትታል ብሏል፡፡
የባንኩን ደንበኞች እንደለማኝ የሚቆጥሩ ገማች መሃንዲሶች እንዳሉ የተናገሩ ደንበኞች፤ ለአንድ ንብረት የሚሰጡት የዋጋ ግምት እጅግ የተራራቀ በመሆኑ  ለሙስና የተጋለጠ ነው ብለዋል፡፡
ለአስቸኳይ ወይም እንደ እርሻ ለመሳሰሉ ወቅታዊ ስራዎች ብድር የሚጠይቁ ደንበኞች አመት ሙሉ ይጉላላሉ ብለዋል - ደንበኞች፡፡
የዋስትና ንብረት አስይዘው ብድር ለመስጠት እንደጠየቁ የተናገሩ የሰሊጥ ነጋዴዎች፤ በመጋዘን የሰሊጥ ክምችት ማሳየት አለባችሁ መባላቸውን ይገልፃሉ፡፡
ነገር ግን፣ በቡናና በሰሊጥ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች በመጋዘን ውስጥ ምርት ማከማቸት በህግ አይፈቀድላቸውም ያሉት እነዚሁ ደንበኞች፤ ምርታቸውን በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን የማስገባት ግዴታ እንዳለባቸው በመግለፅ፣ የባንኩ አሰራር እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡
በ75 ገፆች የቀረበው የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ጥናት፤ የባንኩን አንዳንድ የመሻሻል ምልክቶችንም ጠቃቅሷል፡፡ ባንኩ በእድሜ አንጋፋ ቢሆንም ለረዥም አመታት ያለ እድገት ወደኋላ መቅረቱን ጥናቱ ገልፆ፤ ባለፉት ሦስት አመታት የእድገት ጅምሮች ታይተዋል ብሏል፡፡
በሦስት ዓመታት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከ35 ወደ 105 ያሳደገው ይሄው ባንክ፤ የአያስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር እጅግ ጥቂት ቢሆንም ከ150ሺ ወደ 200ሺ ከፍ አድርጓል፡፡  የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ 2.3 ቢሊዮን ወደ 4.6 ቢሊዮን፣ ጠቅላላ የብድር መጠኑ ከ1.6 ቢሊዮን ብር ወደ 2.4 ቢሊዮን መድረሱም ጥናቱ ጠቅሷል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የባንኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃ/ኢየሱስ በቀለ፤ ጥናቱ ገና እየተመረመረ በመሆኑ፣ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት እንደሚቸገሩ ገልፀዋል፡፡ የ99ኙን ጄኔሬተሮች ግዢ በተመለከተም፣ የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረበውን ሪፖርት፤ ገና እያጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  

Read 3604 times