Saturday, 24 May 2014 14:11

የአክሰስ ሪልስቴት ቤት ገዢዎች የመንግስትን ድጋፍ ተማፀኑ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

በሪል እስቴቱ የተገዙ የግንባታ ቦታዎችን ለመውረር የተዘጋጁትን ህገ ወጦች እንፋረዳለን ብለዋል

በግንባታ መዘግየት እንዲሁም ከደንበኞች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት እና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የአክሰስ ሪልስቴት መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከአገር ወጥተው አለመመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ መንግስት የግንባታ ቦታዎቹ ላይ ህገወጥ ወረራ እንዳይካሄድ መከላከል አለበት ሲሉ ቤት ገዢ ደንበኞች ጠየቁ፡፡
ቦሌ ፍሬንድሺፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ፊት ለፊት የባለ 14 ፎቅ ህንፃ መሰረት እንደተጀመረና መቶ ሚሊዮን ብር እንደወጣበት የገለፀው የቤት ገዢዎች ኮሚቴ፤ ህገ-ወጥ መሬት ወራሪዎች ከመቶ መኪና በላይ አፈር በመድፋት ቦታውን ከጥቅም ውጭ አድርገውብናል ብሏል የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አክሎግ ስዩም፣ ለፖሊስ አመልክተን ምላሽ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
ከአሜሪካ እንደመጡ የገለፁ የቤት ገዢዎች ተወካይ በበኩላቸው፤ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በቤት ሰራተኝነትና በሌሎች ዝቅተኛ ስራዎች ለፍተው ባጠራቀሙት ብር ከሪል ስቴቱ ቤት ለመግዛት ክፍያ መፈፀማቸውን ተናግረዋል፡፡
በእኛ ላይ የደረሰው ችግር አገሪቱንም ይጐዳል ያሉት እኚሁ ተወካይ፤ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህንን ችግር ሲሰሙ ወደ አገራቸው ተመልሰው የመስራት ፍላጐታቸው በፍርሃት ይሰናከላል ብለዋል፡፡
“የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መሞታቸው የተሰማን አሁን ነው” ካሉ በኋላ፤ መንግስት ለህልውናው ሲል  እልባት እንዲሰጠን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
በፍ/ቤት የተጀመረው ሂደት በአብዛኛው ቤቶቹን ወደ ሀራጅ ሽያጭ ስለሚወስድ በቤት ገዢዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት የኮሜቴው አባላት፣ አክሰስ ሪልስቴት ህልውናው እንዲቀጥልና ቤት ገዢዎችም እንዳይጐዱ የሚያስችል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በከተማዋ 20 ሽያጭ የተካሄደባቸውና ዘጠኝ ሽያጭ ያልተካሄደባቸው የሪልስቴቱ የግንባታ ቦታዎች መኖራቸውን የገለፀው ኮሚቴው፣ እነዚህን ቦታዎች ለመቀራመት የሚሞክሩ ህገወጦች ስጋት ሆነውብናል ብሏል፡፡
በአክሰስ ሪልስቴት ውስጥ ችግር ከተፈጠረ በኋላ በ1800 የአገር ውስጥና በ350 በውጭ የሚኖሩ ቤት ገዢዎች የኩባንያው ባለአክሲዮን በመሆን እንደ አዲስ ያዋቀሩት ሲሆን፤  ከ1.4ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀማቸውም ተገልጿል፡፡

Read 2441 times