Saturday, 24 May 2014 14:09

በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ኩባንያ ቁፋሮ ውሃ ተገኘ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(8 votes)

ሌላ ጉድጓድ መቆፈር እጀምራለሁ ብሏል
ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአለም አገራት በነዳጅ ፍለጋ ስራ ላይ የተሰማራው “ታሎው ኦይል” ኩባንያ፣ በደቡብ ኦሞ ቁፋሮ፣ የነዳጅ ሳይሆን የውሃ ክምችት ማግኘቱን ትናንት አስታወቀ፡፡
ዘ አይሪሽ ታይምስ እንደዘገበው፣ ኩባንያው “ሺመላ” በተባለ ቦታ፣ የእሳተ ጐመራ አለቶችን ጭምር በመቦርቦር 1,940 ሜትር ጥልቀት ድረስ በቁፋሮ ማካሄዱን ጠቅሶ፤ ከፍተኛ የውሃ ክምችት የያዘ የምድር ውስጥ ሃይቅ ማግኘቱን ገልጿል፡፡
ኩባንያው የነዳጅ ፍለጋ ቁፋሮው ስኬታማ ባይሆንም ተስፋ እንደማያስቆርጠው ገልጾ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረውን የነዳጅ ፍለጋ በመቀጠል  ‘ጋርዲም - አንድ’ የተባለ ሌላ አዲስ ጉድጓድ፣ በዚያው በደቡብ ኦሞ ራቅ ብሎ በሚገኝ ቦታ ቁፋሮ ለመጀመር መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ ኩባንያው በደቡብ ኦሞ አካባቢ ሲያከናውነው የቆየውን ሌላ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ ምንም አይነት ተጨባጭ ውጤት ባለማግኘቱ በዚህ አመት መጀመሪያ ማቋረጡንም ዘ አይሪሽ ታይምስ አስታውሷል፡፡
ታሎው ኦይል የ‘ሺመላ - አንድ’ ቁፋሮውን ያለስኬት ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ የኩባንያው የአክሲዮን ዋጋ በ1 ነጥብ 3 በመቶ መቀነሱ ተነግሯል፡፡
በደቡብ ኦሞ በሚደረገው የነዳጅ ፍለጋ፤ ታሎው ኦይል 50 በመቶ፣ አፍሪካ ኦይል ኮርፖሬሽን 30 በመቶ፣ ማራቶን ኦይል ኢትዮጵያ 20 በመቶ ድርሻ ይዘው በሽርክና እየሰሩ እንደሚገኙ ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡

Read 4423 times