Saturday, 17 May 2014 15:05

ሰብአዊነት-ሥራ-ፖለቲካ

Written by  ዳደ ደስታ
Rate this item
(1 Vote)

“ለደርግ ሆስፒታል፡ ወታደር ከበደ ጉነቲ ጉይሳ፤ ዕድሜ 40፣ ትውልድ ወለጋ - ጊምቢ፣ የተጎዳው ከወገብ በታች ብዙ ቦታ ላይ፣ በመትረየስ ጥይቶች…” 

             ከጥቂት ወራት በፊት፣ አንድ የውጭ ቴሌቪዥን ቻ ናል በ ጣም አ ስገራሚ ዶ ክሜንታሪ አሳየን። አንዲት እንስት አንበሳ፣ ግልገል ሚዳቋ ለብቻዋ ታገኛለች። ‘አኝ’ ታረጋታለች ብለን ስንጠብቅ፣ ጭራሽ ትንከባከባትና ከመሰል ስጋ- በል አራዊቶች ትከላከልላት ጀመር። አንድ አንበሳ አድብቶ ሚዳቋዋን ሊያንቃት ሲል፣ አንበሳይቱ አየችና በቅጽበት አፈፍ አድርጋ፣ አሽሽቻት። ይህን ያዩ ባለሙያዎች ተደመሙ። አንበሲቷ ያሳየችው ርህራሄም ‘ከእንስሳዊ ባህርይ የወጣ ነው’ ተባለ። አንዱ የእንስሳት ባህርይ ባለሙያማ ጭራሽ ‘አንበሳዋ ሚዳቋዋን መብላት ትታ፣ ስትንከባከብ የታየችው ቀውሳ መሆን አለባት’ ሲል ግምቱን ሰነዘረ። ‘በታዳኝ እንስሳ ላይ ርህራሄ ያሳየ አዳኝ እንስሳ፣ እንስሳዊ እብደት ውስጥ የገባ ብቻ ነው’ ሲል አብራራ። በዚህ መሰረት ሰው ሰብአዊነትና ርህራሄ ካላሳየ ‘እንስሳ ሆነ’ እንደምንለው ሁሉ፣ እንስሳውም አይምሬነቱን ትቶ ‘ሰብአዊነት’ ሲፈጽም ካየን ‘ቀወሰ’ እንለዋለን ማ ለት ነው። እስከዛሬ ግን ‘ ያበደ ውሻ’ ሲባል ሰምተን ይሆናል እንጂ ‘እንስሳ ቀወሰ’ ሲባል ሰምተን አናውቅም። ዞሮ ዞሮ ሰው የሰጠው ፍርድና ምስክርነት ነው።

ሁለት ሰዎች ጸባቸው ከልክ በላይ ተካርሮና ጦዞ ‘ይዋጣልን” በሚል ለመገዳደል ቢወስኑ፣እናም ይህ ውሳኔ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ በመገዳደሉ ሂደት፣አንዱ ቆስሎ ቢወድቅና ለመዳን ያለችው ሰብአዊነት-ሥራ-ፖለቲካ ዳደ ደስታናፍቆት ዮሴፍ “ለደርግ ሆስፒታል፡ ወታደር ከበደ ጉነቲ ጉይሳ፤ ዕድሜ 40፣ ትውልድ ወለጋ - ጊምቢ፣ የተጎዳው ከወገብ በታች ብዙ ቦታ ላይ፣ በመትረየስ ጥይቶች…” ብቸኛ ዕድል፣ በዚያ ሊገድለው ባቆሰለው ጠላቱ እርዳታ በኩል ብቻ ቢሆን፣ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ የተለያዩ ስሜቶች እናስብ። እንደ ሰው ሰብአዊነት ከውስጠ-ስሪታችን ጋር ተጋምዶ የተፈጠረ፣ አብሮን ተወልዶ አብሮን የሚያድግ የገዢ ባህርያችን መገለጫ ሆኖ፣ ከሰብእናችን ጋር የተገጠመልን ባህረ-ስሜት ነው። ከውጭ ከሌላ ሰው የምንዋሰው አሊያም የምንሽምተው ነገርም አ ይደለም። ራሳችን አሽቀንጥረን ካልጣልነው በስተቀር፣ ሰብአዊ ሰሜት እና ሰብአዊ ርህራሄ ሁሌም ያሉ ተፈጥሯዊ ባህርያችን ናቸው። ሰብአዊነታችን የሚለካው የአዳምና ሄዋን ዘር ለሆነው፣ሌላ የሰው ልጅ በምናሳየው የርህራሄ ስሜትና የመርዳት/መደገፍ ዝግጁነት ነው። ፖለቲካ የዚህ ተቃራኒ ነው።

ፈልገንና አቅደን የምንይዘው መስመር እንጂ የተፈጥሮ ግዴታ ስለሆነብን የምንገባበት ጉዳይ አይደለም። እንደ ሰብአዊነት በተፈጥሮ የምናገኘው ሳይሆን፣ ከሰዎች የምንማረውና መርጠን የምንይዘው ዝንባሌ ነው። ስራ ደግሞ በሁለቱ መካከል ያለ ቁም ነገር ይመስላል። ቀጥሎ፣ እነዚህን ሶስት ቁምነገሮች (ሰብአዊነት፣ ስራና ፖለቲካ) በሚገርም ዓይነት ሁኔታ አንድ ሰው ላይ ውብ ሆነው ሲገለጹ እናያቸዋለን። “አስተያየት፡ ይህ ወታደር በደረሰበት ከባድ ጉዳት ተሸንፎ ነበር። በተደረገለት ህክምና አሁን ከነበረበት ሁኔታ ቢሻለውም፣ ቁስሉ ሊድንለት አልቻለም…በራሱ ምርጫ ወደናንተ እየመጣ ነው… አስፈላጊውን ትብብርና እርዳታ እንድታደርጉለት ይሁን…” ከ25 ዓመታት በፊት በደብረታቦር ግንባር ውጊያ ላይ ስለነበረው ሁኔታ የምታስረዳ እጅግ አነጋጋሪ ደብዳቤ፣ የተጻፈችበት ሁኔታና ዓላማም እንዲሁ ጥያቄ የሚያጭር፣ የጸሃፊውን አስገራሚ ሰብአዊነት፣ ሙያዊ ስነምግባርና ፖለቲካ አንድ ላይ አጭቃ የያዘች ሰነድ ናት። ‘በፍልሚያና በመገዳደል ውስጥም ለካ ስልጣኔና ቅድስና አለ?’ የምታሰኝ አይን ገላጭ ጦማር። ደብዳቤዋ ከደርግ በኩል ሆኖ ሲዋጋ ቆስሎ፣ በኢህአዴግ ተዋጊዎች እጅ ስለወደቀ አንድ ወታደር በአጭሩ ታትታለች። ውጊያው በኢትዮጵያ ምድር ላይ ነው።

ተዋጊዎች ምንም እንኳ ጎራ ለይተው፣ አንዱ ሌላውን ለ ማንበርከክ የ ሚታኮሱ ቢ ሆኑም ሁ ሉም ያው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ግን፣ ብዙ ዓይነት የጥይትና የፍንዳታ ጦር መሳሪያዎችን፣ የውጊያ አውሮፕላኖችንና ታንኮችን ጨምሮ በእጅ ያለ ነገር ሁሉ ለግድያ በሚውልበት የመጠፋፋት አውድማ ላይ፣ ምን ዓይነት ሰብአዊነትና የሰከነ መንፈስ ሊኖር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል!? በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ እንኳን የጠላትነት ስሜት፣ ምን ዓይነት መራራና ለምህረት በር የዘጋ እንደሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያውያን የቆየ ታሪክ ደግሞ የሞት ሽረት ውጊያ ላይ አንዴ ከተገባ ጠላትን ማሸነፍ፣ ‘የጠላትን አቅም መቆጣጠር’ ከሚለው አልፎ ‘ጠላትን ማስወገድና ማጥፋት’ ወደሚለው የሚያዘነብል ነው። ይህች ወደ ደብረታቦር የውጊያ ግንባር እምትወስደን የእጅ ጽሁፍ ጦማር፣ በይዘትዋና የአፃፃፍ ድምጸትዋ ተገርመን ሳናበቃ፣ በወቅቱ የነበሩትን ተዋጊዎች አስተሳሰብና በእንደዚያ ያለ ሁኔታ ውስጥ ምን ይወስኑና ይፈጽሙ እንደነበረ በአንክሮ እንድናስብ ታደርገናለች። “ሌላው ለመደገፊያ ተብሎ የታሰረለት ጀሶ ከአንድ ወር በኋላ ሊፈታለት ይችላል። ሌላው፣ ካለው ጉዳት አንጻር ደህና ፕሮቲናዊ ምግብ እንዲያገኝ ይሁን” ይህን ደብዳቤ የሚጽፈው የኢህአዴግ ታጋይ የራሱን ስም አይጠቅስም።

ታጋዩ በህክምና ዘርፍ የሚሰራ ነርስ ወይም የጤና መኮንን ለመሆኑ ግን ከደብዳቤው ይዘት እንረዳለን። ኢህአዴግ በዚያን ወቅት ውጊያ በሚያካሂድባቸው ግንባሮች አካባቢ፣ የቆሰሉ የራሱ ታጋዮችን ለማከም ተንቀሳቃሽ ሆስፒታሎችን ወደ ግንባሮቹ ያስጠጋ እንደነበር ይታወቃል። ታዲያ ቆስለው የተማረኩ የጠላት ወታደሮቹንም ቢሆን ማከም ብዙ ተፋላሚ ወገኖች የሚያደርጉት የተለመደ ተግባር ነው። ስሙን ያልነገረን ይህ ታጋይ ነርስ ግን የተጎዳ ‘ጠላቱን’ ለመርዳት የሄደው ርቀት የተለመደ ተግባር አይደለም። ታጋዩ ነርስ ለጻፋት ማስታወሻ የሰጣት የአድራሻ ርእስ “ለደርግ ሆስፒታል- ደብረታቦር” የምትል ናት። እርግጥ የደብዳቤ ቁጥርና የኢህአዴግ ማህተም ይዛ፣ፕሮቶኮል አሟልታ የወጣች ደብዳቤ አይደለችም። በዚህም ምክንያት ታጋዩ ነርስ በግሉ ተነሳሽነት ወይም በአለቆቹ ይሁንታ ይጻፋት መገመት ካልሆነ በቀር በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። የመገመት ጉዳይ ከሆነ ግን፣ የኢህአዴግን የተማከለ አሰራርና ድርጅታዊ ዲሲፕሊን ለሚያውቅ ሰው፣ አንድ ታጋይ ያለ አመራሩ እውቅናና ፈቃድ በግሉ ውሳኔ፣ ድርጅቱ ‘ጠላት’ ከሚለው አካል ጋር ደብዳቤ ይጻጻፋል ተብሎ አይታሰብም። ይህን ግምት ከተቀበልን የደብዳቤዋ ዓላማና አጠቃላይ ይዘትየግንባሩም ነው ብለን ልንወስድ እንችላለን።

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ደብዳቤዋን በእጅ ጽሁፍ የከተባት ታጋይ ነርስ፣ የግል ሰብእናውን የምናይበት መነጽር አለ። ለምሳሌ ጉዳተኛ ወታደሩ ወይም ከበደ ጉነቲ ስለደረሰበት የመቁሰል አደጋና ክብደት፣ ስለተደረገለት ህክምና፣ ስለወሰዳቸው መድሃኒቶች፣ የጀሶው መፍቻ ቀን ወዘተ-- መረጃ ደብዳቤው ላይ እንዲያሰፍር ሙያውም አለቆቹም ያዙት ይሆናል። “…ደህና የፕሮቲን ይዘት ያለው ምግብ እንዲሰጠው ይሁን” የምትለዋ መስመር ግን የራሱን አሳቢነትና ተቆርቋሪነት የምታጎላ ሆና ትታያለች። ዓረፍተ-ነገሯ የአደራና የምክር ዓይነት ቃና ታጭራለች። የደብዳቤዋን ስሜት ይዘን ስንጓዝ፣ የሙያ ስነምግባርና ወንድማዊ ርህራሄ ተጋግዘው የጠላትነት ድንበሩን እንዳፈረሱት እንገነዘባለን። ታጋዩ ነርስ ግን እዛ ስሜት ላይ ብቻ አይተወንም። ወታደር ከበደን ለመርዳት ከ’ጠላት’ ጋር መፃፃፍና ቁስለኛውን በተመለከተ መረጃ መለዋወጥ ሙያዊና ሰብአዊ ግዴታ ቢሆንም ከጥቂት መስመሮች በኋላ፣የትግሉን ሁኔታና ቀጣይ ፍልሚያ በተመለክተ ግን የቀረ ወይም የተቀየረ ነገር እንደሌለ ታጋዩ ነርስ ያስታውሰናል። “በደርግና በኢሰፓ ከርሰ መቃብር ላይ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንመሰርታለን!” የደብዳቤዋ ጸሃፊ፣ በዚች መፈክር የራሱን የፖለቲካ አቋም ገልጿል። ይህ ደብዳቤ፣ ለደርግ ሃላፊዎች የተጻፈና በቁስለኛው ወታደር እጅ የሚሰጥ ከመሆኑ አንፃር “በደርግና በኢሰፓ ከርሰ መቃብር ላይ…” የሚለው አባባል፣ በደብዳቤው አምጪ ላይ የሚፈጥረው ችግር አልታየውም፣ ወይም እንደፍጥርጥሩ ብ ሎታል።

የ ሆኖ ሆ ኖ ግ ን ታ ጋዩ ነርስ፣ ራሱን ከሰብአዊነት፣ከሙያና ከፖለቲካ አንጻር ገልጦ አሳይቶናል። በረሃ ላይ በህክምና መስክ ተሳታፊ የነበረ አንድ ነባር የኢህአዴግ ሰው፣ ስለዚህኛው ደብዳቤ አንስቼለት ብዙም አልደነቀውም። ያኔ ለ ኢህአዴግ ሃኪሞች፣ የሪፈራል ደብዳቤ ለደርግ መጻፍ የተለመደ እንደነበረ ነው የገለፀልኝ። ‘የዓላማ ጉዳይ ነው’ በሚልም ክስተቱ ያን ያህል የሚያስደንቅ ነገር ነው ብሎ እንደማያስብም ጨምሮ ነግሮኛል። በደብዳቤዋ መጨረሻ ላይም “ማከማችን ከዓላማችን ይፈለፍላል” የሚል መልእክት ይነበባል። ይህች ደብዳቤ፣ ያኔ በደርግ መንግስት ቁጥጥር ስር ወደ ነበረችው የደብረታቦር ሆስፒታል ነበር የተላከችው። ከወራት በኋላ ኢህአዴግ በዘመቻ ቴዎድሮስ ብዙ የአካባቢውን ቦታዎች ሲቆጣጠር፣ ደብዳቤዋ ከብዙ ነገሮች ጋር ተዝረክርካ ተገኘች። ደብዳቤዋ ላይ የተጠቀሱ ቀናት ሁለት ናቸው፤ የተጻፈችበት ቀንና ወታደር ከበደ ቆሰለ የተባለበት ቀን። ሁለቱም ቀናት በአንድ ወር ውስጥ ያሉ ቢሆኑም፣ ደብዳቤው የተጻፈበት ቀን ወታደሩ ቆሰለ ከተባለበት ቀን ቀድሟል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በእኔ በኩል ጸሃፊው ቀን ሲጽፍ፣ወይም ወታደር ከበደ የ ቆሰለበትን ቀ ን ሲ ጽፍ፣አ ለ ያም ሁ ለቱንም አቀያይሮ ጽፎት ሊሆን እንደሚችል ግምት ይዣለሁ። ደብዳቤው እኔ እጅ የደረሰበትን መንገድ በማጤንና የዚህ ዓይነት የሪፈራል ደብዳቤዎች ይጻፉ እንደነበር በማረጋገጤ፣ የደብዳቤውን ትክክለኛነት ፈጽሞ አልተጠራጠኩትም። የሰው ልጅ እርስ በርሱ ርህራሄ በጎደለው ጭካኔ ሲጎዳዳ፣ “ሰው አራዊት ሆነ” እንድንል እንገደዳለን። ከእለታት አንድ ቀን አራዊት ራሱ የሰብአዊነት ተግባር ሲፈጽም ሲታይ ግን “ስለቀወሰ ነው” ተብሏል። እንደዚያ ከሆነ፣ ከሰው አራዊት፣ ከሰው ቀውስ ይሰውረን እንጂ፣ የአራዊቶች መቀወስ ክፋት የለውም። የእምነት ሰዎችም፣ መጽሃፉም፡ ‘ነብርና ፍየል፣ አንበሳና ጊደር አብረው የሚቦርቁባት ዓለም ትመጣለች፣ በተስፋ ተመላለሱ’ ሲሉ ያጽናኑናል፣ አይደል። እስከዚያው ራሳችንን በመልካም ሰብአዊነት፣ በመልካም ስራና፣ በመልካም ፖለቲካ እናሰልጥን።

Read 2145 times