Saturday, 17 May 2014 15:46

ቡና እንጠጣ

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(3 votes)

                 ቡና በአለማችን የተትረፈረፈ ምርት አይደለም፡፡ በተፈላጊነት ግን ከነዳጅ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል፡፡ በአለም ላይ በየአመቱ ከአምስት መቶ ቢሊዮን ስኒ በላይ ይሸጣል፡፡ ቡና እንጠጣ በቀን ውስጥ የሚደጋገም ቃል ሳይሆን አይቀርም፡፡ “ካልዲ” በሚባል ኢትዮጵያዊው እረኛ አማካኝነት በከፋ እንደተገኘና ኮፊ ለሚለው መጠሪያ መነሻ እንደሆነ የሚነገርለት የአለማችን ተወዳጅ መጠጥ፤ በየአገሩ በተለያዩ የአፈላልና የአቀራረብ ስርአቶች አሉት፡፡ የኢትዮጵያ አይነት ያሸበረቀ ስርአት ግን የትም ቦታ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ውጪ በቦረና የቡና ስርአት የተለየ ነው፡ ፡ ቡናው ይቆላና ሳይወቀጥ ወተት ውስጥ ይጨምሩታል፡፡ ወተቱን አየጠጡ የተቆላውን ቡና ያጣጥሙታል፡፡ በእርግጥ ጣሊያን ከቡና ጋር ስሟ ይነሳል፡፡ እንዲያውም የኤስፕሬሶ ማሽንን ለመጀመሪያ ጊዜ የፈበረከች አገር ናት፡ ፡ ስፔን፣ አሜሪካ፣ ቱርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ብራዚል፣ አየርላንድና ሌሎችም ከቡና ጋር የቅርብ ትውውቅ አላቸው፡፡

ቡናን በማምረት ከሚታወቁት አገራት ውጭ አብዛኞቹ ጠጪዎች ከጥሬ ቡና ጋር እውቅና የላቸውም፡፡ ከካፌ ውጪ ጥሬ ቡና ታጥቦ ተቆልቶ ተወቅጦ ለጠጪው የሚቀርብባት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ በመቀጠል በአፍሪካ ሁለተኛ የቡና አምራች አገር ብትሆንም ህዝቡ ቡና ጠጪ አይደለም፡፡ እንዲውም ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ፈረንጆች ቡና ያበዛሉ ይላሉ፡፡ ቡናቸውን ወደ ውጪ ይልካሉ፡፡ መጠጣት ለሚፈልግ ሰው የታሸገ ቡና ከውጪ ይመጣለታል፡፡ የአየርላንድ ቡና በአለም ላይ እውቅና ካገኙ ቡና እንጠጣ መጠጦች አንዱ ነው፡፡ በ1940ዎቹ እንደተጀመረ የሚነገርለት የአይሪሽ ቡና፣ ዊስኪ እና ክሬም ተጨምሮበት ይቀርባል፡፡ ቡናው የሚጠጣው ከእራት በኋላ ነው፡፡ አይሪሾች ሶስት ተወዳጅ መጠጦችን በአንድ ላይ በመቀላቀል ጣእማቸው እንዲባክን ያደርጋሉ የሚሉ አልጠፉም፡፡

ቡና በአንድ ወቅት በየመንና በአረቢያ በሀኪም ትእዛዝ ብቻ የሚወሰድ መጠጥ እንደነበረና የመጀመሪያው ቡና ቤት የተከፈተው በ1475 በኮንስታንትኖፕል በአሁኑ ኢስታንቡል እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ቱርኮች ቡና የሚሸጥባቸውን ቤቶች የጠቢባን ትምህርት ቤት በማለት ሲጠሯቸው፣ በእንግሊዝ ውስጥ የመጀመሪያው “ኮፊ ሀውስ” በ1652 ሲከፈት ሴቶች በአስተናጋጅነት ካልሆነ በተስተናጋችነት እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ቡና የተወዳጅነቱ ያህል የዘመቻ ኢላማም ሆኗል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የመካ አስተዳዳሪ የነበሩት ካህር ቤይ ህዝባቸው ቡና እንዳይጠጣ አግደው የነበረ ሲሆን፤ ምክንያታቸውም ህዝቡ በአገዛዙ ላይ እንዲያምፅ ብርታትን ይሰጣል በሚል ነው፡፡ የእንግሊዙ ንጉስ ቻርለስ ሁለተኛአውሮፓ ውስጥ የነበረውን አብዮት ለማጨናገፍ በማሰብ ቡና አውሮፓ ውስጥ እንዲታገድ አዝዞ የነበረ ሲሆን፤ የጀርመኑ ንጉስ ታላቁ ፍሬድሪክም በ1647 ባወጣው አዋጅ ሰዎች ለቡና መጠጫ ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ በሚል ቡና እንዳይጠጣ አግዶ ነበር፡፡ በዓለማችን እጅግ ውድ የሚባለው ቡና የሚሸጠው በኢንዶኔዢያ ነው፡፡ የቡናው ስያሜ ኮፒ ሉዋክ ወይም ሲቬት ቡና ይባላል፡፡

በኤዢያ የሚገኘው ኤዢያን ሲቬት የሚባለው እንስሳ ጥሬውን ቡና ተመግቦ በአካሉ የምግብ ማላሚያ ክፍሎች ካሳለፈው በኋላ በቆሻሻ መልክ ሲያስወግደው አፈሩ ላይ በድጋሚ ይበቅላል፡፡ በዚህ መንገድ የበቀለው ይህ የዓለማችው ውድ ቡና ለአንድ ሲኒ የሚያስከፍለው ዋጋ 50 ዶላር ነው፡፡ የእንግሊዙ ጆርጅ ሶስተኛ በ1967 በሻይ ቅጠል ላይ ያደረገው የታክስ ጭማሪ በአሜሪካዊያን ከፍተኛ ተቃውሞ ከማስከተሉም በተጨማሪ አመፅ መቀሰቀሱ አሜሪካውያኑ ፊታቸውን ወደ ቡና እንዲያዞሩ አድርጓል፡ ፡ ቡ ናንም በ መጨረሻም በ አሜሪካ አ ብዮት እንግሊዝ ተሸንፋለች፡፡ ታወቂው እና በአለማችን ግንባር ቀደሙ የቡና መሸጫ ሱቅ ስታር ባክስ በ1971 ሲያትል ውስጥ የተከፈተ ሲሆን፤ በአርባ አገር ወደ 17ሺ ገደማ ቅርንጫፎች ያሉት ተቋም ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብትሆንም የቡና ቀን የላትም፡፡ አሜሪካን ሴፕቴምበር 29፣ ኮስታሪካ ሴፕቴምበር 12፣ አየርላንድ ሴፕቴምበር 19፣ ጃፓን ኦክቶበር 1፣ብሄራዊ የቡና ቀን በማለት ያከብራሉ፡፡

Read 4259 times