Saturday, 17 May 2014 15:44

የጐንደር ገጠመኞቼ

Written by  ከጉማራ ዙምራ
Rate this item
(5 votes)

የህንፃዎች ስያሜ “አጃኢብ” ያሰኛል

           በሶስት ወራት ልዩነት ጊዜ ውስጥ ከትምህርትና ጤና ጋር የተያያዙ ጥናቶችን ለማካሄድ ወደ ደቡብና ሰሜን ጐንደር አካባቢዎች ተጉዤ በነበረበት ወቅት ከታዘብኳቸው፤ ካስተማሩኝና ካዝናኑኝ ገጠመኞቼ ጋር እስቲ ጥቂት አረፍ በሉ። የቀዳሚው ቀን ጉዟችን ዓባይ በረሃ ላይ በነበረው ሙቀት ከፈነዳው ጐማ በቀር ሰላማዊ በሚባል መልኩ ባህርዳር ከተማ ላይ ተጠናቋል። በማግስቱ የመጀመሪያው የጉዞዬ መዳረሻ ወደሆነችውና የደቡብ ጐንደር ዞን አስተዳደር መቀመጫ፤ ደብረታቦር አቀናን። ደብረታቦር ከተማ አፄ ቴዎድሮስ ሴባስቶቦል መድፍን ያሰሩበት ጋፋት የተባለው ቦታ፤ በደርግና በኢህአዴግ በ1981 ዓ.ም ከባድ የጦርነት አውድማ የነበረው ጉና ተራራ እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊና ረዥም ዘመን ያስቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትና ቅርሶች ያሉበት ከተማ ናት። ከተማዋ ሌሎች የዞን ከተሞች ካላቸው መሰረተ ልማት አንጻር በእኔ እይታ አነስተኛ የሚባል አገልግሎቶች ያሏት ቢሆንም እንደ ኮብል ስቶን መንገድ፤ ት/ቤት፤ ኮንዶሚኒየምና የመሳሰሉት የተለመዱ መሰረተ ልማቶች የተጀመሩባትና ተስፋ የሰጧት ከተማ ነች።

ባለሀብቶች እየገነቧቸው የሚገኙ ችምችም ያሉ ፎቆችም ከተማዋ በእድገት ሩጫ ላይ ሆና “ከእንቅልፌ እየነቃሁ ነው የምትል ቢያስመስሏትም፣ ከፎቆቹ ጀርባ ያሉ ጭርንቁስ ቤቶች ደግሞ “ገና መች ነቅተን፣ ኧረ እያንቀላፋን፤ እያንጐላጀን ነው” እያሉ የጐንደር ገጠመኞቼ የህንፃዎች ስያሜ “አጃኢብ” ያሰኛል የሚያሳብቁባት ከተማ ትመስላለች። ደብረ ታቦር ከተማው መሀል ስንገባ፣ ግርምት ከፈጠሩብኝ ጉዳዮች አንዱ የተጠናቀቁት ፎቆች ስያሜ ነው። ፍሬንድሺፕ፤ ደንበል፤ ዙርጋ፣ አበሩስና ለመሳሰሉ የህንጻ ስያሜዎች ተጋላጭ የነበረ ግለሰብ፣ ወደ እዚያች ከተማ ውስጥ ገብቶ ወደ ግራ ሲዞር፣ የህንጻው ባለቤቶች እስከ አያት ድረስ የሚዘልቅ ስያሜ፤ ገበየሁ አየለ እንግዳ ማረፊያ፤ ሞላ አለምኔው ህንጻ፤ ፈንታነሽ ብርሃኑ ፔንሲዮን…ደግሞ ወደ ቀኝ ዞር ሲባል፣ በሞቱት አያት ወይም እናት ወይም አባት መታሰቢያነት የተገነባ ህንጻ መሆኑን ለማብሰር፤ እማሆይ ዘርፌ ላመስግን መታሰቢያ ሆቴል፤ አያሌው ካሳ መታሰቢያ ህንጻ፤ የአቶ አለህኝ እና የወ/ሮ ተኳዳ መታሰቢያ ህንጻ ወዘተ እያሉ የተሰደሩት ህንጻዎች “አጃኢብ” (“አጀብ አጀብ!” እንደማለት) ሳያስብለው አይቀርም። “ጐንደሬ ክብር ይወዳል አንተው።

” አለችኝ፤ ስለ ስያሜዎቹ ጥያቄ የሰነዘርኩላት አንዲት ሴት። የፎቆቹ መጠጋጋት እና ምንም አይነት የፓርኪንግ ቦታ ሳይኖራቸው የተሰሩት ህንፃዎች ግን ድንገት ትንፋሽ እጥር፤ እፍን፣ መንፈስን ጭንቅ የሚያደርጉ አይነት ናቸው። እንደ እኔ ግምት ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለባለሃብቶች ለማዳረስ በሚመስል ሁኔታ፣ ቦታዎቹ በጠባቡ ተሸንሽነው 100 ካሜ ቦታ ላይ እስከ ጂ+4 ፎቆች ተገንብተው ይገኛሉ። የከተማዋን እድገት ያፋጥናሉ በሚል ሰበብ እየተገነቡ ያሉት ፎቆች፣ ምናልባትም ከ20-30 ዓመት በኋላ ከግንባታ ወጪያቸው እጥፍ በሆነ በጀት አፍርሶ ሌላ መገንባት የሚያስፈልግበት ጊዜ እንዳይመጣ እሰጋለሁ። ስለሆነም የከተማው አስተዳደር ከወዲሁ ዘላቂና የማያዳግም ጥናት በማድረግ፣ የቦታ አሰጣጡን ቢያስተካክል መልካም ነበር። ታዲያ ከነዚሁ ፎቆች ውስጥ የአልጋ ፕሮፎርማ ለማሰበሰብ፣ አንድ ሁለቱ ጋ ጐራ ማለታችን አልቀረም። “አልጋ አለ?” “አዎድ።” “ባለ ስንት?” “ባለ 200፤ 150 እና ባለ 100።” “ምን ምን አገልግሎት አለው?” “ባለ 200 እና ባለ150ው ዋይ ኤፍ አይ አለው፤ ሙቅ ሻወር አለው፤ ቴሌቪዥን አለው።

ባለ መቶው ግን የጋራ መታጠቢያ ብቻ ነው ያለው።” አመስግነን ወጣን። ሌላ ፎቅ ገባንና በእድሜ ጠና ያሉና በዘበኝነት ማእረግ ላይ እንግዳ ተቀባይነት ደርበው የሚሰሩ የሚመስሉ ሰው አገኘን፡- “አባት አልጋ አለ?” “አዎድ።” “ባለ ስንት?” “ባለ 200፤ 150 እና ባለ 100።” “ምን ምን አገልግሎት አለው?” “ባለ 200 እና ባለ 150ው ሙቅ ሻወር አለው፤ ቴሌቪዥን አለው። ባለ መቶው ግን የጋራ መታጠቢያ ብቻ ነው ያለው።” “ዋይ ኤፍ አይ የላችሁም?” “ምንድን ነው ደግሞ እሱ?” “አይ አባቴ ዋይ ኤፍ አይ ማለቴ የኢንተርኔት አገልግሎት ማለቴ ነው?” “ኸዚህ ኢንተርኒት የለም።

ኢንተ ርኒት ያለ ኸ ዚያኛው ፎቅ (ቀድመን ወደ ጐበኘነው ፎቅ እየጠቆሙ) ነው።” “ታዲያ ኢንተርኔት ሳይኖረው ዋጋው አልተወደደም?” “እኔ ምኑን አውቄው ብለህ አንተው። ባለቤቶቹ ይሄን ብለህ ተናገር አሉኝ ነገርኳችሁ። የሚያሻችሁን መምረጥ የእናንተ ፈንታ ነው እንግዲህ።” “እሱስ አዎ አባቴ።” አመስግነን ተለያየንና ዋይ ኤፍ አይ አለው ወደተባለው ፎቅ ሄደን፣ አልጋውን አሳዩን ስንል… እንግዳ ተቀባይዋ መስኮቱ ወደ መንገድ ዳር የሆነ መኝታ ክፍል ስታሳየን፤ “እባክሽ እህቴ፤ መስኮቱ ወደ መንገድ ዳር ያልሆነ ክፍል ቀይሪልን?” አልናት። “ጫጫታ ይረብሸኛል ብለህ ነው?” “አዎ?” “እረ ወዲያ ተወውማ አንተው። አገሩ ዘገምተኛ ነው። ገና 2 ሰዓት ላይ ጭልል ነው የሚል።” “ይቅርታ እህቴ፤ ዘገምተኛ ማለት ግን ስድብ አይሆንብሽም?” “እረ ወዲያ በብርድ የቆፈነነ ሀገር። ገና መሸት ሲል አዳሜ በጊዜ ነው ቤቱ ሚገባ። እንደውም ይሄ ደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ ከተከፈተ ተማሪዎቹ አልፎ አልፎ ያመሹ እንደው እንጂ ሌላስ የለም።” ከፈገግታ ጋር ምክሯን ተቀብለን ክፍላችንን ያዝን።

Read 5890 times