Saturday, 17 May 2014 15:17

የበረሃ አንበጦች ወረርሽኝ ለኢትዮጵያ አሳሳቢ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

“በዚህ ወር ሌላ የአንበጣ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላል” - ፋኦ የአንበጣ መንጋው ጉዳት እንዳያደርስ እየተከላከልን ነው - ግብርና ሚ/ር

     በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት ለማ፤ የአንበጣው መንጋ በሱማሌ ላንድ ተራብቶ በንፋስ እየተገፋ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ገልጸው፣ በሶማሌና በኦሮሚያ አካባቢ በመስኖ በሚለማ ሰባት ሄክታር ሽንኩርትና ድንች ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ውሏል ያሉት ወ/ሮ ህይወት፣ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ከሱማሌ ላንድ የገባው የአንበጣ መንጋ አሁን ያለበት እድሜው ብዙ እንዲመገብ የሚያደርገው እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የመከላከል ስራዎችን በማከናወኑ ጉዳት አላደረሰም ብለዋል፡፡ ከ30 የአንበጣ መንጋዎች ለብቻ ተለይቶ የመጣ አንድ መንጋ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በኩል እንዳለፈና የንፋስ አቅጣጫን እየተከተለ እንደሚሄድ ወ/ሮ ህይወት ተናግረው፤ አሁን ያለው መንጋ አድጎና እንቁላል ጥሎ እንዳይራባ የመከላከል እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል፡፡

ሶማሌ፣ ድሬዳዋና ኦሮሚያ ክልል ላይ የአንበጣ መንጋ እንዳለ ጠቅሰው፣ ለብቻ ተነጥሎ ወደ አዲስ አበባ የመጣው መንጋ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የንፋስን አቅጣጫ ተከትሎ በምዕራብ አዲስ ከአዲስአለም አለፍ ብሎ ወልመራ እንደደረሰና የአካባቢው ግብርና ጽ/ቤቶች አስፈላጊውን የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም የምግብ ፕሮግራም፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ፣ በወቅቱ ተገቢው መፍትሄ ካልተሰጠው፣ በአርብቶ አደር ማህበረሰቡ ህልውና ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ገለጸ፡፡ በዚህ አመት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን እመግባለሁ ብሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት በበኩሉ፣ የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ፣ በሳኡዲ አረቢያና በኦማን ሊባባስ እንደሚችል ባለፈው ሳምንት ባወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ኤልዛቤት ባይርስን ጠቅሶ ሮይተርስ ከጄኔቫ እንደዘገበው፣ በአገሪቱ የተከሰተው የአንበጣ ወረርሽኝ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተበጀለት በሰብሎች ላይ ጥፋት ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ “በምስራቃዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እየታየ ያለው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ፣ የአለም የምግብ ፕሮግራምን እያሳሰበው ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመግታት በወቅቱ ተገቢ እርምጃዎች ካልተወሰዱ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል” ብለዋል ቃል አቀባዩዋ፡፡ ባለፉት አራት ተከታታይ አመታት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የጣለው ዝናብ፣ ከሚጠበቀው አማካይ የዝናብ መጠን በታች እንደነበር ያስታወሱት ኤልዛቤት ባይርስ፣ ይህም ከአንበጣ ወረርሽኙ በተጨማሪ ለምርት መቀነስ የሚዳርግ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የእርስ በእርስ ጦርነትን በመሸሽ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ የአለም የምግብ ፕሮግራም ስደተኞቹን ለመመገብ የያዘውን በጀት እያሟጠጠበት እንደሚገኝና ገንዘቡ እስከ መጪው ወር ሊያልቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት አመታት፣ ከ120 ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን አብዛኞቹም በርሃብ የተደቆሱና የምግብ እጥረት ያጠቃቸው እንደሆኑ የጠቆመው የአለም የምግብ ፕሮግራም፣ ይህም በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን አጠቃላይ ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን ከፍ እንዳደረገው ገልጿል፡፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም ከስደተኞች በተጨማሪ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግረኛ ኢትዮጵያውያን እየመገበ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ በዚህ አመትም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን የምግብ ድጋፍ ተጠቃሚ እንደሚደርግ አስታውቋል፡፡ የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያን መንግስት መረጃ በመጥቀስ፣ የምግብ እጥረት ከአምስት ኢትዮጵያውያን ህጻናት የሶስቱን ዕድገት እያቀጨጨ እንደሚገኝ መናገሩን ዘገባው ጨምሮ ጠቁሟል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት በበኩሉ፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መረጃ የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ፣ በሳኡዲ አረቢያና በኦማን ሊባባስ እንደሚችል ገልጾ፣ በርካታ የአንበጣ መንጋዎች ከሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ በመነሳት፣ ወደ ምስራቃዊ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተናግሯል፡፡ ምንም እንኳን በምስራቃዊ ኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ለማዋል የአየር ላይና የምድር እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም፣ አንበጦቹ ሊራቡና በዚህ ወር አዳዲስ መንጋዎችን ፈጥረው የበለጠ ሊሰራጩ እንደሚችሉ ድርጅቱ ገልጿል፡፡

Read 4623 times