Saturday, 17 May 2014 15:13

የድሬዳዋ ከተማ መሬት አስተዳደር ኃላፊ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀቁ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

    በመሬት ውዝግቦች የምትታወቀው የድሬዳዋ ከተማ መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ታዲዮስ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀቁ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በከተማዋ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ውስጥ በኃላፊነት ተመድበው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ገዛኸኝ ታዲዮስ፤ ሥራቸውን የለቀቁት ባለፈው ሳምንት ሲሆን በምትካቸው የከተማዋ የከንቲባ ፅ/ቤት ኃላፊ የነበሩት የድሬዳዋ ከተማ መሬት አስተዳደር ኃላፊ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀቁ አቶ አብዱልጀባል አብዱልሰመድ ተሾመዋል፡፡ በከተማዋ ውስጥ ባለው የመሬት አስተዳደርና የባለቤትነት ጥያቄ ውዝግብ የተነሳ በርካታ ጫናዎች እንደነበረባቸው የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ በዚህ ሳቢያም ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን ባለመቻላቸው በፈቃዳቸው ስራቸውን እንደለቀቁ ገልፀዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በራስ ፍቃድና ፍላጎት ከኃላፊነት መልቀቅ እብዛም ያልተለመደ መሆኑን የገለፁት ምንጮች፤ የአቶ ገዛኸኝ እርምጃ ለብዙዎች እንግዳ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡ አቶ ገዛኸኝ ታዲዮስን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም ኃላፊው ሥራቸውን በፈቃዳቸው ስለመልቀቃቸው የከተማዋ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በየነ አረጋግጠውልናል፡፡ በከተማዋ አስተዳደር በርካታ የመሬት ጥያቄዎች መኖራቸውን የገለፁት አቶ ፍቃዱ፤ ይህንን አሰራር ለማስተካከልና የማደራጀት ስራዎችን ለመስራት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከጥቂት ሳምንታት በፊት በግምገማ በተነሱት የከተማዋ የጤና ቢሮ ኃላፊ ምትክ የተሾመ ሰው እንደሌለና ቢሮው በተወካይ እየተመራ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በሶማሌና በኦሮምያ ክልሎች የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ለዓመታት የቆየ ውዝግብ መኖሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ከተማዋን ሁለቱ ክልሎች በየሁለት ዓመቱ እየተፈራረቁ በከንቲባነት እንዲያስተዳድሩት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ አሰራር ከንቲባው አስተዳደሩን በአግባቡ ሳይለማመድ ስራውን እንዲያቋርጥ የሚያደርግ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከንቲባዎቹ በየአምስት አመቱ በመቀያየር እንዲያስተዳድሩ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

Read 2613 times