Saturday, 10 May 2014 13:02

የእብዱ ሰው ማስታወሻ

Written by  ደራሲ፡- ጌ ደ ሞፓሳ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(7 votes)

          (የእብዱ ሰው ማስታወሻ ወይም The Dairy of a Mad Man በሚል ርዕስ ሦስት ታላላቅ ደራሲያን ማለትም ፈረንሳዊው ጌ ደ ሞፓሳ፣ ቻይናዊው ሉ ሰን፣ እና ሩሲያዊው ኒኮላይ ጎጎል ምርጥ ምርጥ አጫጭር ልብ ወለዶች ጽፈዋል፡፡ የሶስቱም ደራሲዎች ስራዎች ድንቆች ናቸው፡፡ ለምን እብዶች ለዘመናት ለዚያውም በታላላቅ ደራሲዎች ተመራጭ ገፀ-ባህሪያት ሆኑ? እብዶች እንዴት ነው የሚያስቡት? ከስራዎቹ አስደናቂ መልሶች ታገኛላችሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ያቻይናዊውን የሉሰን አጭር ልብ-ወለድ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ የፈረንሳዊውን ደራሲ ጌ ደ ሞፓሳ ሥራ እነሆ ብለናል፡-) የማይሞት ሰው የለም፤ እሱም ሞተ፡፡ ሲሞት የፈረንሳይ ጠቅላላ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ነበር፡፡

በፈረንሳይ ፍርድ ቤቶች የህግ አንቀጽ መጥቀስ እና የሱን ስም መጥራት እኩያሞች ናቸው፤ ተመሳሳይ ስሜት ነው እሚፈጥሩት፤ አክብሮት እና ፍርሀት። ህፀፅ አልባው ህይወቱ ማንንም የሚያስቀና ነበረ፡፡ የፍትህ አንቀንቃኞች፣ የህግ ተማሪዎች፣ ጠበቆች፣ ዳኞች፣… ረዥም፣ ቀጭን፣ የገረጣ እና ከጥልቅ ጉድጓዶቻቸው ውስጥ የሚንቦጎቦጉ አይኖች ያሉትን ይህን ሰው ሲያዩ በክብር ይሰግዳሉ፡፡ ህይወቱን ያሳለፈው ወንጀለኞችን በመቅጣት እና ደካሞችን በመከላከል ነበረ፡፡ ህይወቱን ያሳለፈው ለፍትህ በመታገል ነበረ፡፡ ተራ አጭበርባሪዎችም ሆኑ አደገኛ ነፍሰ ገዳዮች ስሙን ሲሰሙ ይርበደበዳሉ፡፡ ተራ አጭበርባሪዎችም ሆኑ አደገኛ ነፍሰ ገዳዮ ምን እንዳደረጉ ብቻ ሳይሆን ምን ሊያደርጉ እንዳሰቡ እንደሚያውቅ ያውቃሉ፡፡ አቤት ሲፈሩት! በሰማንያ ሁለት ዓመቱ ነው የሞተው። ብሔራዊ ቀብር ነው የተፈፀመለት፡፡ አስክሬኔ ጉድጓድ ሲገባ እሬሳውን ያጀቡት ወታደሮች በሉ፣ ሴቶች በሉ፣ ህፃናት በሉ፣ ምን አለፋችሁ … ቀባሪዎቹ ሁሉ የእውነት ሃዘን ነበር ያዘኑት፡፡

የሃቅ እንባ ነበር ያፈሰሱት፡፡ ስንብታቸውም መራራ ነበር፡፡ የሰውየው እውነተኛ ማንነት የታወቀው፣ ዘግናኙ ሀቅ ገሃድ የወጣው ኋላ ነበር፡፡ ሟች የግል ሰነዶቹን የሚያስቀምጥበት መሳቢያ ውስጥ ይህ ማስታወሻ ተገኘ፡፡ የማስታወሻው ርዕስ “ለምን?” ይላል፡፡ ይኸውላችሁ፡- ሰኔ 20 ቀን 1851 ዓ.ም፡- ገና ከፍርድ ቤት መመለሴ ነው፡፡ በሎኔልን በሞት እንዲቀጣ ፈረድኩበት፡፡ የታባቱንስና! አሁን እስኪ ምን ሆንኩኝ ብሎ ነው አምስት ልጆቹን እና ባለቤቱን በስንት ጥይቶች የፈጀው? ምን ሆንኩኝ ብሎ? ይህ ድርጊት ምንም አይነት ምክንያት ሊቀርብለት አይችልም፤ ቢቀርብ እንኳ ሊያሳምን አይችልም፡፡ በረዥም የስራ ዘመኔ እንደታዘብኩት፣ ወንጀለኞች አይናገሩት እንጂ መግደል ደስ የሚል ነገር አለው፡፡ ለደስታ ብለው የሚገሉ ሰዎች እንዳሉ አውቄያለሁ፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ፣ የእድሜ ልክ እስራት እና የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው እያወቁ፣ ለምን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ይገድላሉ? ከመግደል የሚያገኙት ደስታ ከቅጣቱ ስለሚበልጥባቸው አይደል? እንዲያ ነው፡፡

አዎ እንዲያ ነው፡፡ እንደ መግደል የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ከመግደል የሚገኘው ደስታ ከሌላ ከምንም ነገር አይገኝም፡፡ ከመግደል የሚገኘው ደስታ ከደስታዎች ሁሉ የላቀ ነው፡፡ መፍጠር እና ማጥፋት እኩያሞች አይደሉምን? ያለ ጥርጥር መፍጠር እና ማጥፋት እኩያሞች ናቸው። መፍጠር እና ማጥፋት ሁለቱም ድንቅ ነገሮች ናቸው፡፡ የአለምን ታሪክ መርምሩ፡፡ የዓለም ታሪክ በሁለት ቃላት ተጠቅልሎ ሊነገር ይችላል፤ መፍጠር እና ማጥፋት በሚሉ ሁለት ቃላት፡፡ ታዲያ በየቀኑ ሰዎች ቢገዳደሉ ይገርማል? አይገርምም፡፡ መግደል ሱስ ነው ልበል? አዎ መግደል ሱስ ነው፡፡ ሰኔ 25 ቀን፡- ሰሞኑን ደግሞ ስለ ህልውና እያሰብኩ ነው የከረምኩት፡፡ እነዚህ የሚንከወከዉ፣ ወዲህ ወዲያ የሚሉ ሰዎች ቆይ ምንድናቸው? ህልውና ምንድነው? ህልው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? በቃ እንዲህ ወዲህ ወዲያ መንከውከው ነው? እኔ ልንገራችሁ፤ ሰዎች ምንም ናቸው፡፡ ምንም ነገር ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ምንም ነገር ደግሞ እነሱን ጉዳዬ ናቸው አይላቸውም፡፡ የሚያጓጉዛቸው፣ የሚረግጡት መሬት እንኳ ምናቸውም አይደለም፤ እነሱም ለመሬቱ ምንሞቹ ናቸው፡፡ ሰዎች ምንም ናቸው።

ሰዎችን ማን አባቱ፣ መቼ አባቱ እንደፈጠራቸው አላውቅም፤ እንዲሁ የሚንከወከው መናኛ ፍጡራን መሆናቸው ግን አውቃለሁ፡፡ እነዚህን ማን፣ መቼ፣ ለምን፣ እንደፈጠራቸው የማይታወቁ ሰዎች ባጠፋቸውስ? ብገላቸው? ምን ችግር አለው? ምንም፡፡ ሰዎች ያለምክንያት ነው የተፈጠሩት፤ እነዚህን ያለምክንያት የተፈጠሩ ሰዎች ያለምክንያት ብገላቸው ምን ችግር አለው? ምንም፡፡ በዚያም ላይ መግደል ደስ ይላል። የሆነ ሰው የሚባል ፍጡር አለ። እኔ ከፈለገሁ ይህን ሰው ተብዬ ፍጡር ከህያውነት ወደ ምንምነት መቀየር እችላለሁ፡፡ ማንንም ሰው ከ “ነው” ወደ “ነበር” ልቀይር እችላለሁ፡፡ እና ታድያ ይህ ደስ የሚል ብቃት አይደል? እንዴታ! ደስ ይላል እንጂ፡፡ ሰኔ 26 ቀን፡- ቆይ ግን መግደልን ሀጥያት ወይ ወንጀል ያደረገው ማነው? የምሬን ነው፡፡ መግደል ለምን ወንጀል ሆነ? በጥልቀት ካሰባችሁበት መግደል የተፈጥሮ ህግ ነው፤ መግደል የተፈጥሮ የማይዛነፍ ህግ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፍጡር ለመኖር ሲል ይገላል፡፡ ምን ለመኖር ብቻ ለመግደል ብቻ ብሎም ይገድላል፡፡ እንስሳቶች ለመኖር ሲሉ ይገድላሉ፤ ሰውም እንዲሁ ለመኖር ሲል ይገድላል፡፡

የሰው ለየት የሚለው ቤቱ ሆዱን ከሞላ በኋላ፣ እንደገና ስንቅ ይዞ ለአደን ይወጣል፤ የማይበላቸውን እንስሳት ይገድላል፡፡ ለምን ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ከመግደል የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም ነው። ህጻናትን አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? ገዳዮች ናቸው፡፡ ትናንሽ ነፍሳትን በእጆቻቸው፤ አእዋፋትን በድንጋይ እና በባላቸው ይገድላሉ፤ አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ትንንሽ እንስሳትን ሁሉ ይገድላሉ። እነዚህ ህጻናት ሲያድጉ እንስሳትን መግደል ብቻ አያረካቸውም፡፡ አብሮአቸው የሚያድገው የመግደል ጥማትን ለማጥገብ ሰው ይገድላሉ፡፡ በጥንት እምነቶች ስርአት፣ ምእመናን ሰውን ለአምላካቸው መሰዋእት ያቀርቡ ነበር፡፡ ሰዎች ሰው ለመግደል ያላቸውን ድብቅ ፍላጎት እንዴት በረቀቀ ሁኔታ ሀላል እንዳደረጉት አያችሁ? በእግዚአብሔራቸው አሳበው በመግደል፣ በህብረት የሚረኩበት ስርዓት ፈጠሩ፡፡ አሁን ይህ ቀርቷል። አሁን፣ አሁን፡- “መግደል ሀጥያት ነው፤ መግደል ወንጀል ነው” እንላለን፡፡ ገዳዮችንም እናወግዛለን፤ እንቀጣለን፡፡ በመግደል የሚረካው ፍላጎታችን ግን አሁንም አብሮን አለ፡፡ በህብረት የምንሳተፍበት የሰው መስዋእት ሲቀር ምን አደረግን? በህብረት የምንገድልበት ጦርነት የሚባል ስርአት ፈጠርን። ሰዎች በሚረባው በማይረባው ምክንያት ጦርነት ይቀሰቅሱ እና ሀገር ለሀገር ተቧድነው ይፋጃሉ፡፡

ከዚህ በላይ የሞት ድግስ አለ? ከዚህ በላይ የደም ድግስ አለ? የለም፡፡ ህጻናት፣ ሴቶች፣ ሲቪሎች እና ወታደሮች እንደ ጦርነት እና እንደ ጦርነት ታሪክ የሚወዱት ነገር የለም፡፡ ሌሊት እንቅልፋቸውን አጥተው የሚያነቧቸው መፅሐፍት ስለ ምን የተፃፉ ናቸው? ስለ ወንጀሎች እና ጦርነቶች የተፃፉ አይደሉምን? ናቸው፡፡ በጦርነት የተሳተፊት እና ብዙ ሰዎች የገደሉ ሰዎች በምድርም በሰማይም መኮነን ነው የነበረባቸው፤ የሚሆነው ግን እንዲያ አይደለም። በጦርነት የተሳተፉ እና ብዙ ህይወት የቀጠፉ ሰዎች በሽልማት ነው የሚንበሸበሹት፤ በረዣዥም የማእረግ ስሞች፣ በሚያብረቀርቁ ኮከቦች፣ በክብር ዩኒፎርሞች ይንበሸበሻሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ በጦርነት የተሳተፉ እና ብዙ ሰዎች የገደሉ ሰዎች የወርቅ መስቀል ሁሉ ይሸለማሉ፡፡ አሁን ለገዳይ መስቀል ያውም የወርቅ መስቀል መሸለም ምን ይሉት ፌዝ ነው? በጦርነት የተሳተፉ እና ብዙ ሰዎች የገደሉ ሰዎችን ኩራት ደግሞ አይታችሁልኛል? ህዝቡ እንዴት እንደሚያከብራቸው ታዝባችኋል? ሴቶች በፍቅር የሚያብዱላቸው ምን ስለሆኑ ይመስላችኋል? ምንም ስለሆኑ አይደለም፤ ገዳይ ስለሆኑ ነው፤ ለዚያውም ከሌሎች አብዝተው ስለገደሉ ነው፡፡ ተራ ወንዶች እንዴት እንደሚቀኑባቸው አስተውላችኋል? ለዚያውም እኮ እነዚህ በጦርነት የተሳተፉ እና ብዙ ሰዎች የገደሉ ሰዎች፣ ነፍስ ማጥፊያ ሽጎጦቻቸውን እንድናይላቸው አድርገው ታጥቀው ነው በኩራት የሚንጎራደዱት፡፡

ይኸ ሁሉ ለምን የሆነ ይመስላችኋል? ምክንያቱማ የመግደልን ታላቅ ህግነት ተፈጥሮ በእያንዳንዳችን ልብ ላይ በደማቁ ፅፋዋለች፡፡ እንደ መግደል ውብ፣ ማራኪ እና ተከባሪ ነገር የለም፡፡ ሰኔ 30 ቀን፡- መግደል የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ተፈጥሮ ለመታደስ መግደል አለባት፡፡ ተፈጥሮ ዘላለማዊ ወጣትነቷን እንዳለ ለማቆየት መግደል አለባት፡፡ ብቡ ሰው ሆነ፣ ብዙ ነገር በሞተ ቁጥር ተፈጥሮ የበለጠ እየታደሰች፣ የበለጠ ወጣት እየሆነች ትመጣለች፡፡ የተፈጥሮን ሁለመና አስተውላችሁ ከሆነ፣ ረቂቅ ቋንቋዋን አድምጣችሁ ከሆነ እንዲህ ስትል ነው የምትሰሟት፡- “አቦ አፍጥኑታ፤ ቶሎ፣ ቶሎ ተገዳደሉ፡፡” ነሐሴ 2 ቀን፡- ሰው?.... ይህ ሰው ይሉት ፍጥረት ምንድነው? እንዲያው ዝም ብዬ ሳስበው የሰው ልጅ የፍጥረት ሁሉ ታላቁ መገለጫ ነው፡፡ ትውስታዬ እና ሳይንሱ የሚነግሩኝ ይህንኑ ነው፤ የሰው ልጅ ቅልብጭ ያለ የዩኒቨርሱ ምንነት ማሳያ ነው፡፡ ስለዩኒቨርሱ ምንነት ለማወቅ ስለሰው ማጥናት በቂ ነው፡፡ ሰው ታላቁ አለም ውስጥ ያለ ሚጢጢ አለም ነው፡፡ ነሐሴ 3 ቀን፡- አቦ ይህ መግደል ይሉት ነገር፣ ነገረ-ሀሳቤን ሁሉ ተቆጣጥሮታል፡፡ በመግደል ጣፋጭ የሆነ፣ ልዩ የሆነ ደስታ እንደሚገኝ እርግጠኛ እየሆንኩ መጥቻለሁ። ምን ይሆናል መሰላችሁ? የሆነ የሚተነፍስ፣ ደሙ የሚራወጥ፣ የሚያስብ ሰው ይሉት ነገር አለ። ‘ቆይ እንዴት’ ትሉትና፣ ፊታችሁ ታቆሙትና የሆነ የሰውነት ክፍሉ ላይ የሆነች ቀዳዳ፣ በሆነ መሳሪያ ታበጁለታላችሁ፡፡ አንዲት ቀዳዳ እኮ ናት፤ ለዚያውም መናኛ ነገር፡፡ ከዚያ በዚያች ቀዳዳ በኩል ቀይ ነገር እንዲፈስ ማድረግ እና ሲፈስ ማየት። ህይወት ይሉት ነገር ያለው እዚያው ቀይ ፈሳሽ ውስጥ ነው፡፡

ይህ ቀይ ፈሳሽ ፈሶ ሲያልቅ ሁሉ ነገር ያበቃል፡፡ አሁን መተንፈስ የለ፤ መንቀዥቀዥ የለ፤ ሀሳብ ይሉት ነገር የለ፤ አለቀ፡፡ አሁን ፊታችሁ የሚኖረው ቀዝቃዛ፤ ነገሬ ይህ ነው የወማይል የስጋ ክምር ይሆናል፤ አይገርምም? እኔን ለጉድ እየገረመኝ ነው፡፡ ነሐሴ 5 ቀን፡- ሰዎች አያውቁም እንጂ እኔም እኮ ገዳይ ነኝ። “ይኼይሰቀል፤ ይኼ በጊሎቲን አንገቱ ይቀላ” ስል ነው የኖርኩት፡፡ ሰዎች ግድያ የሚፈፀመው በመሳሪያ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ተሳስተዋል፡፡ እኔ በቃላት ነው ስገድል የኖርኩት፡፡ ፍርድ ቤት በክብር ተሰይሜ፡- “እከሌ ይሰቀል፡፡… እከሌ ይቀላ” ስል ነው የኖርኩት። ቆይ፣ ቆይ ግን እኔም እንደሌሎቹ ለምን በመሳሪያ አልገድልም? የምር ለምን አልገድልም? ማን ይጠረጥረኛል? ማን ያውቅብኛል? ነሐሴ 10 ቀን፡- ማን ሊያውቅብኝ ይችላል? የቱ ሰው እኔን በግድያ ሊጠረጥረኝ ይችላል? እኔን? እኮ ማን? በተለይ ደግሞ ምንም ያላደረገኝን አንድ ምስኪን ሰው ብገድል፣ ማን ሊጠረጥረኝ ይችላል? ማንም፡፡ ነሐሴ 15 ቀን፡- የመግደል ረሀብ ሊገድለኝ ነው። ስለመግደል ሳስብ መላ ሰውነቴ በጉጉት፣ በደስታ ይንቀጠቀጣል፡፡

ነሐሴ 22 ቀን፡- የመግደል ጥማቴን መቋቋም አልቻልኩም፤ በቅርቡ ወደ ተግባር መሸጋገር አለብኝ፡፡ ሰራተኛዬ ወፎች ይወዳል፤ ከምከፍለው ደመወዝ ቆጥቦ በውድ ዋጋ የገዛት ወፍ አለችው፡፡ የመግደል ሙያዬን ዛሬ መከመር አለብኝ፤ ከምን መጀመር እንዳለብኝም ወስኛለሁ፡፡ ጆኒን ወደ ገበያ ላክሁት፡፡ ምስኪኗን ወፍ ካለችበት አወጣኋት፤ ትሞቃለች፤ የልብ ምቷ እንዲሰማኝ ጨመቅ አደረግኋት፡፡ መዳፌ ውስጥ ልቧ ትር፣ ትር ሲል ይሰማኛል፡፡ በመዳፌ ውስጥ እንደያዝኳት ወደ መኝታ ክፍሌ አመራሁ፤ በእያንዳንዱ እርምጃ ጨመቃዬን እያጠበቅሁት ነበር፡፡ ጨመቃዬን ባጠበቅሁት መጠን፣ የወፏ የልብ ትርታ በደንብ እየተሰማኝ መጣ፡፡ ቀፋፊ ነገር ነው እያደረግሁ ያለሁት፤ እንዲያም ሆኖ፤ የሆነ ደስ የሚል ነገር አለው፡፡ ቀስ ብዬ፣ በእርጋታ እና በጥንቃቄ አንገቷን ቀነጠስኩት፡፡ እንዴት እንደተንፈራገጠች አትጠይቁኝ፡፡ እንኳን እሷን እምታህል ሚጢጢ ወፍ ቀርቶ፣ እብድ ውሻ እንኳን እንዲያ ሊንፈራገጥ አይችልም፡፡ ገርሞኛል፡፡ አንገቷን ቀነጠስኩት፡፡ ደሟ ሲፈስ አየሁኝ፡፡ አሁን ገዳይ ሆኛለሁ፡፡ አደገኞቹ እና ምርጦቹ ገዳዮች እንደሚያደርጉት አደረግሁኝ፡፡

በእርጋታ መቀሱን አጠበኩኝ፣ በእርጋታ እጄን ታጠብኩኝ። ሬሳዋን በጨርቅ ጠቅልዬ ጓሮ ውስጥ ያለ እንጆሪ ዛፍ ስር ቀበርኳት፡፡ ሬሳዋን ማንም ሊያገኝ አይችልም፡፡ ከዛሬ ወዲህ የዛን የእንጆሪ ዛፍ ፍሬ በየእለቱ አጣጥማለሁ፡፡ ካወቃችሁበት ህይወትን ማጣጣም ይሏችኋል ይኼ ነው፡፡ አቦ እንዴት ደስ ይላል፡፡ ሠራተኛዬ ጆኒ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ “ወፏ በራ ጠፋች፡፡” አልኩት፡፡ አመነኝ፡፡ እንዴት እኔን ይጠርጥር?! ይገርማል፡፡ ነሐሴ 25 ቀን፡- ሰው መግደል አለብኝ፤ የግድ ነው መግደል አለብኝ፡፡ ነሐሴ 30 ቀን፡- ገደልኩ፡፡ የሆነ ሚጢጢ ልጅ ገደልኩ፡፡ ቨርን የሚባለው በአቅራቢያችን ያለ ጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ እያደረግሁ ነበር፡፡ ስለምንም ነገር እያሰብኩ አልነበረም፡፡ መንገድ ላይ አንድ ህጻን ቅቤ የተቀባ ዳቦ እየገመጠ፣ በክብር መንገድ እየለቀቀልኝ፡- “እንዴት ዋሉ ክብር ፕሬዚደንት?” አለኝ፡፡ “እንዴት ዋልክ?” የመግደል አሳቤ ድንገት ከተፍ አለ፡፡ ‘ልግደለው እንዴ?’ ብዬ እራሴን ጠየቅሁኝ፡፡ “ማሙሽዬ ብቻህን ነህ እንዴ?” አልኩት፡፡ “አዎን ጌታዬ፡፡” “ወዲህ ስትመጣ ጫካው ውስጥ ማንንም አላየህም ማሙሽ?” “ማንንም አላየሁም ጌታዬ፡፡” ይኼኔ በመግደል ረሃብ ሰከርኩኝ፤ በወይን እንኳን እንዲህ ሰክሬ አላውቅም፡፡ እንዳይሸሸኝ ብዬ ቀስ እያልኩ ቀረብኩት፡፡ አልሸሸም፡፡ ምን ጠርጥሮ ይሽሽ? አጠገቡ እንደደረስኩ ጉሮሮውን አነቅሁት። በድንጋጤ በተሞሉ የልጅ አይኖቹ አፈጠጠብኝ። አቤት አይኖቹ፤ መቼም አይረሱኝም። በትንንሽ እጆቹ፣ አንገቱን ከእጄ ሊያላቅቅ ታገለ። በመጨረሻም እሳት ላይ እንደወደቀ ላባ ሙሽሽ አለ። ፀጥ፡፡ እሬሳውን አቅራቢያችን የነበረ ኩሬ ውስጥ ጣልኩት፤ ቅጠል አለበስኩት፡፡ በተዝናና፣ በተቀናጣ እርምጃ ወደ ቤቴ ሄድኩ። እራቴን በላሁ፡፡ እራቴ እንዲህ እንደዛሬው ጣፍጦኝ አያውቅም፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ሰውነቴ ቅልል ብሎኝ፣ እንዲህ እንደዛሬው የመታደስ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ እራቴን እንደበላሁ ለመጠጥ “ፐርፌክት ቡና ቤት” ሄድኩ፡፡ ቡና ቤቱ ውስጥ ለጉድ ሳወራ ነበር፡፡

ገርሟቸው፡- “ምነው ዛሬ ጨዋታ አበዛህሳ?” ሁሉ አሉኝ፡፡ ደም አለማየቱ ቆጭቶኛል፤ ብዙም ግን ደስታዬን አልቀነሰውም፡፡ ታህሳስ 31 ቀን፡- የህጻኑ ልጅ እሬሳ ተገኘ፡፡ ገዳዩ እየተፈለገ ነው። ወገኞች! መስከረም 1 ቀን፡- ሁለት ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል፡፡ ማስረጃ ግን አልተገኘባቸው፡፡ ወገኞች! መስከረም 2 ቀን፡- የሟች ወላጆች የህግ ምክር ሊጠይቁኝ ቤቴ መጡ፡፡ ለጉድ ነው ያለቀሱት፡፡ ወገኞች! ጥቅምት 6 ቀን፡- ምንም ማስረጃ አልተገኘም፡፡ ህፃኑን የገደለው አንድ በሽሽት ላይ ያለ ወንጀለኛ ነው ተባለ፡፡ ደሙ ሲፈስ አይቼ ቢሆን ኖሮ፣ ደስታዬ ከአሁኑ የላቀ ይሆን እንደነበር ጠረጠርኩኝ፡፡ ልክ የሀያ ዓመት ወጣቶቸ ለህይወት የሚሰማቸው አይነት ፍቅር ነው፣ እኔም ለመግደል እየተሰማኝ ያለው፡፡ የመግደል ፍቅር ሊገድለኝ ነው፡፡ ጥቅምት 20 ቀን፡- ወንዳታ! አሁንም ገደልኩኝ፡፡ ቁርሱን በልቼ በአቅራቢያችን ያለው ወንዝ ዳርቻ የእግር ጉዞ እያደረግሁኝ ነበር፡፡ ትንሽ እንደተጓዝኩኝ አንድ ሰው የወንዙ ዳርቻ ላይ እንቅልፉን ሲለጥጥ አገኘሁ፡፡

አሳ አጥማጅ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ የገረመኝ አጠገቡ መጥረቢያ አለ፡፡ አሁንም የገረመኝ መጥረቢያው ለኔ ተብሎ የተቀመጠልኝ ነው የሚመስለው፡፡ በእርጋታ መጥረቢያውን አነሳሁት፤ ያለኝን ሀይል ሁሉ ሰብስቤ የአሳ አጥማጁን ጭንቅላት ፈለጥኩት፡፡ ወንዳታ! ደም አየሁኝ፤ የጽጌረዳ ቅላት ያለው ደም አየሁኝ፡፡ አቦ እንዴት ደስ ይላል፡፡ ደሙ በቀስታ እየፈሰሰ ከወንዙ ውሃ ጋር ተቀላቀለ፡፡ በቀስታ፣ በጣም በቀስታ እየተራመድኩ ወደ ቤት ሄድኩኝ፡፡ አሁን ደግሞ አንድ ነገር ቆጨኝ፤ የሰውየውን አናት ስፈልጠው፣ ሰዎች ቢያዩን ኖሮ አሪፍ ነበር፤ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ይሆን ነበር፡፡ ምን አይነት ጨካኝ ገዳይ መሆኔን ሰዎች ቢያዩልኝ ምርጥ ነገር ነበር፡፡ ኤዲያ! ጥቅምት 25 ቀን፡- የአሳ አጥማጁ ግድያ ከተማው ውስጥ ትልቅ መነጋገሪያ ሆነ፤ ሁሌ አብሮት አሳ የሚያጠምደው የአጎቱ ልጅ በግድያው ተጠርጥሮ ተያዘ፡፡ ጥቅምት 26 ቀን፡- አቃቤ-ህጉ፤ የሟች የአጎት ልጅ ግድያውን እንደፈፀመ በማስረጃ አሳመነ፡፡

የአቃቤ- ህጉ መከራከሪያ ሁሉኑም ሰው አሳምኗል፡፡ ወገኞች! ጥቅምት 27 ቀን፡- በግድያው ተጠርጥሮ የተከሰሰው ሰው፣ ቀሽም ተከራካሪ ነው፡፡ ያቀረበው መከራከሪያ፡- “ግድያው በተፈፀመበት ሰአት በቦታው አልነበርኩም፤ ዳቦ ልገዛ ገበያ ሄጄ ነበር፡፡” የሚል ነበር፡፡ አሁን ይኼ ማንን ሊያሳምን ይችላል? ጥቅምት 28 ቀን፡- በመጨረሻም ተከሳሹ ግድያውን እንደፈፀመ አመነ፣ የእውነት አመነ፡፡ ሁሉም እሱ ግድያውን እንደፈፀመ አምነው ነበር፡፡ ከማመን ውጪ ምንም ሊያደርግ አይችልም ነበር፡፡ ፍትህ ይሉሃል ይህች ነች፡፡ ወገኞች! ህዳር 15 ቀን፡- ተከሳሽ ላይ ያልቀረበ ማስረጃ አልነበረም። በተለይ ተከሳሽ የሟች ወራሽ መሆኑ ሲታወቅ፣ ሁሉም እሱ እንደገደለው አመኑ፡፡ በመጨረሻም ክሱን እንዳየው፣ እኔ የምሰየምበት ፍርድ ቤት ተላከ። ጥር 25 ቀን፡- ምን ልፍረድበት? ምን ጥርጥር አለው… ሞት ነዋ፡፡ ሞት! ሞት! ሞት! ሞት… ፈረድኩበት፡፡ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ ሟችን የገደልኩት እኔ ነኝ እና በሱ ግድያ ተከሶ የመጣውን ሰው ደግሞ እንዲገደል የወሰንኩበት እኔ፡፡ ከዚህ በላይ መታደል አለ? የለም። አንገቱ በጊሎቲን ሲቆረጥ ሄጄ አያለሁ፡፡ የሞት ቅጣት ከፈረድኩ በኋላ፣ አቃቤ-ህጉ ስለ ፍትህ ቤቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁሉ በእንባ ያራጨ ንግግር አደረገ፡፡ እንደ መላእክ ለመሆን ሁሉ ሞካክሮት ነበር፡፡

ወገኛ ሁሉ! መጋቢት 10 ቀን፡- ገደሉት፡፡ ዛሬ ጠዋት አንገቱን በጊሎቲን ቀነጠሱት፡፡ ብዙም አልተረበሸም ነበር፤ ለዚያ አድንቄዋለሁ፡፡ አቦ ግን የሰው አንገት ሲቆረጥ ማየት በጣም ደስ ይላል፡፡ የሆነ ደስ የሚል ነገር ባይኖረውም፣ ያ ሁሉ ሰው ለምን ትእይንቱን ሊያይ መጣ ታዲያ? በጣም ብዙ ሰው ነበር፡፡ ደሚ ሲፈስ አየሁኝ፡፡ በህይወቴ ዋኝቼ አላውቅም፣ ዛሬ መዋኘት አማረኝ፤ ቀይ ፈሳሽ ውስጥ፣ ደም ውስጥ መዋኘት አማረኝ፡፡ አሁን መጠንቀቅ አለብኝ፡፡ ቀጣዩን ግድያ ከመፈጸሜ በፊት ትንሽ መቆየት አለብኝ፡፡ መቆየት የምችልም ይመስለኛል፡፡ በማይረባ ስህተት መያዝ የለብኝም፡፡ ማስታወሻው እዚህ ጋ ነው የሚያበቃው፡፡ ማስታወሻ ደብተሩ ሌሎችም ብዙ ገፆች አሉት፤ ስለ ሌላ የግድያ ወንጀል ግን የተጻፈ ነገር የለም፡፡ ማስታወሻ ደብተሩን ያነበቡ የአእምሮ ህክምና ባለሙያዎች፤ አለም ላይ የየእለት ድርጊታቸውን እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው የሚከውኑ፣ አደገኛ እብዶች እንዳሉ ፃፉ፤ ይኸኛውም ከእነሱ አንዱ ነበር።

Read 4098 times