Saturday, 10 May 2014 12:57

ውበትን ፍለጋ

Written by  ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(2 votes)

(ውበት እንደተመልካቹ አይደለም!)

           ውብ የሆነውን ፈልጎ ማግኘት፤ ከአስቀያሚው ለይቶ ማስቀመጥ ቀላል ነውን? በእርግጥ ቀላል አይደለም፡፡ ግን ደግሞ በፍፁም የማይቻል ጉዳይም አይደለም፡፡ መልካም እና ደጉን ለመለየት የሚያስችል ህሊና እንዳለን ሁሉ፣ ዐይነ ግቡነትና ፉንጋነትን መለየት የሚያስችል ልቡናም አለን፡፡ እንደው በቀላሉ ግራና ቀኛችንን ብናማትር ለምሳሌ እንደ ጌጣ ጌጥ የሚያብለጨልጭ ሕንጻ በአብረቅራቂነቱ ብቻ ውብ እንዳልሆነ ይገባናል (“ያብረቀረቀ ሁሉ ወርቅ አይደለም” እንዲል ምሳሌ)፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ድምፅ ሁሉ ዜማ አይደለም፤ ሸራ ሁሉ ስዕል አይደለም፤ ፊደል ሁሉ ስነ ጽሑፍ ሊሆን አይችልም፡፡ ዋናው ጥያቄ የሚሆነው ውቡን ከአስቀያሚው ለመለየት ምን ዓይነት ብልሃት እንጠቀም? የሚለው ነው፡፡

አንድ የጥበብ ሥራ “ውብ ነው” ወይም “አይደለም” ብለን ለመበየን ሥራው በታዳሚያኑ ዘንድ የሚያሳርፈውን የስሜት መለዋወጥ እንደ መመዘኛ ልንወስደው እንደምንችል የጻፉ አሉ፡፡ የሰው ልጅ ልቡና በሦስት ዋና ዋና የስሜት ደረጃዎች ማለትም ሀዘን - ስሜት አልባነት - ሀሴት (Grief – Indifference - Pleasure) መካከል በቋሚነት እንደሚመላለስ ፔንዱለም ነው፡፡ ኤድመን በርክ አንድ የጥበብ ሥራ ስሜታችንን ሀሴት ወደሚባለው ደረጃ አድርሶ የስሜት ከፍታ የሚያሳድርብን ከሆነ ውብ ልንለው እንችላለን ይላል፡፡ (ሀሴት ሲባል ግን “ተባዕቱ እና እንስቷ ገጸባሕርያት ከእንደገና ተገናኝተው በሰላም መኖር ጀመሩ” ብሎ የሚጨርስ ባለ መልካም ፍፃሜ ታሪክ መቋጫ ላይ ያለውን ዓይነት አይደለም)፡፡

ግን ደግሞ ስሜታችንን ወረድ አድርጎ ሀዘን ወደሚባለው የስሜት ዝቅታ ባያደርስ እንኳ አየት አድርገነው በስሜት አልባነት የምናልፈው ሥራም የውበት ሚዛን አይደፋም ይላል በርክ፡፡ እኔ ደግሞ ስሜትን ቆንጥጦ መያዝ የሚችል ነገር የመንፈስ ከፍታ የማሳደር አዝማሚያ ይኖረዋል እላለሁ፡፡ በሚገባ የተደረደሩ ዕቃዎችን፤ በሚገባ የተሰደሩ ጡቦችን፤ በትይዩነት የተቀመጡ እኩል ዋጋ ያላቸው ሳንቲሞችን፤ በስርዓት የተደራረቡ ባለ እኩል መጠን ክርታሶችን ወዘተ በምታዩበት ጊዜ ለአፍታም ቢሆን ልቦናችሁን እንዴት ወሰድ እንደሚያደርገው ታዝባችኋል? በእነኚህና እነኚህን በመሰሉ ስርዓታቸውን የጠበቁ አሰዳደሮች ውስጥ የምናየው (አይተንም ቀልባችን የሚሰረቀው) ቅጥ-አምባር (Pattern) ያለው አደረጃጀታቸውን ስለምናይ ነው፡፡

ቅጥ-አምባር በቀላል አባባል “ያማረ መልክ፣ አሰካክና አቀነባበር” ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄውም ከዚህ ቀጥሎ በሚገኘው ጥቅስ ውስጥ ተብራርቷል፡፡ የነማ ገ/ማርያም ባሰናዱት “የፍልስፍና ትምህርት፤ ቅፅ 2” ላይ ሲያብራሩት፤ “… ከአንድ የኪነጥበብ ተግባር በኩል የሚጠበቀውና የሚፈለገው መልኩ፣ ማለት አሰካኩና አቀነባበሩ ብቻ ያማረ እንዲሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ሙዚቃም እንደሆነ የሚፈለግበት፣ የድምፅን ዓይነቶች ሰብስቦና አቀነባብሮ አስማምቶም ለሰው ህሊና እንደሚያስደስትና ልብን እንደሚማርክ ዐይነት አድርጎ ድምጾቹን እንዲሰጥ ብቻ ነው” ቅጥ በሚገባ ተቀናጅቶ የተሰደረ ሁከት ነው (Pattern is an organized chaos እንደማለት)፡፡ ቅጥ መስጠትም ድብልቅልቁ ወጥቶ መላ ቅጡ የጠፋውን የእውነታ ዓለም ወግ በማስያዝ፤ በማደላደል በስነ ጥበብ ሥራ መልኩ አንፀባርቆ የማቅረብ ሂደት ነው፡፡ ውብ ብለን ልንጠራው የምንችለው ነገር ሁሉ መሠረቱን ቅጥ ላይ ካሳረፈ እንግዲህ አስቀያሚ የምንለው የሚዋቀረው በሁከት መሠረት ላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የውበቶች ሁሉ ቀላል፡- ቅጥ-አምባር ቅጥ አምባር ቀላሉ የውበት ዓይነት ነው፡፡

በግጥም ስንኞች ውስጥ፤ በሙዚቃ ቅንብሮች ውስጥ፤ ኬሮግራፊን በመሰሉ የክወና ጥበባት ውስጥ የምናየው ነገር ለዚህ አብነት ነው፡፡ ከተጠቀሱት ውስጥ ለምሳሌ የመጨረሻው (ኬሮግራፊ) ውብ ነው የምንልበት ምክንያት ተመሳሳይ ለሆነ ሙዚቃዊ ምት በተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ ምላሽ የሚሰጡ ከያኒያን ተሰልፈው ስለምናይ ነው፡፡ እዚህ ላይ የቅጥ አምባሩ ማዕከል መሰለፋቸው ቢሆንም ውብ የሚያደርገው ግን በተመሳሳይ ሰዓት ለአንድ ዓይነት ሙዚቃዊ ምት ምላሽ ሲሰጡ ለማየት የሚያስችለን ቅጥ አምባር ነው፡፡ ለዚህም ነው ኬሮግራፊ ከሌሎች ዓይነት ተራ ሰልፎች ተለይቶ ውብ የሚሆነው:: ቅጥ አምባር በክዋኔ ጥበባት ብቻ ሳይሆን በትረካ ውስጥም ይገኛል (ታሪክ ነገራው በልቦለድ፣ ተውኔት ወይም ፊልም ሊሆን ይችላል)፡፡ ትረካ ሁሉ መጀመሪያ፣ መካከል እና መጨረሻ አለው፡፡ በአንድ በተወሰነ ሰዓት (ወይም ገጽ) ላይ መነገር የተጀመረው ታሪክ አንድ ሌላ ጊዜ (ወይም አንቀጽ) ላይ ይፈፀማል፡፡ ሁሉም ትረካ ተጀምሮ የሚያልቅበት ቁርጥ ያለ ጊዜ አለው፡፡

ስለዚህም መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ትረካ ሊኖር እንኳ አይችልም፡፡ ስለዚህም የማንኛውም ትረካ ህላዌ በነኚህ ሦስት አውታሮች ተወጥሮ የቆመ ነው፡ መጀመሪያ - መካከል እና መጨረሻ፡፡ ይሄም በታሪክ ነገራ ውስጥ ቀላሉ ዓይነት ቅጥ አምባር ነው፡፡ ከትረካ ዘውጎች መካከል ዋነኞቹ ለሆኑት ለኮሜዲ እና ትራጄዲ፣ ከአሪስቶትል ጊዜ ጀምሮ የተቀመጠው የተለያየ የመዋቅር ስልት ቅጥ አለው፡፡ በዘውግ ኮሜዲ የሆነ ሥራ ከትራጄዲው የሚለዩት ባሕርያቱን የሚያገኘው ለአወቃቀሩ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች ነው፡፡ ስለዚህም ቅጣቸው የተለያየ በመሆኑ አንዱ ሌላውን ሊሆኑ አይቻላቸውም፡፡ ቅጥ አምባር በዚህ ረገድ ከውበትነት ባሻገር የማንነት መገለጫም ነው፡፡ ቅጥ-አምባርን “መልክና ሥነ-ሥርዓት” ብለው በሌላ አገላለጽ ያስቀመጡት የማነ ገ/ማሪያም፤ ከጥንት ፅርአውያን ፈላስፎች መካከል አሪስቶትልን ጠቅሰው እንዳሉት ደግሞ “…ውበት ያለው ከመልክና ከሥነ-ሥርዓት ላይ ነው፡፡ ከመጠን በላይ የሆነ ነገር ወይም ከደንበኛ መጠን ያነሰ፤ በአጭሩም መጠንን ከዚያም ሥነ-ሥርዓትን ያልተከተለ፤ ከእነዚህ ውጭ የሆነና የተዛባ ነገር ሁሉ በምንም ዓይነት አኳኋን ሰውን ሊማርክ አይችልም”፡፡

(ዝኒ ከማሁ) ውበት እንደ ተመልካቹ አይደለም! “ውበት እንደተመልካቹ ነው” የሚለው አባባል ውበት ሊመዘን፣ ሊሰፈርና ሊለካ የማይችል ሀሳብ እንደሆነ ቅድመ ግምት ይወስዳል፡፡ ነገር ግን ውበት በልኬት ተሠፍሮ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ሚዛን ላይ ሊቀመጥ የሚችል ማንኛውም ዓይነት አካል ደግሞ የመዛኙ ወይም ከተመዘነ በኋላ የሚያየው ሰው ማንንት ተፅዕኖ ሳያድርበት የቀደመ መጠኑን ይዞ ይቆያል፡፡ ቅጥ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሆነ ዓይነት ቅጥ ይዘው በተሰደሩ አካላት ውስጥ ትይዩነት (symmetry) አለ፡፡ ትይዩነት የሚፈጠረው ደግሞ የግራና የቀኙ ሚዛን ሲጠበቅ ነው (ግራና ቀኙ balanced ሲሆኑ)፡፡ ሚዛን ለመጠበቅም እኩል መሆን የግድ ነው፡፡ ሁለት የተለያዩ አካላት እኩል ናቸው ካልን ደግሞ በተዘዋዋሪም ቢሆን መዝነን አረጋግጠናቸዋል ማለት ነው፡፡ በዚህች ቀላል በመሰለች አባባል ተመልካች የውበትን መኖር አለመኖር ለመበየን ሙሉ መብት ተሰጥቶታል፡፡ እኔ ደግሞ ይሄን መብቱን እገፍፋለሁ - ውበት እንደተመልካቹ አይደለም፡፡

ውበት እና እውነት እውነታ (እንዲሁም ውበት) የግለሰቦች ልቡና (consciousness) ተገዢ አይደለም፡፡ አንድ ግለሰብ ወደደም ጠላም ህልውና አለ፡፡ ዐይኖቹን ቢጨፍን፤ ማሰቡን እንኳ ቢያቆም የማይጠፋ እውነት፤ የማይገረሰስ ዓለም መኖሩን አይገታውም፡፡ ከዚህ ሀሳብ ተቃራኒ እቆማለሁ የምንል ከሆነ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር እውነታ አለ ማለታችን ነው (እውነታ ግን ቢሊዮኖች ሆነን የምንጋራት ነጠላ ህላዌ ነች)፡፡ ጥንታዊው የማንነት ሕግ እንዲህ ይላል፡- “ሀ በቃ ሀ ነው” (A is A)፡፡ “ሀ”ን ማንም ይመልከተው ማን “ለ”ን ሊሆን አይቻለውም፡፡ ውብ የሆነ ነገር በሁሉም ሰው ዐይን ዘንድ ውብ ሆኖ ይታያል እንደማለት ነው፡፡ ውበት እውነታ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሀሳብ እንደመሆኑ፣ ሊኖረው የሚችለው አንድ አይነት ትርጓሜ ነው፡፡ የውበት ህላዌም በተመልካቹ ፍርድ ላይ ተስፋን አያደርግም፡፡

Read 4748 times