Saturday, 17 December 2011 08:59

አብዛኞቹ የዘመኑ ገጣሚያን ሙሾ አውራጆች ናቸው መባላቸውና የቀረበባቸው ማስረጃ…

Written by  ገዛኸኝ ፀ
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ ደራሲያን ዓላውቅ ያሉት የህገመንግስቱን አንቀፆች ወይስ የልማታዊ መንግስቱን ፖሊሲዎች?

የደራሲ ዳንኤል ወርቁ “ጥናት” አግባብነትና የማጠቃለያው አንድምታ …

ፈር መያዣ - ባለፈው ሣምንት “የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ወቅታዊ ሁኔታ ከኢ ፌዲሪ ህገመንግስት አኳያ” በሚለው በደራሲ ዳንኤል ወርቁ ጥናታዊ ጽሑፍ ዙሪያ መወያየታችን ይታወቃል፡፡ ጥናቱ፣ “በኢፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት ለሙያ ማህበራት፣ ለሚዲያና ሥነ - ጥበብ ባለሙያዎች በተዘጋጀው ብሔራዊ ኮንፈረንስ ላይ” (ከህዳር 15-16 ቀን 2004 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር) ከቀረቡ የመወያያ ጽሑፎች አንዱ ስለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ስለመቅረቡና ከሌሎች የመወያያ ጽሑፎች ጋር አብሮ ተጠርዞ ለታዳሚ ስለመታደሉ ባለፈው ሳምንት ተወስቷል፡፡

የጥናት አቅራቢው ደራሲ ዳንኤል ወርቁም በርካታ የትርጉም ሥራዎችን ለህትመት ያበቁ፣ ረጅምና አጫጭር ልቦለዶች የሳተሙ፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ለሀገራቸው የኪነጥበብ እድገት ይበጃል ያሉትን ሃሳብ ሁሉ በግልጽነትና በቀናነት የሚያቀርቡ፣ ትውልዱ የንባብ ባህል እንዲያዳብር የቻሉትን ያህል (በተለይ በህፃናት ላይ) እየሠሩ ያሉ፣ ተሸላሚ የፊልም ባለሙያ መሆናቸውን ተወስቷል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፉም የራሱ የሆኑ በጐ ጐኖች አሉት፡፡ ስሜታዊ የሚመስሉ መደምደሚያዎቹንም በቀናነት ተመልክተው ሊተላለፍ የተፈለገውን ቁምነገር ብቻ አጠንፍፈው ለሚያነቡም ብዙ ሊያተርፉበት እንደሚችሉ መመስከር መልካም ነው፡፡ አሁን ደግሞ፣ ሣምንት ያልተነሱ፣ ጥናታዊ ጽሑፉ አጽንኦት የሰጠባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች እንደሚከተለው በወፍ በረር እየቃኘን መወያየታችን እንቀጥል… “የዘመኑ ግጥሞች የሀዘን እንጉርጉሮዎች” የመባላቸው አግባብ በመወያያ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ገጣሚያንን በተለይ የዘመኑ ወጣት ገጣሚያን፣ መርዶ ነጋሪ፣ ሙሾ አውራጅ እንደሆኑ ተደርጐ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ለምሣሌ፣ “ከአንድ እጅግ ጨቋኝ ከሆነ ስርዓት [የደርግን ዘመን ማለቱ ነው] የተላቀቀ ህብረተሰብ የመጀመሪያ እርምጃው አፍኖ የያዘውን አየር በረጅሙ ተንፍሶ ማስወጣት ነው፡፡ ለዚህም ስነግጥም በጣም ፈጣኑ መንገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም የታየው ይሄው እውነት ነው፤ ሆኖም ግጥሞቹ ወደፊት እንደምንጠቅሳቸው የጀርመን ደራሲያን ሥራዎች ወገብን አስታጥቀው ወደ ተግባር የሚወስዱ አልነበሩም፡፡ ተመሳሳይ የሃዘን እንጉርጉሮዎች ነበሩ” (ገጽ 7) ይላል፡፡ እዚህ ላይ በአንድ አንባገነን ሥራ የታፈነን ልሣን በረጅሙ ለማስተንፈስ “ስነግጥም በጣም ፈጣኑ መንገድ ነው” የሚለው እንዴት ተረጋገጠ? ማንኛው የሥነጽሑፍ ባለሙያ በጥናት አረጋገጠው? ሌሎቹ የሥነ ጽሑፍ ዘውጐች እንዴት ተነፃፀሩ የሚሉት ጥያቄዎችን ማንሳት ቀላል ነው - ጥናቱ ግን አይመልስም፡፡ ወደ ሀዘንተኛ ግጥሞቹ እንመለስ፤ ጥናቱ፣ “ህገመንግስቱ ይዞት የመጣውን ነፃነት የመረዳት እና የመተርጐም ነገር በግጥሞቻችን ውስጥም ጐልቶ አይታይም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ግጥሞቻችን እጅግ በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ የተለመዱ የምሬት እና የሀዘን እንጉርጉሮ ግጥሞች ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም አስገራሚና አስደንጋጭ የሚያደርገው እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ ብዙዎቹ የዚህ ዘመን ደራሲዎች ወጣቶች መሆናቸው እና ከዚህም ጥቂት የማይባሉት ህገመንግስቱ ሲፀድቅ ከፍ ቢል የአንደኛ ደረጃ ተማሪ የነበሩ መሆናቸው ነው” (ገጽ 11) ይላል፡፡ ይህን አንቀጽ (ዝርክርክ የቃላት ድሪቶውን ትቶ) ያነበበ ሰው፤ ጥናቱ በርከት ያሉ የዘመኑ ወጣት ደራሲዎች የቃል ወይም የጽሑፍ መጠይቅ እንደቀረበላቸው ወይም የህይወት ታሪካቸውን የሚገልጽ የሰነድ ምርመራ እንደተደረገባቸው ያስባል - “ጥናታዊ” ጽሑፍ ስለሚያነብ፡፡ ግን፣ ጥናቱ “እጅግ ለቁጥር የሚያታክቱ የግጥም መድበሎች” እንዳጋጠሙት (ገጽ 12) እየገለጸና የአንዱን የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ስም እንኳ ሳይጠቅስ፣ “የዘመኑ ወጣት ደራሲያን” እድሜ ሳይቀር ወስኖ “ያስተነትናል”፤ “ግጥሞቹም…የአንባቢን የማንበብ ስሜት ከማሳደግ ይልቅ በደራሲያን ላይ አንባቢው ያለውን ከበሬታ እና እምነት ዝቅ” (ገጽ 14) እንዳደረጉ ያስረዳል፡፡ እዚህ ላይ ሌሎቹ ተጓዳኝ “ትንተናዎች” ትተን ግጥሞቹ “ሀዘንተኛና አንጐራጓሪ ናቸው” ከተባለበት ማዕዘን ላይ ቆመን ጥናቱ ያቀረባቸው ማስረጃዎችን ብንፈልግ አናገኝም፡፡ “እንደ የጀርመን ደራሲያን ሥራዎች ወገብን አስታጥቀው ወደ ተግባር የሚወስዱ” እንዳልሆኑ ግን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ምን ያህል የግጥም ሥራዎችና ወጣት ገጣሚያን እንዳሉ፣ የተወሰኑ በናሙናነት ተመርጠው ምን ምን ርዕሰ ጉዳዮችን እንዳቀነቀኑ፣ ምንም አይነት ግርድፍ እንኳ መረጃ ሳይጠቆም ደራሲያኑን ሙሾ አውራጅ ናቸው ማለት ይቻላል?በሌላ በኩል፣ ጽሑፉ ነገሮችን በስብጥር ለማየት የተሳነው ይመስላል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ያቀረበው መረጃ፣ በሌላ ቦታ ላይ ጥናቱ ያልፈለገውንና ያልተረዳውን ግን ተጠየቂያዊና ምክንያታዊ የሆነ ምላሽ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡ አንደኛው ገጽ ላይ አግባብ ያለው ማስረጃ የሆነው ጉዳይ፣ ከሌላኛው ገጽ ጋር ተናቦና ተሰናስሎ ባለመቅረቡ ሲከሽፍ ይታያል፤ ባለበት ቦታ ከሽፎ ቢቀር ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ሌላ ፈታኝ ጥያቄ ያጭራል፡፡ የተነሳንበትን (የደራሲዎቻችን መርዶ ነጋሪነት፣ ሀዘን አንጐራጓሪነት) ሳንረሳ፣ አንድ ማንፀሪያ ዋቢ እናጣቅስ፡

 

ጥናቱ፣ “በህገ መንግስታችን አንቀጽ 91 ላይ መንግስት ጥበብን ማሳደግ ግዴታ አለበት ይላል፡፡ ይህ አንድ በመቶ እንኳን አንባቢ በሌለበት ሃገር፣ ደራሲው ዳቦውን ለማግኘት ቀንና ሌሊት ደፋ ቀና በሚልበት አገር፣ እጅግ በዛ ቢባል አንድ መጽሐፍ በአማካይ 3000 ብቻ በሚታተምበትና እና ከዚህም ላይ ደራሲው ለጥቂት ዳቦዎች ብቻ በሚከፈለው አገር ይህ አንቀጽ እጅግ አስፈላጊ እና በተግባርም ሊተረጐም የሚገባው ነው” (ገጽ 23) ይላል፡፡ ውድ አንባቢያን ከላይ ያጣቀስኩትን አንቀጽ ደግማችሁ እንድታነቡት በትህትና ብጠይቅስ? ልብ በሉ! ጥናቱ እስከ አሁን ሲወተውተው የነበረውን ወቀሳውንና ምክሩን በዜሮ ያባዛው አይመስላችሁም? ጥናቱ የጀርመኑን ደራሲ የሃይነሪሽ ቦል “የዛን ጊዜ ዳቦ” የሚለውን ልቦለድ ጠቅሶ፣ የጀርመን ደራሲያን ጠንካራ ገፀባህሪ ቀርፀው፣ “ኑሮን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ተጋድሎ” በተደጋጋሚ ያወድሳል (ገጽ 9)፡፡ በተቃራኒው የዘመኑ የኢትዮጵያ ደራሲያን (ገጣሚያን) ግን የደሃ አገራቸውንና “የልማታዊ መንግስታቸውን” ተጨባጭ ሁኔታ የሚገልፁ፣ ድህነትን በጥንካሬ እንዴት ማለፍ እንደሚቻል የሚያመላክቱ ሥነጽሑፎችን (በተለይ ግጥሞችን) መፃፍ እንዳቃታቸው በተደጋጋሚ በአጽንኦት ይገልፃል - ጥናቱ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ጥናቱ፣ የጀርመን ደራሲያን የልቦለድ ገፀ ባህሪ ቀርፀው ድህነትን ለማሸነፍ በመጣራቸው በተደጋጋሚ ሲያውድሳቸው እና እንደ አርአያ ሲቆጥራቸው ታይቷል፤ በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ግን በልቦለድ ሳይሆን በተጨባጭ እውነት “ዳቦ ለማግኘት ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና ማለታቸው” በጀርመኖቹ ትይዩ ስናናብበው ዋጋ አጥቷል፡፡ ወደ ዋናው ጉዳያችን ስናቀና፣ “የዘመኑ ግጥሞች ሀዘንተኛና አንጐራጓሪ መሆናቸው እንዴት ታወቀ?” የሚለውን ምላሽ የነጠፈበት ጥያቄ ማንሳት ትተን ሌላ ተጠየቅ ልናነሳ ግድ ይለናል፡፡ ለመሆኑ የዕለት ዳቦውን ለማግኘት ሌት ተቀን መባከን ግድ የሚለው፣ ለፍቶ ደክሞ ለጥቂት ዳቦዎች ብቻ የሚከፈለው የዘመኑ ኢትዮጵያዊ ደራሲ (ገጣሚ)፣ በወረቀት ሁዳዱ ሀዘንና እንጉርጉሮ ቢዘራ፣ ብዕሩ ሙሾ ቢያወርድ ምንድን ነው ሀጢያቱ? የዕለት እንጀራውን ያላገኘ ደራሲ ብዕሩ እንዴትን ብሩህ ተስፋ ሊያፈነጥቅ ይቻለዋል? ጥናቱስ ቢሆን እውነተኛ ደራሲ የማህበረሰቡን ተጨባጭ ኑሮ ማሳየት አለበት ይል የለ (ገጽ 16)? እነዚህን ጥያቄዎች ብቻ ስናነሳ፣ ጥናቱ እርስበርስ የማይናበቡና የማይመጋገቡ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳ ደፈር ያሉ ወቀሳዎችን ለመሰንዘር የተጣደፈ ያስመስለዋል፡፡ ጥናቱ፣ የሥነ ጽሑፍ ደራሲያኑን ድክመት ለማንፀር የሌሎች ኢ-ልቦለድ ጽሑፎችን ህትመት ሁኔታ በግርድፉ ተመልክቷል፡፡ የተለያዩ የጦር ሜዳ ውሎዎች፣ ያለፉት መንግስታት ታሪኮች፣ ግለታሪኮች፣ የትግል ታሪኮች፣ የፓርቲ ታሪኮች፣ የተለያዩ ሀይማኖታዊ መፃሕፍት፣ ጽንፈኛ የእምነት መጽሐፍት፣ የተለያዩ የሥነ ልቦና፣ የወሲብ መፃሕፍት፣ ካለምንም ሳንሱር መታተማቸውን ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል፣ “ህገመንግስቱ ይዞት የመጣውን መብትና ነፃነት ተጠቅሞ ጐላ ያለ ሥራ የሰራ ደራሲም ሆነ ድርሰት ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል” (ገጽ 12) ይላል፡፡ በተለይ ህገመንግስቱ ሲፀድቅ፣ “በሚያስገርም ሁኔታ ከፍ ቢል የአንደኛ ደረጃ ተማሪ የነበሩ” (ገጽ 11) የዘመኑ ደራሲያን፣ የግለ ታሪክና የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ፀሐፊዎቹን ያህል ቀርቶ፣ ትንሽ ነገር እንኳ አለመፃፋቸውን በአጽንኦት ተናግሯል፡፡

እዚህ ላይ ጥያቄ እናንሳ? የዘመኑ ደራሲ ካለፉት ትውልዶች መፃሕፍት የሚማረው ምንድን ነው? እነሱ ሽብርና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከተውት ይሆን? ወዘተ ብሎ ጥናቱ፣ መጠየቅና የተወሰነ ነገር ማለት ይችል ነበር፤ ይገባልም፡፡ የዛሬው ደራሲ፣ ህገመንግስቱን ያረቀቁት፣ ያፀደቁትም ሆነ እንደገና “ህገ አራዊት” እያሉ ጭምር ግራ የሚያጋቡት ያለፉት ስርአት ተወላጆች በምክንያት ብቻ ሳይሆን በጭፍን ጥላቻና ግትርነት እርስበርስ ሲጠላለፉ የሚያሳዩትን መፃሕፍታቸውን ማንበቡ ተጽእኖ ፈጥሮበት ይሆን? ሊባል ይችላል፡፡ ዛሬም ድረስ የሃገሪቱን ፖለቲካ ተቆጣጥረው እጣ ፈንታውን የሚወስኑት ህገመንግስት አርቃቂና አጽዳቂ ወላጆቹ፤ ከሃገር ጉዳይ ይልቅ የራስ ቅንጣት ዝና ሲያብከነክናቸው፣ ምቀኝነትና ግትርነት ሲያጠቃቸው ታዝቦ ቢሆንስ? ለምሣሌ ስዬ አብርሃ በፃፉት “ነፃነትና ዳኝነት” መጽሐፍ እና ኮ/ል ኢያሱ መንገሻ በፃፉት “መለስ ዜናዊ እና የህወሓት የትግል ጉዞ” መጽሐፍ ውስጥ የተወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንኳ የተለየና የሚቃረን ሰብዕና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ህገመንግስቱ ሲፀድቅ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ የነበረው የዘመኑ ደራሲ፣ እሱ ሊያውቃቸው ከሚችለው በላይ እነ ኮሎኔል ኢያሱ እንደሚያውቋቸው ይረዳል፡፡ ሁለት የትግል ጓደኞቻቸው በተቃረነ መንገድ ሰብዕናቸውን ሲገልፁ ሲያነብ ለምን? ይላል፡፡ ዘመነኛው ደራሲ፣ በእድሜ ብቻ ሳይሆን በአዕምሮውም ካልበሰለ፣ በጥራዝ ነጠቅ፣ በጆሮ ጠገብ እውቀት ወይ ስዬን ወደ ኢያሱን ደግፎ ይገጥማል - የዘመኑን ግጥም፡፡ አእምሮው ትንሽ ከጐለበተ በእሱ እድሜ የተረዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን በትክክል ማን እንደገለፃቸው ያለውን “እውነት” የግጥሙ ማዕከላዊ ማጠንጠኛ አድርጐ ይገጥማል፤ አዕምሮው በወጉ እያደገ የመጣ ብልህ ከሆነ ደግሞ፣ ደጋግሞ ይጠይቃል፡፡ ከዚያ፣ አቶ መለስ አንድ ሰው ሳሉ ሁለት የትግል ጓዶቻቸው በተቃራኒ ሰብዕና ሲገልጿቸው ሲያይ ዘመነኛ ገጣሚው አንድ ሀቅ ያረቃል፡፡ ቢያንስ ከሁለት አንዱ ደራሲ ስሜታዊ ሆነው እንደፃፉ፣ የተሳሳተ መረጃ ለትውልዱ እንደከተቡ ያረጋግጣል፤ ህገመንግስቱን አርቅቀው ያፀደቁት አባቶቹ ዛሬም በዚህ እድሜያቸው እንደሚዋሹ ግትር ወይም አድር ባይ እንደሆኑ ሁሉ ያውቃል፡፡ ይህ ደግሞ ከማሳዘን አልፎ ሊያሳፍረው ሁሉ ይችላል፤ ወዲያው፣ “የከሸፉ ደራሲዎች” ብሎ ማህበራዊ ሂስ ያለው፣ ሀዘንተኛ እንጉርጉሮ ይጽፋል፡፡ የገጣሚው ዘመነኛ ዜጋ፣ ፅንፈኛ የሀይማኖት መፃህፍትንም ያነባል፡፡ ደራሲ እንኳን የእለት እንጀራውን ማግኘት እየከበደው፣ ብዙ ድሆች ባሉበት ሀገር ሀይማኖታዊ መፃሕፍት የውጥረት ማዕከል ሢፈጥሩም ያያል፡፡ በዚህ ጊዜ ቀሽም ገጣሚ እሡ የሚያምንበት ሀይማኖት በመወቀሱ ወይም በመሠደቡ አዝኖ ሀዘንተኛ ግጥም ላምላኩም፣ ለኛም ይጽፋል፡፡ ብልህና የምር ገጣሚ፣ ሀገሩ የራሷን ሆድ ለመሙላት ማምረትና ያመረተችውንም በፍትሃዊነት መከፋፈል ሢገባት፣ እሷ ግን የዕለት ጉሮሮዋን በማይዘጋ “ሀይማኖት” ከመቦዘኗ በላይ መከራዋን በገዛ እጇ እየጠራች መሆኑን ሢረዳ የምር ያዝናል፡፡ የገጣሚ ነፍሡ “ግጠም ግጠም” ትለዋለች - ይገጥማል፤ ብዕሩን ከወረቀቱ፣ አይነ ልቦናውን ከህገ ልቦናው ይገጥማል - ሀዘንተኛ እንጉርጉሮ ግጥም ይገጥማል፡፡

ጥናቱ አውቆም ይሁን ሣያውቅ የጠቀሣቸው መረጃዎች ሢፈከሩ (ሢተረጐሙ)፣ የዘመኑን ገጣሚ እንዲያንጐራጉር፣ ሙሾ እንዲያወርድ የሚያስገድዱ ይመስላሉ፡፡ በርግጥ የዘመኑ ግጥሞች፣ ምን ያህል የሀዘን እንጉርጉሮ እንደሆኑ ጥናቱ በማስረጃ አላስተነተነም፤ እኔም ሀዘን አንጐራጓሪ ስለመሆንና አለመሆናቸው በጥናት አላረጋገጥኩም፡፡ ጥናቱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የዘረዘረው ሃገራዊ እውነት ግን የዘመኑ ትውልድ የሀዘን ግጥም እንዲያንጐራጉር ሊያደርገው ይችል ይሆናልና ከእዚህ አንፃርም ጥናቱ የተለያዩ ጥናታዊ ሣይሆኑ ምናልባታዊ  ሀሣቦችን እንኳ ቢያመላክት መልካም ነበር ለማለት ነው፡፡

 

“ጥናቱ” የጥናትና ምርምር መርሆች ስለመከተሉ

በጥናቱ ውስጥ በግልፅ የተቀመጠ ዓላማ አልሠፈረም፡፡ ይሄ ነው የሚባል ያጠናን ዘዴ አለመከተሉ ደግሞ ለፈርጀ ብዙ እንከኖች መፈጠር ምክንያት የሆነ ይመስላል፡፡ የጥናቱ ወሠን አይታወቅም፤ ሢፈልግ ልቦለድ ሣይፈልግ ኢልቦለድ፣ ሲፈልግ በሥነ ጽሁፍ ቅንብብ፣ ሣይፈልግ በኪነጥበብ ቅንብብ፣ ሢፈልግ የቅርብ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሣይፈልግ የሩቅ የከሸፉ መረጃዎችን ያጣቅሣል፡፡ በአማርኛ የተፃፉ የኢትዮጵያን የሥነ ጽሁፍ ሥራዎች ለማጥናት የሞከሩት ቶማስ ኬን ሥላልገባቸዉ ብቻ ሣይሆን፣ ግራ ስለገባቸዉ ጭምር ከ35 ዓመት በፊት በድፍረት የሠነዘሩትን ሀሣብ አጣቅሦ የዛሬዎቹን ደራሢያን ለማንኳሰስ የተጠቀመበት ስሜታዊነት ሢታይ ጥናቱ መናኛ መረጃዎችን ተጠቅሟልም ማለት የሚቻል ይመሥላል፡፡

በማጠቃለያው ጐልቶ የታየው ህገመንግስቱንና መንግስትን አንድ አድርጐ የመመልከት አዝማሚያ፣ የዛሬው መንግሥት በሌላ ቢተካ እንኳን ህገመንግስቱ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሠበውን ዘላቂነት የሚፈታተነው ይመስላል፡፡ ደራሲያኑም ዓላውቅ ያሉት የህገ መንግስቱን አንቀፆች ነው ወይስ የልማታዊ መንግስቱን ፖሊሲዎች? የሚል ጥያቄ ሁሉ ያጭራል፡፡ በዚሁ ትይዩ፣ የጥናቱ አጠቃላይ መንፈስ ደግሞ ደራሲያን ህገመንግስቱን ሊያውቁ፣ ሊያነቡ ይገባል ከሚለው በላይ፣ የህገመንግስቱን እሴቶች ሁሉ የማስተዋዋቅ ግዴታ እንዳለባቸው ጭምር አቋም የያዘ ይመስላል፡፡ ይህን መንፈሡን ከአጠቃላይ ከጥናቱ ድምፀት መረዳት የሚቻል ይመስላል፡፡

ይህ አካሂያድ ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከህገመንግስቱ (ከራሡ ጋር) ጭምር ግጭት ይፈጥራል፤ ህገመንግስቱ በአንቀጽ 29 ላይ ማንኛውም ሰው (ደራሲያንም ማለቱ ነው) ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሣቡን የመግለጽ፣ በፈለገው ሚዲያ የማሠራጨት በሥነ ጥበብም (በድርሠትም ጭምር) የመፃፍ ሰፊ ነፃነት ይሰጣል፡፡ ለዚህ ነው፣ ህገመንግስቱን እንኳን ሣያውቁት ለተቀመጡት (ጥናቱ ያለው እውነት ከሆነ ማለት ነው) ቀርቶ አውቀው ለሚጠሉትና እንዲቀየር ጭምር ለሚታገሉት (የሚታገሉ ድንገት ካሉ) መብት ይሠጣል ያልነው፡፡ አጠቃላይ ከሆነ ከዚህ መንግስታዊ መብትና ነፃነቶች አንጻር ሢጤን፣ አንድ ጠርዝ ላይ ቆሞ ደራሲያንን የህገ መንግስቱ ወገንተኛ እንዲሆኑ ለማግባባት ወይም “በጐ ተፅዕኖ” ለመፍጠር መሞከር ጠቀሜታው (Relevance) ምን ያህል ነው? የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ሊያስነሣ ሁሉ ይችላል፡፡

ጥናቱ በባለጊዜው ትውልድ (በዘመኑ ደራሲያን) ላይ መርዶ ለመንገር ለምን ፈለገ?

በተለያዩ አጋጣሚዎች ያለ በቂ ማስረጃ፣ የዘመኑን ትውልድ ዝቅ አድርጎ የመመልከት፣ አቅመ ቢስ እንደሆነ የመወትወት አዝማማሚያዎች ይታያሉ (ይህ የጥናት ውጤቴ ሣይሆን የትዝብት ነፃ አስተያየቴ ነው)፡፡ በዚህ ጥናት በዘመኑ ደራስያን ላይ የቀረበው ወቀሳ አከል ማብራሪያም የዚሁ ዘመነኛውን ትውልድ ዝቅ አድርጐ የመመልከት አባዜ አካል ይመስላል፡፡ አሊያ፣ ቢያንስ በደራሲ በተሠራ ጥናት ላይ ስለ ዘመኑ ደራሲያን አንዳንድ ገነው የወጡ ተጨባጭ ጥረቶችና ተግባሮች ይጠቆሙ ነበር፡፡ ለማንኛውም አሁን ግን ይህን ንግግር ተመልከቱ …

“ሀገሪቷ ከብዝበዛና ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ የሚቻለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀት በራሷ ልጆች አእምሮ ውስጥ ገብቶ ማዕድኖችዋና ውድ የመሬት ውስጥ ሀብቶቿ በራሷ ልጆች በልፅጐ በቅፅበት የምታድግበትን መንገድ ስናፈላልግ መሆኑ ገባኝ፡፡ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዊያን ማድረግ የሚቻለው ትክለኛው የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ትክክለኛው የቴክኖሎጂ መሣሪያ በራሷ ልጆች እጅ ሲገባ መሆኑን ተረዳሁ” (ገጽ 192)፡፡

“የዚችን ሃገር ትክክለኛ ብልጽግና የምትመኝ ከሆነ ከሰሜን እስከ ደቡብ … ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የተዘረጉ የባቡር ሀዲዶች ከሁሉም በፊት እንዲኖራት ማለም አለብህ” (ገጽ 195)፡፡

እነዚህ ንግግሮች የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ወይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አይደሉም ብሎ መከራከር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ግን የነሡ ቀጥተኛ ንግግር አይደሉም፡፡ ይልቁንም ህገ መንግስቱ ሢፀድቅ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረ በአንድ ወጣት ባለ ራዕይ ስኬታማ ደራሲ ከተፃፈ መጽሐፍ የተወሠዱ፣ ናቸው፡፡ ወይም ጥናቱ ከ3ሺ በላይ ኮፒ አይታተምባትም ባላት በዛሬዋ ኢትዮጵያ (ባለኝ ግርድፍ መረጃ መሰረት) ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ130 ሺህ ኮፒ በላይ (ከዋጋው እጥፍና ከዛ በላይ በሆነ ዋጋ ሁሉ) ከተሸጠና የትውልዱን የንባብ ዛር አስነስቷል ከተባለው ከዴርቶጋዳ መጽሐፍ የተወሠዱ የባለርዕይ ትውልድ የርዕዩ ክታቦች ናቸው፡፡ ጥናቱ፣ ዴርቶጋዳን ከውጭ የተኮረጁ፣ በውጭዎች ስልት የተፃፉ ብሎ እንደነገሩ አሽሙሮት ከሚያልፍ፣ የወጣቱን ደራሲ ስኬት ጭምር ሊመሠከርበት የሚችልበት አጋጣሚ ነበር - በቀናነት፡፡ መጽሐፉን የሚያሳትምበት ያልነበረው፣ (በ20ዎቹ እድሜ ክልል ያለውን ደራሲ) ዛሬ በተጨባጭ ለሌሎች ሥራ መፍጠር የቻለ ወጣት ባለሃብት የሆነበትን ሀቅ መመስከር ይቻል ነበር፡፡ ዛሬ ማሳተሚያ ላጡ ሌሎች ወጣት ደራሲያን መከታና ኩራት እስከ መሆን ደርሷል፤ ለዚህ ሁሉ የበቃው ደግሞ ህገመንግስቱ በፈቀደለት መሠረት ሀሣቡን በነፃ ገልፆ፣ ርዕዩንና ተስፋውን ቀድሞ በከተተበት መጽሐፉ ሽያጭ መሆኑ ደግሞ ሌላ ስኬት ነው፡፡ እኔ እስከ አሁን ባለኝ መረጃ መሠረት በሃገሪቱ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ የልቦለድ መጽሐፍ ጽፎ በአንድ አመት ወደ ወጣት ባለሃብትነትና ኢንቨስተርነት የተቀየረ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ (የዘመኑ ትውልድ ተምሣሌት) ይመስለኛል፡፡ ታዋቂው ተመራማሪና የሥነጽሁፍ ባለሙያ ዶ/ር ታየ አሰፋ፣ አንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጁት የአፍሪካ ደራሲያን አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ፣ “Pseudo – Science /Technology and Politics in Dertogada and Ramatohara” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፤ የይስማከ ወርቁን በሣይንስ ተሸርቦ የቀረበ የትውልዱን የፖለቲካ ርዕዩን አርቆ አሣቢነቱን መስክረውለታል፡፡ እኔም የነፍስህን መስክር ከተባልኩ ደግሞ፣ ለ”አዲሲቷ” ባለ ርዕይ ሃገር ተስፋ ከሚሆኗት ወጣት ትውልዶቿ መካከል አንዱ የሆነው ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፤ ሃገራዊ ሽልማት የሚያስፈልገው የትውልዱ ጀግና ነው ማለት ይቻላል፡፡ (መጽሐፉ እንከን አይወጣለትም አላልኩም፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መድረክ ያቀረብኩትን መጠነኛ ጥናታዊ ጽሁፍ መመልከት ይቻላልና)፡፡ በመጨረሻ፡- ደራሢ ዳንኤል ወርቁ፣ ይህን “ጥናታቸውን” የጊዜ እጥረት ባለበት ሁኔታ በችኮላ ያቀረቡት ይመስለኛል፡፡ አብዛኞቹ ድክመቶችም በጊዜ እጥረት የተፈጠሩ እንጂ ከእውቀት ማነስ የመጡ ነው የሚል አስተያየት ለመስጠት አልደፍርም፤ ፍፁም ስህተትም ነውና፡፡ አንባቢዬም ያልኩትን እንደምትጋሩት ተስፋ አለኝ፡፡ እናም ደራሲው በሌሎች ተመሳሳይ መድረኮች ጊዜ ከፍለው በማስረጃና በመረጃ ጠብሰቅ ያሉ ሌሎች ጥናታዊ ሥራዎችን እንደሚያቀርቡልን ያለኝ እምነት ፅኑ ነው፤ ይህ አባባል ደግሞ ትሁት ለመሆን ብዬ ያቀረብኩት አይደለም፤ ከጠንካራ ሥራቸውና ብቃታቸው ጀርባ ጨምቄ ያጠነፈፍኩት እውነት ነው እንጂ፡፡ የዚህ ሂሣዊ መጣጥፍ ዋና ዓላማም ይኸው ብቻ ነው - በቃ፡፡

 

 

 

Read 5917 times Last modified on Saturday, 17 December 2011 09:05