Saturday, 10 May 2014 12:00

በሸራተን ተጀምሮ በሂልተን የተጠናቀቀው የንግድ ም/ቤት ምርጫ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

          የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 6ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ቀን ከቆረጠ፣ ቦታ ከመረጠ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሰረት ነው፣ ባለፈው ሃሙስ የጉባኤው ተሳታፊዎች ማልደው ወደ ሸራተን አዲስ ሆቴል ያመሩት፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ንግድ ሚኒስትር በአቶ ከበደ ጫኔ የመግቢያ ንግግር፣ ከጧቱ 2፡30 የተከፈተው የምክር ቤቱ 6ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የአመራሮችን ምርጫ ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎች ይዞ ይጀመር እንጂ፣ እንደታሰበው በወጉ መቀጠል አልቻለም፡፡ የምክር ቤቱን ቀጣይ አመራሮች ለመምረጥ የተያዘው ዕቅድ፣ በተሰብሳቢዎች ዘንድ ጥያቄ ተነሳበት፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎች ሀሳብ ለሃሳብ መግባባት ተስኗቸው፣ እርስበርስ መሟገትና መከራከር ያዙ፡፡ የአለመግባባቱ መንስኤ የሆነው ደግሞ፣ “ምክር ቤቱ በ1999ዓ.ም በንግድ ሚኒስቴር ያፀደቀው መተዳደሪያ ደንብ ከሚፈቅደው ውጭ፣ በዳሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ብቻ የአመራሮች ምርጫ በየሁለት አመቱ እንዲከናወን መደረጉ አግባብ አይደለም” የሚል ሃሳብ ከተሰብሳቢዎች መነሳቱ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ በተለይም የምክር ቤቱ አባላት የሆኑትን የሃረሪ፣ የሶማሌ፣ የቤኒሻንጉል፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎችን ሲያወዛግብ ነበር ያረፈደው፡፡ የእነዚህ ክልሎች ተወካዮች “መተዳደሪያ ደንቡ እኛን አይወክለንም፤ መሻሻል አለበት፤ ደንቡ ተግባራዊ መሆን ያለበት ከዛሬው ምርጫ ጀምሮ ነው” በማለት ያንጸባረቁት አቋም፤ በቀድሞ የምክርቤቱ የዳሬክተሮች ቦርድ አባላትና በዕለቱ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲመሩ የነበሩ አስራ ሁለት አባላትን ጭምር ያጨቃጨቀ ጉዳይ ነበር፡፡ ቅሬታ ያቀረቡት ክልሎች፣ ምክነያታቸውን እንዲያስረዱ በተጠየቁት መሰረት፣ የትግራይ ክልሉ ተወካይ “ደንቡ የክልሎችን መብትና ግዴታ ያካተተ ባለመሆኑ ነው፣ እኛን አይወክልም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌሎችም ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ ደንቡ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሁን አይሁን የሚለው አወዛጋቢ ጉዳይም፣ የኋላ ኋላ ጠቅላላ ጉባኤው በድምጽ ብልጫ እንዲወስን ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ “ደንቡ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሁን” የሚለውን በአብላጫ ድምፅ አጸደቀ፡፡ ቀጣዩ ጉዳይም በደንቡ መሰረት የምክር ቤቱን አመራሮች ምርጫ ማካሄድ ሆነ፡፡ ለእጩነት የቀረቡት የምክር ቤቱ አባላቶች ከታወቁ በኋላ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ምርጫው መካሄዱ ሶስት ሰዎችን ከዕጩነት እንዲገለሉ አድርጓል፡፡ ለፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንትነት ከታጩት አስር ሰዎች ውስጥ ከድሬዳዋ ከትግራይና ከአዲስ አበባ የመጡ ሶስት ተወዳዳሪ እጩዎች በደንቡ መሰረት የተገለሉ ሲሆን፤ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞንም፣ “እኔ ደክሞኛል ሃላፊነቱን ለሌላ ተተኪ ሰው ማስተላለፍ ነው የምፈልገው” በማለት እራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል፡፡ ወ/ሮ ሙሉ በምርጫው ላለመሳተፍ ያሳለፉትን ውሳኔ አስቀድመው በግልጽ በመናገራቸው፣ ጉዳዩ ያስደነገጣቸውና ወ/ሮ ሙሉ በሃላፊነታቸው መቀጠል ይገባቸዋል ብለው ያሰቡ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት፣ እግራቸው ስር በመውደቅ መለመናቸውን ቀጠሉ፡፡

ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ግን፣ ውሳኔያቸውን ከዘጠኝ ወራት በፊት ጀምሮ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲገልጹ እንደነበር ጠቁመው፣ በዕለቱ በምርጫው ላለመሳተፍ ከያዙት አቋም ንቅንቅ እንደማይሉ ተናገሩ፡፡ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት፣ አቶ ታደሰ ገና ከኦሮሚያ፣ አቶ ጌታቸው አየነው ከአማራና አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ከደቡብ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ነበሩ፡፡ ለምክትል ፕሬዝዳንተነት የታጩት ደግሞ፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ም/ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንን፣ አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ከትግራይ ንግድ ምክርቤት እንዲሁም አቶ ወንድማገኝ ነገራ ከአዲስ አበባ ነበሩ፡፡ የአመራር አባላትን የመምረጥና የስድስት ወር ሪፖርት አድምጦ የመወያየት አጀንዳ ይዞ፣ ከጧቱ 2፡30 የተጀመረውና በውዝግብ ታጅቦ የቀጠለው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ ወደ ምሽት ተሸጋገረ፡፡ በዕጩነት በቀረቡት ተወዳዳሪዎች ላይ ድምጽ የመስጠቱ ስነስርዓት ተጠናቋል፡፡ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ላይ፣ የሸራተን አዲስ ሰራተኞች ወደ ጉባኤው አዘጋጆች በመቅረብ አንድ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ “በሆቴሉ ጠቅላላ ጉባኤያችሁን ለማካሄድ ያስያዛችሁት ሰዓት አልቋል፤ ቦታው ለሌላ ጉዳይ ስለሚፈለግ እንድትለቁልን በአክብሮት እንጠይቃለን!” የሚል፡፡

ይሄን ተከትሎም፣ ተሰብሳቢዎች የሰጡት የምክር ቤቱ አመራሮች ምርጫ ድምጽ ተቆጥሮ ውጤቱ ሳይታወቅና አሸናፊው በይፋ ሳይገለጽ፣ ጉባኤው ተበትኖ ተሰብሳቢዎች የሸራተን አዲስን ግቢ ለቀው ለመውጣት ተዘጋጁ፡፡ ቀጣዩ የምሽት ጉዞ፣ ወደ ሂልተን ሆቴል ነበር፡፡ በሁኔታው የተበሳጩ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ እንደምንም ስሜታቸውን ቻል አድርገው ወደ ሂልተን ሆቴል ቢያመሩም፣ በዚያ የጠበቃቸው ሁኔታም የበለጠ ቅሬታንና ንዴትን ነበር የፈጠረባቸው፡፡ ሂልተን ሆቴል ለምክር ቤቱ ድንገተኛ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው፣ ግቢው ውስጥ በሚገኝ ገላጣ ስፍራ ላይ ስብሰባ እንዲያደርጉ በመፍቀድ ነበር፡፡ ይህም በርካቶቹን የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፍተኛ ተቃውሞ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ አስገድዷቸዋል፡፡ የጉባኤውን ዝርክርክነትም አፍ አውጥተው ሲተቹ ተደምጠዋል፡፡ “ሸራተን የተደረገው የድምፅ መስጠት ስነ-ስርአት ተጠናቆ በአግባቡ ውጤት ሳይነገር፣ ወደ ሂልተን ሂዱ መባላችን አግባብ አይደለም፡፡ በምክር ቤቱ ይህንን አይነት ዝርክርክነት ስመለከት፣ ዛሬ ሶስተኛ ጊዜዬ ነው” ብለዋል፣ ከትግራይ ክልል ተወክለው በጉባኤው ላይ ተሳተፉት አቶ ገብረማርያም በወቅቱ ቅሬታቸውን ሲገልጹ፡፡ በሂልተን ሆቴል ቅጽር ግቢ በተበታተነ ሁኔታ በአሰልቺ ስሜት ውስጥ ሆነው የምርጫውን ውጤት መጠባበቅ የጀመሩት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ተጨማሪ ከሁለት ሰዓታት በላይ ጊዜን መጠበቅ ነበረባቸው፡፡

በዚህ ሁኔታ እኩለ ሌሊት አለፈ፡፡ ከሌሊቱ 6፡20 ሲል ግን፣ የምርጫውን ውጤት ያዘጋጁት ሰብሳቢዎች፣ በሆቴሉ አንድ ጥግ ላይ ተሳታፊው በሚገባ ባልሰማበት ሁኔታ ውጤቱን ገለጹ፡፡ ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል፣ አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በ62 በመቶ ድምፅ በማግኘት፤ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ከቀረቡት ደግሞ፣ አቶ አበባው መኮንን በ72 በመቶ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸው በስሚ ስሚ በየተሳታፊው ጆሮ ደረሰ፡፡ ዘጠኝ የዳሬክተሮች የቦርድ አባላትም በጠቅላላ ጉባኤው ተመረጡ፡፡ የምርጫ ውጤቱ መታወቁን ተከትሎ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት የቀድሞ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ “እኛ የጠበቅነውና ያሰብነው ባይመረጥም፣ የህዝቡን ድምፅ ማክበር ግድ ይላል፡፡ የተመረጡት አመራሮች ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ጠንካራ ስራዎች በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል ማስቀጠል አለባቸው” ብለዋል፡፡ በሆቴሉ ቅጽር ግቢ ከአንድ ዛፍ ስር የተሰባሰቡት የዕለቱ ተመራጭ አመራሮች፣ በተተራመሰ ሁኔታ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ቃለ መግባታቸውን ተከትሎም፣ አዲሱ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት እንዲህ ሲሉ ተናገሩ - “ምርጫው ፍትሃዊ ነው፤ መንግስትም ከእኛ ሊማር ይችላል ብዬ አምናለሁ!”፡፡

Read 3196 times Last modified on Saturday, 10 May 2014 12:52