Saturday, 03 May 2014 13:23

“ከዝንጋታና ከአለማስተዋል የተነሳ የዘለልሁት ታሪክ ከተገኙ…ጥፋቴን ተውልኝ”

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(0 votes)

ርዕስ፡- የአፄ ሠርጸድንግል ዜና መዋዕል
 (ግዕዝና አማርኛ)
ተርጓሚ፣ አዘጋጅና አርታኢ .. ዓለሙ ኃይሌ
አሳታሚ … በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ምርምርና ማዕከላዊ ዶክሜንቴሽን መምሪያ
የህትመት ዘመን …. ሰኔ 1999 ዓ.ም
ህትመት … ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት
 (አዲስ አበባ)
የገፅ ብዛት … 224 (ግዕዙ ወይም አማርኛው ብቻ)
የሽፋን ዋጋ … አልተገለጠም (አልተጻፈበትም)

ቅድመ ኩሉ
“የዚህ መጽሐፍ ባለቤት (ዜና መዋዕል ጸሐፊው) እንዲህ ይላል፤ ይህን መጽሐፍ የምታነቡና የምትሰሙ ዐዋቂዎች ወንድሞቼ ሆይ! ከዝንጋታና ከአለማስተዋል የተነሳ የዘለልሁት ታሪክ ብታገኙ፣ ስህተትም ብታዩ የሰው ልጅ ዕውቀቱ ሙሉ ሳይሆን ጎዶሎ መሆኑን አስባችሁ ጥፋቴን ተውልኝ፡፡ መጨመርንስ ስለከንቱ ውዳሴ ብየ አልጨመርሁም፤ የሰማሁትንና ያየሁትን ጻፍሁ እንጂ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ሆይ! ማረው፤ ይቅርም በለው ብላችሁ ጸልዩልኝ” (ገፅ 142)
ይህንን ፍሬ ሀሳብ ለመንደርደሪያ የተጠቀምሁት ኋላ ለማነሳቸው ጉዳዮች ዋቢ እንዲሆነኝ ስለፈለግሁ ነው፡፡ ሃሳቡ የዜና መዋዕሉ ጸሐፊ ነው፡፡ ጸሐፊው ማን እንደሆነ በውል ባይታወቅም አሳታሚው ባለሥልጣን በመግቢያው ላይ “ወልደ ህይወት” እና “አባ ባሕርይ በከፊል ሳይጽፉት አልቀረም” የሚል እምነት መኖሩን አስፍሯል፡፡ ግን የአንድ ንጉሥ ታሪክ (የዕለት በዕለት ውሎ) በጥንቃቄ የመዘገብ ኃላፊነት የተቀበለ ሰው እንዴት ስሙን አይጽፍም? መልሱ “ስምን ያለመጻፍ ልማድ ስለነበረ ነው” የሚል ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትህትና ነው “ምን ሠራሁና ስሜ ይጻፋል?” የሚል፡፡
ዜና መዋዕሉ የተጻፈው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፤ ባለ ዜና መዋዕሉ አፄ ሠርጸድንግል በ1542 ዓ.ም ተወልዶ ኢትዮጵያን ለ34 ዓመታት ከመራ በኋላ ገና የ47 ዓመት ጎልማሳ ሳለ በ1589 ዓ.ም በድንገት አርፏል፡፡ ሞት ባይቸኩልበት ኖሮ በጣም ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ሊሰራ ይችል እንደነበረ ከፈጸማቸው ተግባራቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡
የዓለም አገሮች አብዛኛው ታሪክ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ነው፤ የጦርነቱ ሰበብ ደግሞ ያው የሃብት ማካበት ወይም የ“ገብር! አልገብርም” ጣጣ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የአፄ ሠርጸድንግል የ34 ዓመታት ታሪክ ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ በሰሜንና በደቡብ፣ በምስራቅና ምዕራብ ኢትዮጵያ ከግዙፍ ሰራዊቱ ጋር እየተዟዟረ የሃገር አንድነት ያስከብር፤ በግራኝ አህመድ ጦርነት ምክንያት ተበታትነው የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ ይጠግን ነበር፡፡
15 ዓመት ሳይሞላው ለዘውድ የበቃው አፄ ሠርጸድንግል መንበረ ስልጣኑን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ የሾማቸው እየከዱት፣ ያመናቸው እየወጉት መከራውን ቢያይም በሄደበት ሁሉ በለስ የቀናው መሪ እንደነበር ዜና መዋዕሉ ያስረዳል፡፡ ድል የሚያደርገው ደግሞ በጦርነት ብቻ አይደለም፡፡ ከፍተኛ በደል የፈጸሙበት፣ ለአንገቱ ጎራዴ የሳሉለት ጠላቶቹ ሁሉ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ሲማጸኑት ያለምንም ማቅማማት ይቅር ይላቸው ነበር፡፡ ስለሆነም ንጉሠ ነገሥቱ በጦርነት ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲ ጥበብም የተካነ መሪ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ግዕዙንና አማርኛውን ጎን ለጎን (በንፅፅር) በማድረግ የተተረጎመው ይህ ዜና መዋዕል በቋንቋ፤ በባህል፣ በታሪክ፣ በመልክአ ምድር (ጂኦግራፊ)፣ በሃይማኖት ወዘተ መስክ ጥናት ለሚያካሂዱ ባለሙያዎች የላቀ ጥቅም እንደሚሰጥ አያጠራጥርም፡፡ ለምሳሌ በቋንቋው መጥፋት የሚታወቀው የጋፋት ህዝብ የት አካባቢ ይኖር እንደነበረ፣ የሚወደው ምግቡ ምን እንደነበር፣ የተለያዩ አካባቢዎች ምን እየተባሉ ይጠሩ እንደነበር፣ የኢትዮጵያ ግዛት ከየት እስከየት እንደነበር ሁሉ ወርቃማ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን የያዘ ክቡር ሰነድ ነው፡፡ የየአካባቢው ገዥዎች የማዕረግ ስሞችና የሰራዊቱ ክፍሎች መለያዎችም ያስደንቃሉ፡፡
የመዋዕለ ዜናው ይዘት
መዋዕለ ዜናው የንጉሠ ነገሥቱ አባት አፄ ሚናስ ከሞተበት ከየካቲት 5 ቀን 1555 ዓ.ም እስከ መለክ ሰገድ አፄ ሠርጸድንግል ሞት (መጋቢት 1589 ዓ.ም) ድረስ የነበረውን ድርጊት ይዘግባል፡፡ እንደ ጸሐፊው አባባል፣ ብዙውን ጊዜ ከንጉሡ ጋር እየዘመተ በዓይኑ በብረቱ ያየውን ሲጽፍ ቀሪውን (ያልተሰማራበትን) ግን “ሰማሁ” እያለ ዘግቦታል፤ ዜና መዋዕሉን ሲጽፍ በስህተት የተዘለለ ጉዳይ ከሌለ በቀር ሆን ብሎ፤ ወይም ለከንቱ ውዳሴ ሲል እውነትን አለማጣመሙንም ጸሐፊው በእግዚአብሔር ስም ምሎአል፤ ሳያውቅ ለሚሰራው የታሪክ ዘገባ ስህተትም አዋቂዎች እንዲጸልዩለት ተማፅኗል (ገፅ 142)፡፡
ዜና መዋዕሉ ለትውልዳችን ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ የሰራቸው አብተ ክርስቲያናት፣ የዘመተባቸው ጦር ሜዳዎች፣ የሀገራችን አስተዳደራዊ ቅርፅ፣ የአካባቢው ስያሜዎች፣ የሹማምንት የማዕረግ ስሞች፣ የንጉሱ ባህርይ (የአመራር ዘዴ)፣ የግዕዝና የአማርኛ ቋንቋ መዛነቅ ወዘተ በዜና መዋዕሉ ውስጥ የሚገኙ እጅግ ጠቃሚ ፍሬ ነገሮች ናቸው፡፡
በከፋ አካባቢ የሚገኙት “ጊዱ ጊዮርጊስ፣ ሸፓ ገብርኤል፣ በሀ ጊዮርጊስ፣ ኩቶ ሚካኤል፣ ደሪ ሚካኤል (ሁሉም ዳቻ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ናቸው)፣ ጫራ ሚካኤል (መንጅ ወረዳ) በአፄ ሠርጸድንግል ትዕዛዝና ድጋፍ የተሠሩ ናቸው፡፡ የእናርያ ሹም የነበረው በዳንች እና መላው ቤተሰቡ በፈቃዱ ክርስትና የተነሳው በዚሁ ንጉሥ ጥበብ ነው፡፡ ምክንያቱም አፄ ሠርጸድንግል ክርስትና ለተነሱት ግብር በመቀነስ፣ ክርስትና ላልተነሱት ደግሞ ግብሩን ጫን በማድረግ የክርስትናን ሃይማኖት ያስፋፋ ነበር (ገፅ 170-171)፡፡ ሆኖም ንጉሡ ክርስትና እንዲነሱ አካላዊ ቅጣት ከመፈጸም ብርቱ ጥንቃቄ ከማድረጉም በላይ ክርስትና የተነሱትን ልዩ ልዩ ሹመት ሽልማት በመስጠት ቤተኛ ያደርጋቸው ነበር፡፡
ለሞት የሚያደርስ በደል የፈጸሙበትን ሁሉ ንጉሡ ይቅር የማለት ልምድም ነበረው፤ ለምሳሌ የፈላሻዎች ኃይለኛ መሪና ጦረኛ የነበረው “ረዳኢ” የተባለው ሰው ደጋግሞ በደል ፈጽሞበት ከሠራዊቱም በርካታውን ጨርሶበት ይቅርታ አድርጎለታል፤ የኤርትራ ገዥ የነበረውን ባህረ ነጋሽ ይስሃቅ ደጋግሞ ቢከዳውም፣ ከቱርኮች ር ግንባር እየፈጠረ በከሃዲነት ቢበድለውም ምህረት አልነፈገውም፡፡
በትዕቢት ገፍተው ለመጡበትና ፊት ለፊት የገጠሙትንም ከፍተኛ ቅጣት ይጥልባቸው ነበር፤ አንገታቸው በሰይፍ እንዲቀላ (እንዲቆረጥ)፣ ቤታቸው እንዲቃጠል፣ አዝመራቸው ሁሉ እንዲወድም ያደርግ ነበር፡፡ ይህ አይነቱ ቅጣት በተለያዩ ጊዜያት ከሰሜን ጎንደር ፈላሻዎች (ይሁዲዎች) እና ከመተከል ቤንሻንጉሎች ጋር ወዘተ በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ ስራ ላይ ውሏል፡፡
አፄ ሠርጸድንግል ለሀገሩ ዳር ድንበር መከበር ፍጹም ቀናዒ ንጉሥ ነበር፤ ለምሳሌ የሰሜኑን የሀገራችንን ድንበር በጉልበት ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉትን ቱርኮችን በ1571 ዓ.ም እና በ1583 ዓ.ም ምፅዋና ደባሩአ ድረስ ዘምቶ ድባቅ መትቶ መልሶአል፤ ከቱርኮች ጋር እየተመሳጠረ የሃገርን ሰላም ሲያናጋ የነበረውን ባህረ ነጋሽ ይስሃቅን እና በምስራቅ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ደባ ይፈጽም የነበረውን ሱልጣን ይማም መሃመድን ወግቶ ኢትዮጵያን በምስራቅና በሰሜን ከተከሰተው ታላቅ አደጋ ታድጓታል፡፡
በጉባ፣ በአይባ፣ በሙገር፣ በግንደበረትና በጉባዔ (እንፍራንዝ አካባቢ የሚገኝ ቦታ) ከተሞችን መሥርቶ የነበረ ሲሆን በተለይ በዋና ከተማነት ይጠቀምበት የነበረው ጉባዔ አካባቢ የገነባው ቤተመንግስቱ ከ400 ዓመት በላይ ዕድሜ ቢያስቆጥርም ዛሬ ድረስ በኩራት ቆሞ የታሪክ እማኝነቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ቦሻ፣ እናርያ፣ ፈጠጋር፣ ወለቃ፣ ኮንች፣ እንደገብጠን፣ ወዘተ የመሳሰሉ ቦታዎች ከፍተኛ ታሪክ የተፈፀመባቸውና ተደጋግመው በዜና መዋዕሉ የሚጠቀሱ ስፍራዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶችም በግራኝ ጦርነት ምክንያት ተበታትነው የራሳቸው የውስጥ አስተዳደር የነበራቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ዜና መዋዕሉ ያስረዳል፡፡ የዝቤ ወንዝ “ጊቤ”፣ አባይ “አባያ”፣ ጐጃም “ጐዣም”፣  የሐ “ጸፍጸፍ” ወዘተ የሚል ቀዳሚ ስም እንደነበራቸው ይኸው ሰነድ ያስረዳል፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተረጐሙት “የአባ ባሕርይ ድርሰቶች” ላይ ግን ጐጃም ጐዚም ይባል እንደነበረ ይተርካል፡፡
በቋንቋ ረገድ “አንቱታ” የተጀመረው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይመስላል፤ ምክንያቱም ግዕዙም ባልተለመደ መልኩ፤ ወጥ ባይሆንም ንጉሡን “አንቱ” እና “አንተ” እያለ ጽፎ እናገኘዋለን፡፡ በግዕዙ ፊደል ውስጥ ምንም የድምጽ ውክልና የሌላቸው “ዠ፣ ጀ፣ ቸ፣ ጨ…” የመሳሰሉ ፊደሎች በብዛት ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ሆኖም አንዳንዴ “ሽሬ” የሚለውን “ሲሬ” እያለ የግዕዙን አጠቃቀም ለመጠበቅ ሞክሯል፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ቢጻፍ ኖሮ “ቦሻ”ን “ቦሳ”፣ “ኮንች”ን “ኮንት”፣ ጐዣምን “ጐዚም” ወዘተ ብሎ መጻፍ ነበረበት፡፡ ይህ የሚያመለክተው ከ16ኛ መ.ክ ጀምሮ የግዕዝ ፊደላት ለኩሽቲክ እና ኦሞቲክ ቃላት ጭምር ምቹ ሁኔታን መፍጠር መጀመራቸው ነው፡፡ (የእነ አፄ አምደጽዮንን፣ አፄ ዘርዓ ያዕቆብንና የሌሎችንም ዜና መዋዕሎች ከሠርጸድንግል ጋር ማመሳከር ሊጠቅም ይችላል)፡፡
በወቅቱ ይሰጡ የነበሩ የማዕረግ ስሞችም አስደናቂ ናቸው፤ ለምሳሌ “ጐጃም ነጋሽ፣ ባህር ነጋሽ፣ ወለቃ ነጋሽ” የሚባሉ የማዕረግ ስሞች ለጐጃም፣ ለኤርትራና ለወለቃ ገዥዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ ለዳሞት፣ ለሸዋ፣ ለአምሐራ ገዥዎች ደግሞ የ “ጸሐፊ ላህም” ነት ማዕረግ ነበራቸው፤ ባሌን እና ገንዝን ለሚገዙትም የ “ገረድ” ነት ማዕረግ ይሰጥ ነበር፡፡
 የመንዝና ኮንች ገዥዎች “ቃፅ” ወይም “መንዝህ ቃፅ” “ኮንች ቅፅ” ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ ሹም ሽሬ፣ ሹም አጋሜ፣ ትግሬ መኮንን ወዘተ በሚባሉ ማዕረጐች አካባቢያቸውን ያስተዳድሩ የነበሩ መኳንንትም ብዙ ናቸው፡፡ ዛሬ ቋንቋቸው የጠፋው የጋፉት ሰዎች በጐጃም፣ በጐንደር፣ በሸዋ፣ በጉራጌ አካባቢና በሌሎችም ቦታዎች ሠፊ ግዛት የነበራቸው ኃይለኛ ጦረኞችና እንሰት የሚመገቡ መሆናቸውንም ዜና መዋዕሉ ያስረዳል፡፡ ከሁሉም በላይ የዜና መዋዕሉ ጸሐፊ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ያየውን ወይም የሰማውን እንዳለ ያስቀምጣል እንጂ ያልሆነ፣ ያልተደረገ ነገር ለመጻፍ አለመዳዳቱን በተደጋጋሚ ማየት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ “ጐሽን” የተባለ የፈላሻዎች መሪ በንጉሡና በሠራዊቱ ተከቦ ለአንድ ወር ተኩል ውጊያ ተካሂዶ ድል መሆኑን ሲያውቀው “ለንጉሡ ከምገዛና የክርስቲያን እጅ ከሚነካኝ ሞት ይሻለኛል” ብሎ ራሱን በገደል ወርውሮ መሞቱን ጽፏል (ገፅ 152)፡፡ የጐሽን ሚስቶችና እህቶቹም በተመሳሳይ ሁኔታ መሞታቸውን በዜና መዋዕሉ ተመልክቷል (ገፅ 153)“ጨዋ፣ ቁርባን፣ አቄትዠር፣ ወደላ፣ ጊዮርጊስ ኃይሌ፣ ግርማ፣ ደረባ ጨዋ፣ መለሳይ (ኤርማጅ)፣ ወዘተ እየተባሉ ይጠሩ የነበሩ እጅግ ብዙ የሠራዊት አይነቶች እንደ ነበሩ የሚተርከው የአፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል፣ ጐጃም ውስጥ በተካሄደ ጦርነት ለአንድ ቀንም ቢሆን የንጉሡን ሠራዊት ያሸነፉ ኦሮሞዎች፣ ብዙ ጊዜ ጦርነት እየገጠሙ ይፈታተኑት የነበሩ አገዎችና በተለይ የፈላሻዎች ጀግንነት በተደጋጋሚ በአድናቆት የተገለጠበት ታሪካዊ ሰነድ ነው፡፡ በዚህም ጸሐፊው ሚዛናዊነቱን አሳይቷል፤ ሊወደስ ይገባል፡፡
ይህንን ታላቅ ሰነድ አፈላልጐ ወደ አማርኛ ያስተረጐመው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ተርጓሚው አቶ ዓለሙ ኃይሌ ድብቁን ታሪካችንን እንድናውቅ ላደረጉት ጥረት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ተመሳሳይ ሰነዶችን በማስነበብ ረገድ ከዚህ የላቀ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመጠቆም ጽሑፌን በዚሁ ልቋጭ፡፡  

Read 2610 times