Saturday, 03 May 2014 13:05

የእብዱ ሰው ማስታወሻ

Written by  ደራሲ- ሉ ሰን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(9 votes)

        (የእብዱ ሰው ማስታወሻ ወይም The Dairy of Mad Man በሚል ርዕስ ሶስት ደራሲያን፡- ፈረንሳዊው ጌ ደ ሞፓሳ፣ ቻናዊው ሉ ሰን እና ሩሲያዊው ኒኮላይ ጎጎል ምርጥ ምርጥ አጫጭር ልብ ወለዶች ጽፈዋል፡፡ የሶስቱም ደራሲያን ስራዎች ድንቆች ናቸው፡፡ ለምን እብዶች ለዘመናት፣ ለዚያውም በታላላቅ ደራሲዎች ተመራጭ ገፀ-ባህሪያት ሆኑ? እብዶች እንዴት ነው የሚያስቡት? ከፅሁፎቹ አስደናቂ መልሶች ታገኛላችሁ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ በተከታታይ የሦስቱንም ደራሲያን ስራዎች እናቀርባለን፡፡ ለዛሬ የቻይናዊውን ሉ ሰን ድርሰት እነሆ ብለናል፡-)
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እያለን ሁለት ወንድማማች ጓደኞች ነበሩኝ፤ አስፈላጊ ስላይደለ ስማቸውን አልፅፈውም፡፡ ሁለቱም አሪፍ ጓደኞቼ ነበሩ፡፡ ቀስ በቀስ የኑሮ መንገድ አለያየን፤ እንኳን ላገኛቸው ወሬያቸው እንኳ ጠፋብኝ፡፡ የሆነ ጊዜ፣ በሆነ አጋጣሚ ከወንድማማቾቹ አንዳቸው በጣም እንደታመመ ወሬ ደረሰኝ፡፡ እንደ አጋጣሚ ደግሞ ከምሰራበት ከተማ ወደ ትውልድ መንደሬ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ የምሄድት ጊዜ ነበረ፡፡ ጥሩ አጋጣሚ ሆነልኝ፡፡ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ወደ ትውልድ መንደሬ ስሄድ፣ እግረ መንገዴን ጓደኞቼን ለማየት ወደ መንደራቸው ጎራ አልኩኝ፡፡ ታላቅየውን ነው ያገኘሁት፤ ታሞ የነበረው ታናሽ ወንድሙ እንደሆነ ነገረኝ፡፡
“አሁን እንዴት ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡
“አሁንማ ተሽሎት የመንግስት ሰራ ተቀጥሮ እየሰራ ነው፤ የሚሰራበት ከተማ ከዚህ ትንሽ ይርቃል እንጂ፡፡”
“ይህን መልካም ዜና በመስማቴ ደስ ብሎኛል፡፡” አልኩት፡፡
“እኔም ይኸን ያህል ተጨንቀህ፣ ይህን ያህል ርቀት ተጉዘህ ልትጠይቀን ስለመጣህ ደስ ብሎኛል፡፡” አለኝ፡
“ምን ነበር አሞት የነበረው ግን?” አልኩኝ፡፡ ወንድምየው ሳቀ፡፡ ካለበት ተነስቶ ሁለት የማስታወሻ ደብተሮች አምጥቶ አሳየኝ፡-
“እነዚህ ማስታወሻች ታምሞ እያለ የፃፋቸው ናቸው፡፡ ማስታወሻዎቹን አንብበህ ህመሙ ምን እንደነበር ልትገምት ትችላለህ፡፡ የልጅነት ጓደኛችን ስለነበርክ ብታነባቸው ጣጣ የለውም፡፡” እያለ የማስታወሻ ደብተሮቹን አቀበለኝ፡፡
“ልውሰዳቸው?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡
“ውሰዳቸው!” አለኝ፡፡
ማስታወሻዎቹን አነበብኳቸው፤ ደጋግሜ፣ በጥሞና አነበብኳቸው፡፡ ከፃፋቸው ማስታወሻዎች እንደተረዳሁት፤ ልጅየው የመገደል-ገደብ-የለሽ-ስጋት (Persecution complex) ነበር ህመሙ፡፡ ማስታወሻው ዝብርቅርቅ ያለ እና ብዙም የሚያያዝ አልነበረም፡፡ አንዳንድ የፃፋቸው ነገሮች በጣም ያስፈራሉ፡፡ ማስታወሻዎቹ የተፃፉበት ቀናት አልተጠቀሱም፤ በተፃፉበት የብዕር አይነት እና በእጅ ፅሁፏቹ አኳኋን ግን በተለያዩ ቀንናት እንደተፃፉ ማወቅ ይቻላል፡፡ አሁን ከማቀርብላችሁ ማስታወሻ አንዲትም የጨመርኩት ወይም የቀየርኩት ነገር የለም፡፡ ፅሁፉ ላይ የተጠቀሱት ሰዎችን ስም (ሰዎቹን ከመንደራቸው ውጪ ማንም ሰው ባያውቃቸውም ቅሉ) ምንም ስለማይጠቅም ቀይሬዋለሁ፡፡ የማስታወሻው ርዕስ፡- “የእብዱ ሰው ማስታወሻ” የሚለው እንኳ ታማሚው ከዳነ በኋላም ለማስታወሻው የመረጠው ነው፡፡ ማስታወሻዎቹ ለህክምና ተማሪዎች እና ለህክምና ባለሙያዎች ጠቃሚ ናቸው ብዬ ስላሰብኩኝ ነው ያሳተምኳቸው፡፡
አንድ፡-
ዛሬ ጨረቃዋ በጣም ብሩህ ናት፡፡
ጨረቃን ለሰላሳ አመታት አይቻት አላውቅም ነበረ፡፡ ዛሬ እንዲህ ሆና ሳያት መንፈሴ ለጉድ ተነቃቃ፡፡ ላለፉት አስገራሚ ሰላሳ አመታት ጨለማ ውስጥ ነው የኖርኩት፡፡ አሁን በጣም መጠንቀቅ አለብኝ፡፡ ችግር አለ፡፡ ችግር ከሌለ የአቶ ቻኦ ውሻ ለምን ሁለቴ ገላመጠኝ?
ፍርሀቴ ምክንያታዊ ነው፡፡
ሁለት፡-
ዛሬ ጨረቃ የለችም፡፡ ይህ የመጥፎ ነገር ምልክት ነው፡፡ ዛሬ ጠዋት ከቤት ስወጣ አቶ ቻኦን መንገድ ላይ አየሁት፡፡ አስተያየቱ እንግዳ ነው፤ ፈርቶአል፤ ሊገለኝ የሚፈልግም ይመስላል፡፡ ሌሎች ሰባት፤ ስምንት የሚሆኑ ሰዎችም በሹክሹክታ ያወራሉ፤ ስለ እኔ ነው የሚንሾካሾኩት፡፡ አስተያየቴ ፍርሃት ለቀቀባቸው፡፡ በመንገዴ ላይ ያገኘኋቸው ሰዎች አንድ አይነት ነበሩ፡፡ ከመካከላቸው በጣም ጨካኙ ጥርሱን ሲያገጥብኝ መላ ሰውነቴ ተንዘፈዘፈ፡፡ ሰዎቹ ሁሉን ነገር አጠናቀው እንደጨረሱ ገባኝ፡፡ አልፈራሁዋቸውም፡፡ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ መንገድ ላይ ያገኘኋቸው ህፃናት ሳይቀሩ ስለ እኔ እያወሩ ነበር፡፡ አስተያየታቸው እንደ አቶ ቻኦ ያለ ነው፡፡ ፊታቸውም እንደ አቶ ቻኦ፣ እንደ እሬሳ የገረጣ ነው፡፡ አሁን እነዚህ ህፃናት ምን አድርጌያቸው ነው እንዲህ የሚሆኑት?!
“ምን እንደአደረኳችሁ ለምን አትነግሩኝም?!” ብዬ ጮህኩባቸው፡፡ ደንግጠው ሮጡ፡፡
ይህ አቶ ቻኦ የሚሉትን ሰውዬ፣ እኒህ በየመንገዱ የሚመላለሱትን ሰዎች ሁሉ ምን እንዳደረኳቸው፣ ምን እንደበደልኳቸው፣ ምን እንዳስቀየምኋቸው አላውቅም፡፡ ስለጥፋቴ ባስብ፣ ባስብ ምንም ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ላስታውስ የቻልኩት ትልቁ ጥፋቴ የአቶ ኩቺዩን የአራጣ ብድር ደብተር በስህተት መርገጤ ነው፤ ይህ የሆነው ከሃያ አመታት በፊት ነበር፡፡ በጊዜው ኩቺዩ አራጣ ያበደራቸውን ሰዎች መመዝገቢያ ደብተሩን ስለረገጥኩበት ከፍቶት ነበር፡፡ አቶ ቻኦ እና አቶ ኩቺዩ ግን አይተዋወቁም፡፡ አቶ ቻኦ ለማያውቀው ሰው አግዞ ሊበቀለኝ ነው ልበል፡፡ ህፃናቱ ግን እንዲህ የሚሆኑት ምን አድርጌያቸው ነው? እኔ የአቶ ኪቺዩን የአራጣ መመዝገቢያ ደብተር ስረግጥ እኮ እነዚህ ልጆች አልተወለዱም፡፡ ምን ይሁን ብለው ነው ታዲያ እንዲህ በፍርሃት የሚያዩኝ? ለምንድነው ሊገሉኝ የሚፈልጉት? ይህ የምር የሚያስፈራ ነገር ነው፡፡ ይህ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ይህ የሚረብሽ ነገር ነው፡፡ ገብኛል፡፡ ይህን ሁሉ ነገር ለልጆቹ ያስተማሩት ወላጆቻቸው ናቸው፡፡
ሶስት፡-
እንቅልፍ የለኝም፡፡ ነገሮችን ለመረዳት በአፅንኦት ማሰብ ይኖርብኛል፡፡ ትላንት መንገድ ላይ ካገኘሁዋቸው ሰዎች መሀል በአቃቤ ህግ የሀሰት ክስ የቀረበባቸው፣ በአዋራጅ ሁኔታ በተደጋጋሚ በጥፊ የተመቱ፣ ሚስቶቻቸው በጉልበተኞች ከእቅፋቸው የተነጠቁባቸው፣ ደሀ ወላጆቻቸው በአበዳሪዎች ወከባ እራሳቸውን ያጠፉ ሁሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ትናንት እኔን ሲያዩኝ ግን ይሔ ሁሉ ውርደት ሲደርስባቸው ያልተሰማቸው አይነት መራራ ፍራቻ፣ መራራ ጥላቻ ነበር የተሰማቸው፡፡
እጅጉን የገረመችኝ ደግሞ ያቺ መንገድ ላይ ያገኘኋት አሮጊት ነበረች፡፡ ልጇን በጥፊ እያላጋችው፣ እንዲህ ስትል ነበር፡-
“አሁን ተመታሁ ብለህ ነው የምታለቅሰው አንተ የሰይጣን ቁራጭ?! እንደ ጥፋትህማ ቢሆን በጥርሴ ስጋህን ብቦጫጭቀው እንዴት ደስ ባለኝ!” ይህን ስትል እኔን እያየች ነበር፡፡ እራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ በፍርሀት ተንቀጠቀጥኩ፡፡ አሁን ብፈራ ያስቃል? እኒያ ረዛዥም ጥርሶች እና አረንጓዴ ፊት ያላቸው ሰዎች ግን የሽሙጥ ሳቅ ሲስቁብኝ ነበር፡፡ ሽማግሌው ቼን እየከነፈ መጣ እና እየጎተተ ወደ ቤቴ ወሰደኝ፡፡
ቤተሰቦቼ የማያውቁኝ፣ የማያውቁኝ አይነት ነገር ሆኑ፤ አስተያየታቸውም እንደሌሎቹ ሁሉ አስፈሪ ነበረ፡፡ ወደ ጥናት ክፍሌ ስገባ ወጥመዳቸው ውስጥ ዳክዬ ወይ ዶሮ የገባችላቸው ይመስል በመስገብገብ በሩን ከውጭ ቆለፉት፡፡ አሁን ይሔ ግራ አያጋባምን? በጣም ግራ ተጋባሁ፡፡
ከቀናት በፊት ወዲያ ማዶ መንደር ያለው እርሻችንን የሚደርስልን ጭሰኛ እቤታችን መጥቶ ነበር፡፡ የዚህ አመት አዝመራ ምንም እንዳላፈራ ነገረኝ፡፡ ታዲያ የመንደሩ ገበሬዎች ለሰብሎቹ መምከን የጠረጠሩትን አንድ ባለ ክፉ ምልኪ ሰውዬ ወግረው፣ ቀጥቅጠው ገደሉት፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፤ ልቡንና ኩላሊቱን አውጥተው ጠባብሰው በሏቸው ብሎ ነገረን፡፡
ጨንቆኝ ወሬውን ሳቋርጣቸው የገዛ ወንድሜም ሆነ ጭሰኛው አፈጠጡብኝ፡፡ ዛሬ ነው እነሱም እንደሌሎቹ ሰዎች መሆናቸው የገባኝ፤ አስተያየታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለ ጉዳዩ ማሰብ ብቻ መላ ሰውነቴን ይረብሸዋል፡፡ ሰዎች ሰዎችን እየበሉ ነው፤ እኔንም ሊበሉኝ ከጅለዋል፡፡ ቆይ ያቺ ሴትዮ ልጇ ላይ፡- “ስጋህን በጥርሴ ብቦጫጭቀው ደስ ይለኛል” ብላ የጮኸችው ለምንድን ነው? እኒያ ባለረዣዥም ጥርስ እና ባለ አረንጓዴ ፊት ሰዎች እንዲያ አይነት ሳቅ ለምን ይስቃሉ? በጣም ግልፅ ነው፤ ለኔ ስውር መልእክት እያስተላለፉልኝም ነው፡፡ ወሬያቸው ውስጥ መርዝ፣ ሳቃቸው ውስጥ ስለታም ሰይፍ አለ፡፡ ጥርሶቻቸው ነጫጭ እና የሚያብረቀርቁ ናቸው፡፡ ሰው በላዎች ናቸው፡፡ እኔ የማላውቀው ምስጢር አላቸው፡፡ ቆይ እንዴት ሰው፣ የሰው በላዎችን ምስጢራዊ ሀሳብ ሊያውቅ ይችላል? እየተካሄደ ያለውን ነገር ለመረዳት በጥንቃቄ ማሰብ ይኖርብኛል፡፡ የታሪክ መፅሐፍትን መረመርኩ፡፡ በጥንት ዘመን ሰዎች ሰዎችን እንደሚበሉ የተፃፉፊ ታሪኮች አሉ፡፡ ዘመኑ መቼ እንደነበር የታሪክ መፅሀፍትን መልሼ አገላበጥኩ፤ ላገኘው አልቻልኩም፡፡ የእያንዳንዱ መፅሀፍ ገፆች ላይ “ልዕልናና ስነ ምግባር” የሚሉ ቃላት ፅፌባቸዋለሁ፡፡ እንቅልፍ የለኝም ብያለሁ፤ ስለዚህ ለሊት እስኪጋመስ ድረስ ማንበቤን ቀጠልሁ፡፡ በመጨረሻም በአረፍተ ነገሮች መሀል ሁለት ቃላት ብቻ ይታዩኝ ጀመር፡- “ሰው በላ” የሚል የመፅሀፉ ገፆች በሙሉ በእነዚህ ቃላት ተሞልተው ነበር፡፡ እነዚህ የመፅሀፉን ገፆች የሞሉት ቃላት እና ከጭሰኛችን የሰማሁት ታሪክ ያስጎመዡኝ ጀመር፡፡
ሰው ነኝ፡፡ ሊበሉኝ ከጅለዋል፡፡
አራት፡-
ጠዋት ላይ በጥሞና፣ ለረዥም ሠዓት ቁጭ ብዬ ነበር፡፡ ሽማግሌው ቼን ቁርስ ይሁንህ ብሎ የተቀቀሉ አትክልቶች እና የተጠበሰ አሳ አመጣልኝ፡፡ የአሳው አይኖች ነጭ ናቸው፤ በዚያም ላይ አፍጧል፤ አፉ ልክ እኒህ ሰዎች እንደሚበሉት ሰዎች በጉጉት ተከፍቷል፡፡ በመጨረሻም የማላምጠው ስጋ የአሳ ይሁን የሰው መለየት አቃተኝ፡፡ አስታወኩ፡፡
ያለሁበት በር ተከፈተና ወንድሜ ከሆነ ሰውዬ ጋር ገባ፡፡ ሰውየው የመግደል ረሃቡ አይኑ ውስጥ ይንቀለቀላል፡፡ በአትኩሮት ሳየው ማንነቱን እንደማውቅበት አውቆ አንገቱን ደፋ፡፡ እንዲም ሆኖ ግን እየሰረቀ በመነፅሩ ጎን ያየኝ ነበረ፡፡
“ዛሬ የተሻለህ ትመስላለህ” አለኝ ወንድሜ፡፡
“ዶክተር ሆ፤ በኔ ጥያቄ፣ ሊያይህ ነው የመጣው” አለ ወደ ሽማግሌው እየጠቆመ፡፡
“መልካም” አልኩኝ፡፡
ሽማግሌው ምን እንደሆነ ወዲያው ነው ነቄ ያልኩት፤ የህክምና ጋዋን የለበሰ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ሰው በላ ነው፡፡ የልቤን ምት የሚለካ መስሎ ምን ያህል እንደሰባሁ ይሰልል ጀመረ፡፡ ይኼን በማድረጉ እንደ ወሮታ ከስጋዬ የተወሰነ ሙዳ እንደሚደርሰው ቃል እንደተገባለት ያስታውቅበታል፡፡ አልፈራኋቸውም፡፡ እንደነሱ ሰው አልበላም፤ በድፍረት ግን እበልጣቸዋለሁ፡፡ሽማግሌው እንዲያያቸው ሁለት እጆቼን ለቡጢ አመቻቸዋቸሁ፤ ሽማግሌው ምንም አላለም፡፡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በዝምታ ከቆየ በኋላ፡-
“ምናብህን ተቆጣጠረው፤ ወደ ወሰደህ አትሂድ፡፡ ለጥቂት ቀናት በቂ እረፍት አድርግ፤ ያኔ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡”
ምናብህን ተቆጣጠረው?! ለጥቂት ቀናት በቂ እረፍት አድርግ?! ነው ያለው?! ለምን?! ምናቤን መቆጣጠር ስችልና በቂ እረፍት ሳገኝ እወፍራለሁ፤ እሰባላቸዋለሁ፡፡ ያኔ በቂ ስጋ ያገኛሉ፡፡ ዶክተሩ እንዳለው፤ “ያኔ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡”
አሁንስ ሳቅ ሊገድለኝ ነው፡፡ እነዚህ ጨዋ መሳይ፣ የሰው ስጋ መብላት ሱስ የሆነባቸው፣ ልምጥምጥ እና ፈሪ ሰዎች ላይ እንዴት በሳቅ አልሞት? አካባቢዬን በሳቅ አናጋዋለሁ፡፡ ዘይገርም ነገር ነው፡፡ ሳቄ ውስጥ ቆራጥነት እና ልዕልና አለ፡፡ አሁንም ሳቅሁኝ፤ ሽማግሌው እና ወንድሜ ሳቄን ሲሰሙ በድንጋጤ ገረጡ፡፡ ሳቄ ውስጥ የነበሩትን ቆራጥነት እና ልዕልና በደንብ ሰምተዋቸዋል፡፡ ቆራጥነቱን ማወቃቸው አሪፍ ነገር ነው፤ ችግሩ ግን ቆራጥነቴን ባወቁ መጠን እኔን ለመብላት ያላቸው ጉጉት ይጨምራል፡፡ የኔን ስጋ በመብላት የኔን ቆራጥነት የሚያገኙ ይመስላቸዋል፡፡
ሽማግሌው እየተጣደፈ ግቢውን ለቆ ወጣ፡፡ ወንድሜ ሸኘው፡፡ ከመለያየታቸው በፊት ሽማግሌው በሹክሹታ ለወንድሜ እንዲህ አለው፡- “በአፋጣኝ ይበላ!” ወንድሜ በመስማማት ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ እነሆ ጉዳዩ ውስጥ ወንድሜም አለበት፤ ይህን ሳውቅ ክው ነው ያልኩት፤ ብዙም ግን አልገረመኝም፤ በፊትም ጠርጥሬያለሁ፡፡
እነሆ ታላቅ ወንድሜ እኔን ለማስበላት እያሴረ ነው፡፡
ታላቅ ወንድሜ የሰው ስጋ በላተኛ ነው፡፡
እኔ ስጋ የሚበላ ሰው ታናሽ ወንድም ነኝ፡፡
ማንም ሊበላኝ ይችላል፤ ዋና ቁም ነገሩ ግን እኔ ስጋ የሚበላ ሰው ታናሽ ወንድም ነኝ፡፡
አምስት፡-
እሺ የትናትናው ሽማግሌ የምር ዶክተር ይሁን ልበል፤ ዶክተር መሆኑ ግን የሰው ስጋ ከመብላት ያግደዋል? እንዲያውም የህክምና መፅሀፍት በእንዲህ አይነት ታሪኮች የተሞሉ ናቸው፡፡ በነዚያ መፅሀፍት ነው የተማረው፡፡ ወንድሜስ ብትሉ? እንዴ በሆነ ሰውዬ በጣም ተናዶ፡- “እሱንማ መግደል እና ስጋውን መብላት፤ ቆዳውን ደግሞ ምንጣፍ ማድረግ ነበር…” ሲል ሰምቼያለሁ፡፡ እኔ ባለሁበት ነበር እንዲያ ያለው፡፡ ያኔ የአፉ ጠርዞች ላይ ቁርጥራጭ ጮማዎች ታዩኝ፤ ቁርጥራጭ የሰው ስጋዎች፡፡
ስድስት፡-
ድቅድቅ ያለ ጨለማ፤ ቀን ይሁን ምሽት መለየት አልቻልኩም፡፡ የአቶ ቻኦ ውሻ መጮህ ጀምሯል፡፡ የአንበሳ ጥንካሬ፣ የጥንቸል ስሱነት፣ የቀበሮ ስሌት ….
ሰባት፡-
ሰዎች ሁሉ እሚያስቧት እና የሚያደርጓትን እያንዳንዷን ነገር አውቃለሁ፡፡
አይገሉህም፤ እራስህ እንድትገድል ይገፋፉሀል፤ በመጨረሻም እራስህን ትሰቅላለህ፡፡ ያኔ የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማቸው፣ በገዳይነት ሳይወቀሱ ስጋህን በፌሽታ ይቀራመቱታል፡፡ በዚህን ጊዜ የፌሽታ ሳቃቸው አየሩን ይሞላዋል፡፡ ራስህን እንድትገድል ማድረጉ ባይሳካላቸውም ብዙ ችግር የለባቸውም፡፡ በፍርሃት እና በጭንቀት አሰቃይተው ይገሉሀል፡፡ በስቃይ ከስተህ መሞትህ ስጋህን ይቀንስባቸዋል፤ ይህ ያናድዳቸው እንደሁ እንጂ ሞትህን ይፈልጉታል፤ ይገሉሃል፡፡
ቆይ ግን ሰዎች ለምን የሰው ስጋ ይበላሉ? ሰዎች የሆነ ነገር ሲላመዱ መጥፎ መሆኑን እየረሱት ይመጣሉ? ወይስ ነገርየው መጥፎ መሆኑን እያወቁ ልባቸውን አደንድነው ነው የሚፈፅሙት?
ስምንት፡-
ሰው መብላት ግን ልክ ነው? ሰው መብላት አግባብ ነው ወይ?
ዘጠኝ፡-
ሰዎች ሰው መብላት ይፈልጋሉ፡፡ በሌሎች ሰዎች እንዳይበሉ ደግሞ በጣም ይፈራሉ፡፡ እርስ በእራሳቸው እረፍት በሚነሳ ጥርጣሬ ነው የሚተያዩት፡፡
ለምን ሰው መብላታቸውን አይተውትም ግን? ያኔ እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው ስራቸውን በእርጋታ ይሰራሉ፤ ዘና ብለው የእግር ጉዞ ማድረግ ይችላሉ፤ ፈታ ብለው ይመገባሉ፤ የእፎይታ እንቅልፍ ይተኛሉ፡፡ እንግዲህ ህይወት ይህን ያህል ቀላል ነው፡፡ በቃ ሰው መብላት መተው፡፡ አሁን ግን ወላጆች እና ልጆቻቸው፤ አባወራዎች እና እማወራዎች፣ ወንድሞች፣ ጓደኞች፣ መምህራኖች፣ ተማሪዎች፣ ይቅር የማይባባሉ ጠላቶች፣ ፍፁም የማይተዋወቁ ሰዎች እንኳ ሰው ለመብላት አብረው ያሴራሉ፡፡ ታዲያ እንዴት አድርገው የሰው ስጋ አምሮታቸውን መተው ይችላሉ?›
አስር፡-
ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፌ እንደነቃሁ ወንድሜን ማዋራት እንደአለብኝ ወሰንኩ፡፡ ጊቢው ውስጥ አገኘሁት፡፡ ሄጄ አጠገቡ ሞገስ በተላበሰ ትህትና ቆምኩ፡፡
“ወንድሜ ሆይ፤ ላወራህ የምፈልገው ነገር አለ፡፡” አልኩት፡፡
“መልካም፤ ምን ይሆን እስኪ?” አለ አናቱን እየነቀነቀ፡፡
“ብዙም የሚረባ ነገር አይደለም፤ ግን እንዴት እንደምነግርህ ግራ ገባኝ፡፡ ይኼውልህ ጥንታዊ ሰዎች፣ ያልሰለጠኑ ሰዎች ስለነበሩ እንዲያው ለአመል የሰው ስጋ ይበሉ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በኋላ ግን ሲሰለጥኑ እና ሙሉ ሰዎች ሲሆኑ እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡ ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ አሁንም የሰው ስጋ የሚበሉ ሰዎች እንዳሉ ግን ደርሼበታለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን እኛ የሰው ስጋ ከማንበላ ሰዎች ጋር ሲያነፃፅሩ ምን አይነት ሀፍረት እንደሚሰማቸው ሳስብ እኔም አፍርላቸዋለሁ፡፡
ችግሩ እነዚህ ሰዎች እኔንም ሊበሉኝ ይፈልጋሉ፡፡ አንተ ብቻህን ምንም ልታደርግልኝ አትችልም፡፡ ጥያቄዬ ለምን ተቀላቀልካቸው ነው? ሰው በላዎች ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፡፡ እኔን ከበሉኝ አንተንም መብላታቸው አይቀርም፡፡ ሰው በላዎች ሌላውን ሰው ብቻ አይደለም የሚበሉት፤ እርስ በእርሳቸውም ይበላላሉ፡፡ አንተ ሰው መብላትህን ማቆም ትችላለህ፣ ያኔ ነገሮች ቀስ በቀስ ይለወጣሉ፡፡ ሰው መብላት የተጀመረው የጥንት-ጥንት ጊዜ እንደነበር አውቃለሁ፤ አሁን ግን መቀየር እንችላለን፡፡ ወንድሜ ዛሬውኑ ሰው ላለመብላት መወሰን እና መተው ትችላለህ፡፡ አሁን ቆይ ባለፈው ጭሰኛችን ኪራይ ቀንሱልኝ ሲል ለምን እንቢ አልክ?”
ታላቅ ወንድሜ በመጀመሪያ የሹፈት ሳቅ ሳቀብኝ፡፡ ከዚያ ምስጥራቸውን እንዳወቅሁት ስላወቀ ነው መሰለኝ አይኖቹ በንዴት ጦፉ፡፡ ከግቢያችን ውጪ ብዙ ሰዎች ተሰብስበዋል፡፡ አቶ ቻኦ ከነውሻው ነው የመጣው፡፡ በአጥሩ ላይ እና በአጥሩ ቀዳዳዎች ወደ ውስጥ ለማየት ይጋፋሉ፡፡ እዚያ አስፈሪ እና የረገጣ ፊታቸው ላይ የሚታየውን ሳቅ ለመደበቅ እየጣሩ ነው፡፡ ሰው በላ ሁሉ፡፡ ሁሉም ሰው በላ ቢሆኑም ፤ አስተሳሰባቸው ግን፣ ሰው ስለመብላት ያላቸው አቋም ግን የተለያየ ነው፤ አንዳንዶቹ በቃ ዝም ብለው ልምድ ስለሆነባቸው ብቻ ነው ሰው የሚበሉት፡፡ ሌሎቹ የሰው ስጋ መብላት ፅዪፍ ስራ፣ ሀጢአት እንደሆነ ያውቃሉ፤ እንዲያም ሆኖ ግን ሰው መብላት ይፈልጋሉ፤ ይበላሉ፡፡ እነዚህኞቹ ምስጥራቸው እንዳይታወቅባቸው በጣም ይፈራሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁን ጉዳቸውን ሳወራ ከንፈራቸውን ግጥም አድርገው ያንን የሹፈት ሳቃቸውን ሳቁብኝ፡፡ ወንድሜ ያኔ አቅሉን ሳተ፡-
“እያንዳንዳችሁ ጥፉ ከዚህ፡፡ እብድ ለማየት ነው ይህን ሁሉ የምትጋፉት?!” ሲል ጮኸ፡፡
ዘዴያቸው ወዲያው ገባኝ፡፡ እብድ ነው ብለው ፈርጀውኛል፡፡ እኒህ ሰዎች በምንም ተአምር አቋማቸውን አይለውጡም፡፡ እብድ ነው ብለው የሰየሙኝ እኔን ለመብላት እንዲመቻቸው ነው፡፡ እብድ ሲበላ ማን ሊያዝን ይችላል? እፎይ ተገላገልን ነው የሚሉት፡፡ እንዲያውም ሌሎቹ ጤነኛ ሰዎች እኔን የበሉኝን ሰዎች እንደ ባለውለታዎቻቸው ይቆጥራቸዋል፡፡ ይህቺ ያረጀች ያፈጀች ዘዴያቸው አትጠፋኝም፡፡
ይኼኔ ለሰው በላዎቹ ሰዎች እንዲህ ስል መጮህ ጀመርኩ፡-
“ተለወጡ፣ ዛሬውኑ፣ የእውነት ተለወጡ፡፡ መጪው ጊዜ ለሰው በላዎች አይሆንም፡፡ የማትለወጡ ከሆነ እርስ በእርሳችሁ ተበላልታችሁ ታልቃላችሁ፡፡ ምን ብዙ ብትሆኑ፣ ምን ቢጤዎቻችሁን አብዝታችሁ ብትፈለፍሉ እውነተኛ ሰዎችን ልትቋቋሟቸው አትችሉም፡፡”
ሽማግሌው ቼን የተሰበሰቡትን ሰዎች ሁሉ አባረራቸው፡፡ ሽማግሌው ቼን ወደ ክፍሌ ይዞኝ ሄደ፡፡ ደክሞኝ ስለነበር ወዲያው እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ እንቅልፌ ግን በቅዠት የተሞላ ነበር፡፡
“ተለወጡ፣ ዛሬውኑ፣ የእውነት ተለወጡ፡፡ መጪው ጊዜ ለሰው በላዎች አይሆንም፡፡” ብዬ እየጮህኩ ከእንቅልፌ ነቃሁ፣ ላብ በላብ ሆኜ ነበረ፡፡
አስራ አንድ፡-
ፀሐይ የለችም፡፡ የመኝታ ክፍሌ በር ተከፍቶ አያውቅም፡፡ በቀን ሁለቴ ምግብ ያቀብሉኛል፡፡
ስለታላቅ ወንድሜ ሳስብ የእህቴ አሟሟት ትዝ አለኝ፡፡ እርግጠኛ ነኝ እህቴን እሱ ነው የገደላት ወይ ያስገደላት፡፡ በአምስት አመቷ ነው የሞተችው፡፡ አንጀት የምታንሰፈስፍ፣ ቆንጂዬ ነበረች፡፡ ያኔ እህቴ የሞተች ጊዜ እናታችን በልቅሶ ብዛት ልትሞት ነበረ፡፡ የወንድማችን ስራ ደግሞ እናታችን እንዳታለቅስ መለማመጥ ነበረ፡፡ ስራውን ያውቀዋላ፤ እሱ ነው የገደላት፡፡ ምን መግደል ብቻ … እሱ ነው ገድሏት ስጋዋን የበላው፡፡ የእናታችን ለቅሶ አሳፍሮት ነው እንዳታለቅስ የሚለምናት፡፡ መቼ እሱ ሀፍረት ያውቅና፡፡
እናታችን ትወቅ፣ አትወቅ ባላውቅም እህቴን የበላት ወንድሜ ነው፡፡ እንዲሁ ሳስበው ግን እናቴ እውነቱን የምታውቅ ይመስለኛል፡፡ ጨዋነት ይዟት ነው ያልተናገረችው፡፡
አስራ ሁለት፡-
አሁን ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ እየታከተኝ ነው፡፡
ለምን ሰዎች ከአራት ሺህ ዘመን በኋላ እንኳን ሰው መብላታቸውን አላቆሙም? ሰው ለምን እስከ ዛሬ ሰው ይበላል?
እኔ እራሱ የሰው ስጋ ሳልበላ አልቀረሁም፡፡ እህታችን ከሞተች በኋላ እቤታችን ውስጥ ምግብ የሚያበስለው ታላቅ ወንድሜ ነበር፡፡ ሩዝ እና ወጣችን ውስጥ ጣል፣ ጣል እያደረገ ያበላን የነበረው የእህቴ ስጋ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ታላቅ ወንድሜ፤ ሳላውቅ የታናሽ እህቴን ስጋ አብልቶኛል፡፡
በመጀመሪያ የእህቴን ስጋ ሳላውቅ አበሉኝ፤ አሁን ደግሞ መበላቱ የኔ ተራ ነው፡፡
የሰው ስጋ በልቻለሁ፤ አሁን እንዴት ብዬ ነው ከእውነተኛ ሰዎች ጋር የምቀላቀለው?
አስራ ሶስት፡-
የሰው ስጋ ያልበሉ ጥቂት ህፃናት ይኖሩ ይሆናል፤ እባካችሁ ህፃናቶቹን ታደጓቸው …

Read 4888 times