Saturday, 03 May 2014 13:01

“ትናንት መኖር የምፈልገውን ዓይነት ህይወት ነው ዛሬ የምኖረው”

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(6 votes)

ባለፈው የትንሳኤ በዓል የ “ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ” ፕሮግራም በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል በጎ ተግባር ያቀረበ ሲሆን ብዙዎችም አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሟቿ አርቲስት ማንአልሞሽ ዲቦ ቤተሰቦችን የመኖርያ ቤትና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ጥረትና የተገኘውን አስገራሚ ውጤት ያስቃኛል -ፕሮግራሙ፡፡ አንድ ሰው ብቻውን እንኳን  በቁርጠኝነት ከተነሳ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ትምህርት የሚሰጥና የሚያነቃቃ ሥራ ነው፡፡ “እውቅናን ተጠቅሞ ወገንን መደገፍ በአገራችን  አልተለመደም” ከሚለው አርቲስት ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

የአርቲስት ማንአልሞሽ ዲቦ ቤተሰቦች የነበረባቸውን የመኖርያ ቤት ችግር ለመፍታት ያደረግኸውን ጥረትና የተገኘውን ውጤት በኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ” ፕሮግራምህ ላይ አሳይተሃል፡፡   ከተመልካች ምን ዓይነት ምላሽ አገኘህ?
ሁሌም ጥሩ ነገር ስትሰሪ ይመጣል ብለሽ የምትገምቺው ምላሽ ይኖራል፡፡ እኔ ያገኘሁት ግን ፍፁም ያልጠበቅሁት ነው፡፡ በቃላት እንዲህ ነው ብሎ መግለፅ ያዳግታል ፤በጣም የሚገርም ምላሽ ነው ያገኘሁት፡፡
ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላም ቢሆን ያሰብከው በመሳካቱ ምን ስሜት ፈጠረብህ ?
እኔ ትናንት መኖር የምፈልገውን ዓይነት ህይወት ነው ዛሬ የምኖረው፡፡ በአብዛኛው እኛ አገር እውቅናን ተጠቅሞ ወገንን መደገፍ  አልተለመደም፡፡ ያ ሁልጊዜ ያናድደኝ ነበር፡፡ አርአያህ (ሮል ሞዴልህ) ማነው ስባል እንኳን አንጀሊና ጆሊንና ብራድ ፒትን ነው የምጠራው፡፡ እነሱ ለኛ ሩቅ ናቸው፤ሆኖም  ግን እውቅናቸውን ተጠቅመው የተቸገረ ይረዳሉ፡፡ የኔ እውቅናም እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እንጂ “አየኸው አየሽው” የሚል መጠቋቆሚያ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የእነዚህ ልጆች የቤት ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ የጀመርኩት ሥራ አድካሚ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ነገር እንዳየሽው ተሳክቷል፡፡ እኔ ያሰብኩት እንደውም  ከዚህም በላይ ነበር፤ ነገር ግን ነገሮች እንዳሰብኩት አልሄዱም፡፡ ስራው የፈጠረብኝን ስሜት በተመለከተ----እኔ  ስራውን ለቀረፃ ብዬ አይደለም የሰራሁት፡፡ አሁንም ሳስበው ራሱ ውስጤ ይረበሻል፤ እንባ እየተናነቀሽ ቴሌቪዥን ላይ መስራት በጣም ከባድ ነው፡፡ ቤተሰብ አንድ ላይ ተቀምጦ የሚያየው ፕሮግራም ነው፡፡ ኃላፊነቱ ከባድ ነው ግን  መሸከም መቻል አለብሽ፡፡ ማህበረሰቡንና ትውልዱን የሚቀርፁ፣ ክፍተቶችን የሚደፍኑ ስራዎች መስራት አለብኝ ብዬ ስለማምንም ነው የሰራሁት፡፡
ያሰብከው ከዚህም በላይ እንደነበር ጠቅሰሃል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ነበር ያሰብከው?
ለምሳሌ ልጆቹ ቋሚ የታክሲ ገንዘብ እንዲያገኙ ፈልጌ ነበር፡፡ አክስታቸው ትእግስት ቀን ቀን እየሰራች ትምህርቷን ማታ እንድትማርና አረብ አገር ያለችውን እህቷን እንድታግዝ ነበር ሃሳቤ፡፡ እስቲ አስቢው--- አረብ አገር ያለችው እህቷ ባለፈው ኢትዮጵያውያን ሲባረሩ መጥታ ቢሆን ኖሮ ምን ይሆኑ ነበር? ለትእግስት የተገኘላት ስራ ክፍያው አነስተኛ በመሆኑ ልፋት ይሆንባታል ብዬ ተውኩት፡፡ እሷን ስራ የማስያዙን ነገር ግን አሁንም አልተውኩትም፤እየሞከርኩ ነው፡፡
የማንአልሞሽን ልጆች ለማገዝ ያነሳሳህ ምንድነው? በምን ሁኔታ ላይ ነበር ያገኘሃቸው?
ለቤተሰቡ ቤት ለማግኘት ሰባት ወር ነው የፈጀብኝ፡፡ እንዳልኩሽ ስሰራው ለፕሮግራም ብዬ አልነበረም፡፡ የአርቲስት ማንአልሞሽ ልጆች የት ደርሰው ይሆን ብዬ ሳጠያይቅ--- ለቡ እንደሚኖሩ ሰማሁ፡፡ ሳገኛቸው በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነበሩ፡፡ ለቡ የገቡት ከተማ የቤት ኪራይ በጣም ተወዶባቸው ነው፡፡ እናታቸው በአንድ ወቅት በጣም ታዋቂ አርቲስት ስለነበረች ልጆቿ ብዙ ጥሩ ነገርና ምቾት ለምደዋል፡፡ እኔ ሳገኛቸው ባለፉት አራት አመታት ውስጥ ቤታቸው የሄድኩ ብቸኛ እንግዳ እንደሆንኩ ነገሩኝ፡፡ ቤተሰቡ ከባድ የስነልቦና ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ልጆቹ ተገልለዋል፡፡ እሷ ሳለች የለመዱትን ጥሩ ነገር ሁሉ አጥተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኑሮን ለመቋቋም የወሰኑት ውሳኔ በጣም ከባድ ነው፡፡ አንድ አክስታቸው ትምህርቷን አቋርጣ፣ ልጆቹን እያሳደገች ነው፡፡ ሌላ አክስታቸው አረብ አገር ሄዳ እየሰራች  መተዳደሪያ የሚሆናቸው ገንዘብ ትልካለች፡፡ አሁን ደውላልኝ ነበር፡፡ ያለችበትን ሁኔታ ነግራኛለች፡፡ “እዚህ ያለሁት ተመችቶኝ ሳይሆን ልጆቹ ፆም እንዳያድሩና እንዳይቸገሩ ብዬ ነው” ብላኛለች፡፡
የልጆቹን ስሜት ለመጠበቅ ስትል ብዙ መጨነቅህ በፕሮግራምህ ላይ በግልፅ  ይታይ ነበር---
አዎ--- የልጆቹን ስሜት ላለመንካት በጣም ተጠንቅቄያለሁ፡፡ እናታቸውን አጥተዋል፡፡ በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ዛሬ የሉም፣ ለአራት አመት ማንም አግኝቷቸው አያውቅም፡፡ ዙሪያቸውን ከከበባቸው ችግሮች ውስጥ እኔ ያተኮርኩት በመኖሪያ ቤት ፣ በትምህርት እና በጤና ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያ እነሱ ጋ ልሄድ ነው ስል፣ ጥያቄ ያነሱ  ሰዎችም አልጠፉም፡፡ እኔ ጥያቄው ላይ ሳይሆን መልሱን መስጠት ላይ ነበር ያተኮርኩት፡፡ “ቴሌቪዥን ላይ የምናውቀው ሰው እንዲህ ፍቅር ከሰጠን ሌሎቹም ተሳስተው መሆን አለባቸው--” የሚል ስሜት በውስጣቸው እንዲፈጠር ለማድረግ ነው የሞከርኩት፡፡ በደረሰባቸው ችግር የተፈጠረባቸው ስሜት መለወጥ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እናታቸውን ቢያጡም የሚያስብላቸውና የሚቆረቆርላቸው ወገን እንዳላቸው ሲረዱ ነው ስሜታቸውና አመለካከታቸው የሚለወጠው፡፡  
ለማንአልሞሽ ልጆች ያሰብከውን ለማሳካት ምን ፈተናዎችን ተጋፈጥክ ?
የሄድኩበት መንገድ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የብዙ ሰው ፊት አይቻለሁ፡፡ አንዳንዶች “የምትሰራው ስራ በጣም አሪፍ ነው ፤እንረዳዳለን” ብለው ቃል ከገቡልኝ በኋላ፣ ጉዳዩን ዳር ለማድረስ ስደውልላቸው ጭራሽ ስልኬን አያነሱም፡፡ ስለዚህ ባለችኝ ገንዘብ ስራውን መጀመር ነበረብኝ፡፡ በሌላ በኩል ታይታውን የማይፈልጉ፣ስማችን እንዳይነሳ የሚሉ ሰዎች ያልጠበቅሁትን ድጋፍ አድርገውልኛል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች  የተለያዩ ችግሮችና ውጣውረዶች ገጥመውኛል፡፡ ያሰብኩት ሲሳካ ግን  ሁሉንም እረሳኋቸው፡፡ ምን ሆነ መሰለሽ ---- በቅርቡ የሚወጣ አልበም አለኝ፡፡ ከሱ ጋር በተያያዘ ለአንድ ኩባንያ የስፖንሰርሺፕ ጥያቄ አቅርቤ ምላሽ እየተጠባበቅሁ ነበር፡፡ ልጆቹን ሰርፕራይዝ ለማድረግ ከደብረዘይት ወደ አዲስ አበባ እየመጣን ገላን ላይ ስልክ ተደወለልኝና፣ “የአልበምህን የስፖንሰርነት ጉዳይ ጨርሰናል” አሉኝ፡፡ ያ ለኔ ትልቅ ዜና ነበር፣ ምክንያቱም ገንዘቡ በሚሊዮኖች የሚገመት ነው፡፡ ብታምኚም ባታምኚም ምንም አልመሰለኝም፤ በልጆቹ ደስታ ውስጥ ተውጬ ነበር፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ልጆቹን ከጎረቤት ጋር አስተዋውቀህ ነው የተለየሃቸው፡፡ ይሄ ለኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ስራ ነው ----
ልጆቹን እዛ ላሉት እናቶች እና አባቶች ነው የሰጠኋቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለሁለቱም ትልቅ እድል ነው፡፡ በረዳናቸው ለሚሉት እንደ አባት እና እናት ተንከባክበው የማሳደግ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ልጆቹም ተንከባካቢ አግኝተዋል፡፡ ግቢው ጎረምሳ ይበዛበትና አይመቻቸው ይሆን --- ብዬ አስቤ ነበር፡፡ እኔ አሁን እንደ አባት ነው እያሰብኩ ያለሁት፡፡ ልጆቹን ደህና ቦታ ለማስያዝ ነው ሃሳቤ፡፡ ደውዬ ሳናግራቸውም እንደ አባት ነው የማናግራቸው፡፡ በትውውቁ ላይ አዋቂ ሰዎች ሲመጡ መንፈሴን ከፍ አደረገው፡፡ በነገርሽ ላይ የሆኑ ሰዎች ከዱባይ ደውለው እያለቀሱ “ከዚህ በፊት በውሳኔ ፊልም ነበር ያለቀስነው፤ አሁን ደግሞ ትክክለኛ ህይወት በቴሌቪዥን አይተን አለቀስን” አሉኝ፡፡ ከአሁን በኋላ ልጆቹ ከቤተሰብ ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ በኢትዮጵያ ባህል መሰረት ጉልበት  ስመው ነው ከአዲሱ ቤተሰባቸው ጋር የተዋወቁት፡፡
አንዳንዶች ዝነኝነት ሲመጣ ኣያያዙን  ባለማወቅ ግራ ሲጋቡና ለችግር ሲጋለጡ ይታያል፡፡ ታዋቂነት ላንተ እንዴት ይገለፃል?
ዝናና ክብር ሲመጣ መንገድ የሚስት ይኖራል ፤ ፈፅሞ ከመስመሩ ውልፊት የማይልና መንገዱን የማይስትም አለ፡፡ ቤቱ ለልጆቹ ሲፈቀድላቸው በጣም ተደስቼ ስለነበር ጓደኞቼን “እራት እንብላ” አልኳቸው፡፡ እራት እየበላን ቤቱ እንደተፈቀደ ስነግራቸው፣ የተወሰኑት “ለዚህ ነው የጠራኸን? እኛ ደግሞ ለአልበምህ ስፖንሰር ዘግተህ መስሎን ነበር--” አሉኝ፡፡  ለነገሩ በእነሱም አልፈርድም፡፡ እኛ አገር የተለመው እንዲህ ነው፡፡ አንድ ሰው በአብዛኛው ደስ ብሎት የሚፈነድቀው የራሱ ጉዳይ ሲሞላለት ብቻ ነው፡፡ የሌላው ችግር ብዙም አያሳስበንም፡፡ ሁሉንም ሰው በጅምላ ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ጥቂት ቢሆኑም ከራሳቸው አልፈው ለሌላው የሚያስቡና ለውጥ ለማምጣት የሚተጉ አሉ፡፡
አዲሱ አልበምህ መቼ ይወጣል?
 በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይወጣል፡፡ በጣም አሪፍ ስራ ይዤ መጥቻለሁ ጠብቁ፡፡ አሁን የ “ጆኒ ኢን ዘ ሃውስ” ፕሮግራም ሲዝን ሶስት ስለሚጀምርም በጣም ስራ በዝቷል፡፡
በሲዝን ሶስት ምን አዲስ ነገር እንጠብቅ?
ሲዝን አንድን ጨርሼ ሲዘን ሁለት ልጀምር ስል ከተመልካቾች በተቀበልኩት አስተያየት “ምንም ለውጥ አታድርግ” ያሉኝ ብዙ ነበሩ፡፡ በሚቀጥለው ሲዝን ለተመልካች የሚጠቅም፣ ማዝናናቱን ያልለቀቀ፣ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ፕሮግራም ይዤ እመጣለሁ፡፡ ተመልካቹ  ቀጥል ብሎ ፊሽካውን ነፍቶልኛል፡፡ “እንኳን አሁንና ሙሉ ትጥቅ እያለን በጦር በጎራዴ ታንክ እንማርካለን” አይደል የሚባለው፡፡ አሁን የህዝብ ይሁንታንና ፍቅርን አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህ በእርግጠኝነት ከእስካሁኑ የላቀ ጥሩ ነገር እሰራለሁ፡፡ በነገርሽ ላይ ከህፃናት ጀምሮ መንገድ ላይ ያየኝ ሁሉ ነው የሚመርቀኝ፡፡ አንዳንዴ ከራሳችን አልፈን  ለሌላው አስበን ስንሰራ ሽልማቱ ብዙ ነው፡፡ ከሁሉም ግን የህሊና እርካታው ይበልጣል፡፡ አየሽ  እርስ በርስ ካልተሳሰብንና ካልተደጋገፍን በቀር ሌላ ማንም አይደርስልንም፡፡ በእኔ እምነት “ጠላት” የሚባሉ ሰዎች እንኳን ከምር ጠላት አይደሉም፤ የሚፈልጉት መድሀኒት ነው፡፡
የባህሬን ስራህ እንዴት ነበር?
በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ስራዬን ከጨረስኩ በኋላ አንድ ኢትዮጵያዊት ምሳ ጋበዘችኝና እቤቷ ሄድኩ፡፡ ምሳውን ተጋብዘን ከጨረስን በኋላ፣እዛ ቤት የምትሰራ ኢትዮጵያዊት አለች፡፡ የማንአልሞሽ ልጆች ላይ በተሰራው ፕሮግራም ስሜቷ በጣም መነካቱን ነግራኝ፣ ልሄድ ስል አሰሪዋን “ከደሞዜ ላይ የሚቆረጥ የታክሲ ብር ስጭልኝ” አለቻት፡፡ ልቤ በጣም ተነካና፤ገንዘብ ተከፍሎኝ ልሰራ እንደመጣሁና የሚመልሰኝ መኪና እንዳለ ነግሬያት፣ “አገር ቤት ለቤተሰብ የምትልኪው ገንዘብ ካለሽ ልውሰድልሽ” ስላት “ለነሱ አሁን አልክም፣ ትንሽ አጠራቅሜ ነው” አለችኝ፡፡ ከሌላት ገንዘብ ላይ ልትሰጠኝ በማሰቧ ልቤን በጣም ነካችው፡፡
ከመጣህ በኋላ የማንአልሞሽን ልጆች ጠየቅሃቸው?
አዎ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለሆነው ልጅ ከባህሬን ተጨማሪ ላብቶፕ ስለተላከለት እሱን ላደርስ እሄዳለሁ፡፡ አሁን ቤታቸው በቴሌቪዥን ካየሽው በላይ ሆኗል፡፡ ማድቤቱን የሚሰሩ ሰዎች አግኝተናል፡፡ ዋሪቶችም ኪችን ካቢኔት እንሰራላቸዋለን ብለውናል፡፡ ልጆቹ አዲስ ህይወት ላይ ናቸው፡፡ ስለነሱ ሳስብ ውስጤ በጣም ይረበሻል፡፡ ከለቡ ወደዚህ ቤት ሲመጡ እቃቸው ብዙ ስለነበር የመኪና ዋጋ ተወደደ፣ ሁሉም ከስምንት መቶ ብር በታች አንጭንም ብለው ሙጭጭ አሉ፡፡ ሊያግዛቸው የሄደ ከእኔ ጋር የሚሰራ ልጅ ዋጋ እንዲቀንሱለት ብሎ፣ለሾፌሩ ጉዳዩን ነገራቸው፡፡
እንደዚያ ሲከራከሩ የነበሩት ሰውዬ ምንም ሳያቅማሙ “ነዳጁን ቅዳና በነፃ እወስዳለሁ” አሉት፡፡ በመንገዳቸው ላይ ትንሿ ልጅ “ለካ እስከዛሬ ሌላ አገር ነው የምንኖረው፣ እንደዚህ ርቀን ነበር እንዴ?” ስትል ሾፌሩ ሰምተው እንባቸውን መቆጣጠር አቃታቸው፡፡ እንዳልኩሽ --- ሲዝን ሶስትን ለመጀመርና አልበሜን ለማውጣት ሩጫ ላይ ነኝ፤ ያለችኝን ጊዜ አመቻችቼ  እጠይቃቸዋለሁ፡፡

Read 4141 times