Saturday, 03 May 2014 12:14

በዩኒቨርስቲዎች በተነሳው ተቃውሞ በርካቶች ሞቱ

Written by  አበባየሁ ገበያው እና አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(42 votes)

የከፋ ጉዳት የደረሰው በአምቦ፣መደወላቦ እና ሐረማያ ነው
ተቃውሞው እስከ ሃሙስ በመንግስት ሚዲያ አልተነገረም

አዲስ አበባንና በዙሪያዋ የኦሮሚያ ከተሞችን በማካተት የተዘጋጀውን የጋራ ማስተር ፕላን የሚያወግዙ የክልሉ ተማሪዎች፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያካሂዱት በሰነበቱት ተቃውሞ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፋ፡፡ በትንሹ ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎችም እንደቆሰሉና ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ በተቃውሞዎቹ ዙሪያ ቀጥተኛ ዘገባ ሲያስተላልፍ የነበረው የመንግስት ሚዲያ ሐሙስ እለት ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት የወጣውን መግለጫ ያቀረበ ሲሆን በአምቦና በመደወላቡ 3 ተማሪዎችን ጨምሮ 7 ሰዎች እንደሞቱ አትቷል፡፡ ሲኤንኤንና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን በመጥቀስ የተለያዩ ዘገባዎችን ያሰራጩ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ 30 ሰው መሞቱን እንደተናገሩ ጠቅሰዋል፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቭዥን የሚመለከቱ የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ አንድ ተማሪ እንደሞተና 70 ሰዎች እንደቆሰሉም መግለጫው አስታውሶ፤ ዩኒቨርስቲዎች እንደተረጋጉ መንግስት ቢገልፅም በስልክ ያነጋገርናቸው የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ግን ግጭቱና ውጥረቱ እንዳልበረደ ተናግረዋል፡፡
በአዳማ፣ በጅማ፣ ሃሮማያ፣ አምቦ፣ ነቀምት፣ መደወላቡ እና ድሬደዋ ዩኒቨርሲዎች በተነሳው ተቃውሞ እስካሁን ከተገለጸው በላይ የሞትና የአካል ጉዳት በተማሪዎች ላይ እንደደረሰ የየአካባቢው ምንጮች የገለፁ ሲሂን፣ በርካቶች እንደታሰሩም ጠቁመዋል፡፡ በሃሮማያ ፍንዳታ የሞቱት ተማሪዎች ሁለት መሆናቸውን የገለፁ ምንጮች፣ በብሄር ተወላጅነት የተቧደኑ ተማሪዎች ጎራ ለይተው በፈጠሩት ግጭት በርካታ ተማሪዎች እንደተደባደቡ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባንና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችንም ያስተባብራል ተብሎ የጋራ ማስተር ፕላን የተዘጋጀው ከከተማ አስተዳደርና ከአሮሚያ ክልል መስተዳደር ተውጣጥቶ በተቋቋመ ቡድን ሲሆን፤ ፕላኑን የተቃወሙ ተማሪዎች “የኦሮሚያ መሬትን የሚቆርስ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ነው፡፡ ሃገራችንን ትተን ወዴት እንሂድ!” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡
ማክሰኞ ማታ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የጀመረው ተቃውሞ፤ ረቡዕ እለት ከምሳ በኋላ ረገብ ቢልም ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ ውጥረቱ እንደነበር ለማወቅ ችለናል፡፡ የመማር ማስተማር ትምህርት እንደተቋረጠና ወደ ግቢ መግባት እንጂ መውጣት እንደተከለከለ የገለፁት ምንጮች፤  አንዳንድ ተማሪዎች በአጥር ሾልከው እየወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ረቡዕ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ በቴሌቪዥን እግር ኳስ ሲመለከቱ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የፈንጂ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የተቀሰቀሰው ሁከት ብሄር ወደ ተቧደነ ግጭት እንደተለወጠ የጠቆሙት ምንጮች፤ ግጭቱ ከፌደራል ፖሊስ ከቁጥጥር ውጪ እስከ አርብ ድረስ እንዳልበረደ ጠቁመዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው መውጣትና መግባት ተከልክሎ ቢቆይም፣ ወደ ቤተሰቦቻችን እንመለስ የሚሉ ተማሪዎች በመበራከታቸው ትናንት አርብ ከሰአት በኋላ ጀምሮ እንዲወጡ ተፈቅዷል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያነሱት ተቃውሞ ከሌሎች የጠነከረ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ ተቃውሞው ከዩኒቨርሲቲም ውጭ እንደተስፋፋ ገልፀዋል፡፡ 25ሺ ያህል ሰዎች ከተቃውሞ ወደ አደባባይ መውጣታቸው የተዘገበው አል አፍሪካ፤ ከባድ ግጭት መከሰቱን አትቷል፡፡ በተጨማሪ መረጃ ባይረጋገጥም፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ግን 30 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል ሲኤ ሲሴን ኤን የዘገበ ሲሆን፤ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የሟቾች ቁጥር 7 እንደሆነ ጠቅሶ በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በተነሳው ተቃውሞ ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ ባይቻልም መንግስት 3 ተማሪዎች መሞታቸውንና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳት ስለመድረሱ የተባለ ነገር የለም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ፤ ሐሙስ ጠዋት ተማሪዎች ወደ ግቢ መግባትም መውጣትም ተከልክለው ነበር፡፡ የፌደራል ፖሊስ አባላትም በቡድን በቡድን በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን ከሰዓት ለተቃውሞ የተሰበሰቡ ተማሪዎች የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡  
ከፖሊስ ጋር የተፈጠረ ግጭት ያልነበረ ሲሆን ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ተማሪዎች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር የሚወያዩበት መድረክ እንደሚዘጋጅ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች መናገራቸውን ምንጮች ገልጸው፤ በዚሁ ምክንያት ከፖሊስ ጋር ግጭት አለመፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡  
መንግስት በበኩሉ፤ ተቃውሞውና ግጭቱ ጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎች በሚያሰራጩት አሊባልታ ምክንያት የተፈጠረ ነው በማለት በሁከቱ ጉዳት መድረሱ እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡  
አንድነት ፓርቲ ትናንት “በአፅንኦት እናወግዛለን” ሲል ባወጣው መግለጫ፤ መሬት በግል አለመያዙ ብዙ ችግሮችን እያስከተለ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የተቃውሞ ድምፅ በሚያሰሙ ሰዎች ላይ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ እንደሚያወግዝም ፓርቲው አስታውቋል፡፡

Read 14788 times