Saturday, 26 April 2014 13:17

ፈረንጅ፣ የሐበሻ ዶሮ እና አንበሳ አውቶብስ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

             ዶሮ በተፃፈ ሕግ፣ ፈረንጅ በልማድ በከተማ አውቶብስ አይሳፈሩም፡፡ በዘንድሮው የሁዳዴ ፆም መጠናቀቂያ ስምንተኛው ሳምንት (በሰሞነ ህማማት ማለት ነው) ላይ ግን በከተማ አውቶብስ  ውስጥ  ዶሮም ፈረንጅም ተሳፍረው ተመለከትኩ፡፡ በተለይ ፈረንጅ በአውቶብስ ላይ መሳፈሩና ተሳፋሪውን ለሁለት በከፈለ ክርክር ውስጥ መዶሉ አስገርሞኛል፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ድርጅት መቋቋም ሰበቡ ፈረንጆች ናቸው፡፡ በ1933 ዓ.ም ጣሊያኖች ትተዋቸው በሄዱት 10 ያህል አውቶብሶች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ድርጅቱ፤ ባለፈው ዓመት 70ኛ የምሥረታ ዓመቱን አክብሯል፡፡ ድርጅቱ በሚሰጠው አገልግሎት ግን ፈረንጆች እምብዛም ሲጠቀሙበት አይታይም፡፡ ፈረንጆች አውቶብስ የመጠቀም ልማድ የላቸው ይሆናል እንዳንል ደግሞ በአገራቸው ከዋናዎቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተጠቃሾቹ አውቶብሶች ናቸው፡፡ በእርግጥ እዚያ እንደኛ አገር መጠቅጠቅ የለም፡፡  
አብዛኞቹ የአማርኛ መዛግብተ ቃላት “ፈረንጅ” ለሚለው ቃል “የቆዳ ቀለሙ ነጭ የሆነ፣ የውጭ አገር ሰው” ብለው ነው የሚተረጉሙት፡፡ መዛግብተ ቃላቱ እንዲህ ይተርጉሙት እንጂ ህብረተሰቡ ደግሞ የተለያዩ አመለካከቶችና አተያዮች አሉት - በፈረንጅ ዙሪያ፡፡
ጣሊያንን ከአንድም ሁለት ጊዜ ከማሸነፋችን ጋር በተያያዘ “ነጭና ጥቁር የቆዳ ቀለም ባላቸው ሰዎች መሐል ምንም ልዩነት የለም፤ ሁለቱም በአዳም አምሳያ የተፈጠሩ ናቸው” የሚል አስተሳሰብ ሰፍኗል፡፡ የአፄ ምኒልክ አነጋገር ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ “ፈረንጅ እንደኛው ሰው ነው፡፡ ለገበያ ያቀረበው ዕውቀትም ይሁን ጉልበት ካለው ከፍለነው መጠቀም እንችላለን” ብለው ያምኑ ነበር - ምኒልክ፡፡
“አጤ ምኒልክ” በሚል ርዕስ በጳውሎስ ኞኞ ተዘጋጅቶ፣ በ1984 ዓ.ም ለንባብ በበቃው መጽሐፍ ውስጥ በየስ የተባሉ ታሪክ ፀሐፊ፤ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ያጋጠማቸውን እንግዳ ሁኔታ በአንደበታቸው አስቀምጦታል - “…. በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ተዘዋውሬ አዲስ አበባ ስመጣ አዲስ ነገር አጋጠመኝ፡፡ ይህም አንድ አፍሪካዊ፣ ነጮችን እያዘዘ፣ ቤት ሲያሰራ ማየቴ ነው…. ኢትዮጵያዊያኖቹ ፈረንጆቹን የሚጠሯቸው ባሪያዎች እያሉ ነበር፡፡”
ታሪክ ፀሐፊው በየስ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የአፍሪካ አገራት ያዩትን ነገር በኢትዮጵያ መጠበቃቸው ይመስለኛል ነገሩን እንግዳ ያደረገባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ቅኝ አለመገዛታቸውን ካሰቡት ግን ብዙም የሚገርም ነገር የለውም፡፡ እንዴት አንድ ጥቁር ፈረንጅን “ባሪያ” ይለዋል ካልተባለ በቀር፡፡
ሰው የቆዳ ቀለሙ ቢነጣም፣ ቢጠቁርም በሰውነቱ ሁሉም እኩል ነው ብለው ከሚያምኑት በተቃራኒ፤ እንደ ታሪክ ፀሀፊው በየስ፤ ትልቅ ነገር በማሰብ፣ በመስራትና ስኬታማ በመሆን ነጮች ከጥቁር ሕዝቦች የተሻለ አፈጣጠር አላቸው ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያንም አሉ፡፡ እነዚህ ለፈረንጆች ልዩ አመለካከት አላቸው፡፡ ፈረንጆች ገዢ እንጂ ተገዢ አይደሉም፤ ሀብታም እንጂ ደሀ የለባቸውም …. ብለው ያምናሉ፡፡ ለዚህ እምነታቸውም፣ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡
ባለፈው ሳምንት ከለገሀር ወደ ሽሮሜዳ በሚሄደው 31 ቁጥር አንበሳ አውቶብስ ውስጥ አንድ ፈረንጅ ተሳፍሮ በመታየቱ ምክንያት፣ ተሳፋሪዎችን ለሁለት የከፈለ ክርክር የተነሳውም ለፈረንጆች ሁለት የተለያየ አመለካከት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በአውቶብሱ ውስጥ ስለነበሩ ነው፡፡ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ሀሳብ የሰነዘረው ወጣት፤ “እንዴት ከእኛ ጋር ተሳፍሮ እራሱን ያንገላታል?” የሚል ተንኳሽ ጥያቄ ነበር ያቀረበው፡፡
ለምን? እንዴትና በምን ምክንያት እራስህንና ኢትዮጵያዊያንን ዝቅ አድርገህ፤ ፈረንጅን ከፍ ታደርጋለህ? የሚል ሞጋች ጥያቄ እየቀረበ፤ ከግራና ከቀኝ ምላሽ እየተሰጠ ክርክሩ ቀጠለ፡፡ በሙግቱ የረታ ግን አልነበረም፡፡ በድጋፍና በተቃውሞ ከየአቅጣጫው ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ ክርክሩን ለማርገብ የሞከሩ አልጠፉም “ኧረ ለእንግዳና ሰው አክባሪው መልካም ባህላችን ስትሉ ዝም በሉ” በሚል ግሳፄ፡፡ “ፈረንጁ አማርኛ ብቻ ሳይሆን ግዕዝን ጭምር አቀላጥፎ ያውቅ ይሆናል፤ እንጠንቀቅ እባካችሁ” የሚል ማሳሰቢያም በሹክሹክታ ተሰምቷል፡፡ ማሳሰቢያው ባልከፋ፡፡ ክፋቱ ግን ስንት ነገር ከተባለ በኋላ ሆነ እንጂ፡፡ አንድ ወጣት ተሳፋሪ ደግሞ ለራሱ ለፈረንጁ ስለጉዳዩ በእንግሊዝኛ ማብራሪያ ለመስጠት እየሞከረ ነበር፡፡   
የአውቶብስ ውስጥ ክርክሩ ከአዕምሮ ጅምናስቲክነቱ ባሻገር የሚያስተላልፈው መልዕክትም አለ፡፡ ቀደምት አባቶች ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ነፃነት የከፈሉት መስዋዕትነት ፋይዳው የሚገባው ትውልድ እንዳለ በአንድ በኩል ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፈረንጅ አምላኪዎች መኖራቸውንም ይጠቁማል፡፡
ለመሆኑ ፈረንጆች በከተማ አውቶብስ አይሳፈሩም የሚለው ልማድስ እንዴትና በምን ምክንያት ዳበረ? ያለ ልዩነት ለሁሉም ሰዎች አገልግሎት የሚሰጠው የከተማ አውቶብስ ድርጅት፤ ዶሮ ላይ የጫነው እግድ ግን ለሐበሻ ብቻ ሳይሆን የፈረንጅ ዶሮንም ይመለከታል፡፡ ድርጅቱ ተገልጋዮቼ ማክበር አለባቸው ብሎ በየአውቶብሶቹ በለጠፋቸውና ለቅጣት ይዳርጋሉ ከተባሉ ድርጊቶች አንዱ የቤት እንስሳትን መጫን  ነው፡፡
የቤት እንስሳት በመሆኗ በከተማ አውቶብስ እንዳትሳፈር እግድ የተጣለባት ዶሮ፤ ፋሲካና ሌሎች በዓላትን ከማድመቅ በላይ ባለ ብዙ ታሪክ ናት፡፡ በዶሮ ዙሪያ አስተማሪና አዝናኝ ተረቶች ይነገራሉ፡፡  ዶሮ የቤት እንስሳ ከመሆኗ በፊት ምድቧ ከሰማይ አእዋፋት ነበር አሉ፡፡ በአንዱ ጎዶሎ ቀን አንድ ክንፏ ተገንጥሎ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ከንስር አሞራ መርፌ ተውሳ፣ ክንፏን ሰፍታ ስትጨርስ መሬት ላይ የወደቀው መርፌ ድራሹ ጠፋ፡፡
“የተዋስሽኝን መርፌ እስክትመልሽልኝ ድረስ የእኔና የአንቺ ወዳጅነት በታሪካዊ ጠላትነት ተቀይሯል” ብሎ ንስር አሞራ አቋሙን አሳወቃት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ንስር አሞራ የዶሮ አሳዳጅ ዋነኛ ጠላቷ ሆነ፡፡ ዶሮም የጠፋባትን መርፌ ፍለጋ መሬት መጫሯን ቀጥላለች፡፡ የሐበሻ ዶሮ የዚህ ታላቅ ታሪክ ባለቤት ናት- አፈ ታሪክ እንደሚለው፡
የሐበሻ ዶሮ እንደ ሕዝቡ ለፍቶ አዳሪ ናት፡፡ ሆነ ብሎ ቀለበት የሚሰፍርላት የለም፡፡ መሽቶ እስኪነጋ መሬት ትጭራለች፡፡ የምትንቀውና የምትጠየፈው ነገር የለም፡፡ ጥራ ግራ ነው አካሏን የምትገነባው፡፡ የሐበሻ ዶሮ እንቁላልም ሆነ ሥጋው ከፈረንጁ ዶሮ የበለጠ ተፈላጊ ነው፡፡ እንቁላልና ሥጋው መድሀኒትነት አለው ብሎ ሐበሻ ያምናል፡፡ ምክንያቱም መሬት ጭራ ብዙ ነገር ስለምትበላ ነው፡፡ የሐበሻ ዶሮ ስትበለትም ወርቅ የሚገኝበት አጋጣሚ አይጠፋም፡፡ ብዙ ሴቶች የዶሮ መቋደሻ ላይ ጥብቅ ፍተሻ የሚያደርጉት ያለምክንያት አይደለም፡፡
አሁንማ ዕድሜ ለኑሮ ውድነቱ! የሐበሻ ዶሮንና የፈረንጅ ዶሮን እኩል ተፎካካሪ አደረጋቸው እንጂ ሀበሻ ለበዓላት ማረድ የሚመርጠው የሃበሻ ዶሮን ነበር፡፡ በተለይ ዶሮ ወጥ ላይ ጣዕማቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው ይባላል፡፡
የፈረንጅ ዶሮ፤ ቦታው ሆቴልና ሱፐር ማርኬት ነበር - እንደዛሬው በየቤቱ ሳይገባ፡፡ ፈረንጆቹንም የከተማ አውቶብስ ተገልጋይ ያደረጋቸው የኑሮ ውድነቱ ይሆን እንዴ? በሰሞነ ህማማት ዶሮ የተጣለባትን ሕግ ጥሳ በከተማ አውቶብስ እንደምትሳፈረው፤ ፈረንጆቹም ግርግሩን ተጠቅመው ይሆን እንዴ የቆየውን ልማድ ሰብረው በከተማ አውቶብስ ውስጥ የታዩት?
የሆነ ሆኖ “ፈረንጅ እንዴት ከእኛ ጋር ተሳፍሮ እራሱን ያንገላታል?” የሚለው የአውቶብሱ የክርክር መነሻ ሀሳብ ለተጨማሪ ውይይት የሚጋብዝ ከሆነ አሊያም ሌሎች ሃሳቦችን ከጫረባችሁ ልታካፍሉን ትችላላችሁ፡፡ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡ መልካም የዳግማይ ትንሳኤ በዓል!!!

Read 4091 times