Print this page
Saturday, 26 April 2014 12:45

የጠፋው የማሌዥያ የመንገደኞች አውሮፕላን፤ የአካባቢው የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ

Written by  በኃይለገብርኤል እንደሻው ከመነን gizaw.haile@yahoo.com
Rate this item
(6 votes)

       ንብረትነቱ የማሌዥያ የሆነው ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን እንደወጣ መቅረት፣ ዛሬም ቢሆን ሁላችንንም እያስገረመ ያለና የዘመናችን ያልተፈታ አዲስ እንቆቅልሽ ነው ማለት ይቻላል።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከማሌዥያዋ መዲና ኩዋላ ላምፑር ወደ ቻይናዋ ቤይጂንግ 239 ሲቪል መንገደኞችንና የአውሮፕላኑን ሰራተኞች አሳፍሮ ይበር የነበረው አውሮፕላን ከእይታ የተሰወረው በረራ በጀመረ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነበር።
ከአንድ ወር ከሳምንት በፊት ደብዛው የጠፋው ቦይንግ 777 አውሮፕላን ከጫናቸው መንገደኞች አብላጫ ቁጥር ያላቸው (153 ያህል ይሆናሉ ነው የሚባለው) የቻይና ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።
ይሄ ፅሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ አውሮፕላኑን ለማፈላለግ ከ24 በላይ ሃገሮች የተውጣጡ 60 የሚሆኑ አውሮፕላኖችና መርከቦች ቢሰማሩም፣ እስካሁን ድረስ ተስፋ ሰጪ ውጤት አልተገኘም። እንደውም ለረጅም ጊዜ በደቡባዊው የቻይና ባህር ላይ ይደረግ የነበረው ፍለጋ ወደ ደቡባዊው የህንድ ውቅያኖስ እስከዞረበትና አውስትራሊያ በሰፊው እስከተሳተፈችበት ጊዜ ድረስ ቅንጅት አልነበረውም ተብሎለታል።
ለመሆኑ የጠፋውን አውሮፕላን በማፈላለጉ ስራ ላይ ሃያሏ አሜሪካ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በስፋት ያለመሳተፏ ምክንያቱ ምን ይሆን? ይሄ አሁን አሁን ሁሉንም እያነጋገረ ያለ ጥያቄ ሆኗል። ይሄ ጥያቄ አሜሪካ ካላት የቴክኖሎጂ አቅምና በሌሎች መሰል አደጋዎች ካካበተችው ተሞክሮ አንፃር፣ ልታበረክተው የምትችለውን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰነዘረ ነው።
የየሃገራቱ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክርና የፖለቲካ ጨዋታ ምናልባት የጠፋውን አውሮፕላን የጦስ ዶሮ አድርጎት ሊሆን ይችላልም እየተባለ ነው። ይህ አጭር ፅሁፍ እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን በመዳሰስ ለውይይት የሚሆኑ መነሻ ሃሳቦችን ለመሰንዘር ይሞክራል።
ከፍተኛና ውስብስብ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ያስፈልጉታል የተባለለት የአውሮፕላኑ ፍለጋ፣ የሃያሏን አሜሪካ ተሳትፎ ገና ከጅምሩ መጠየቁ ብዙዎችን ያሳመነ ይመስላል። ለዚህ ጉዳይ በዋናነት የሚነሱት ሙግቶች አሜሪካ ያሏትን እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በእማኝነት ያስደገፉ ናቸው። አውሮፕላኑ ተሰወረ በተባለበት አካባቢ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች የተከማቹት የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑት እነዚህ መሳሪያዎች ለፍለጋው ስኬታማነት እጅግ ወሳኝ ናቸው መባሉም የቆዩ መሰል አደጋዎች በተከሰቱ ጊዜ የተገኘውን አመርቂ ተሞክሮ በዋቢነት በመጥቀስ ነው።  
በ2009 በደቡባዊው አትላንቲክ ዳርቻ የተከሰከሰውንና ንብረትነቱ የፈረንሳይ የሆነውን የ447 አውሮፕላን ስብርባሪና የድምፅ መቅረጫ ጥቁር ሳጥንን በባህር ጠላቂ ዘመናዊ ተ,ሐከርካሪዎቿ ለቃቅማ በማውጣት አለምን ያስደነቀችው አሜሪካ፣ በጠፋው የማሌዥያ ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን ፍለጋ ላይ በሙሉ ሃይሏ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት ያለማሳየቷ በርግጥም ምን ምክንያት ቢኖራት ነው ያስብላል።
ከዚህ ጋር በተዛመደ ይህ ደብዛው የጠፋው አውሮፕላን ለአሜሪካኖቹ አንድ ዕድል ይዞላቸው እንደመጣም በሰፊው ይወራል። ከዓለማችን በቴክኖሎጂ እርምጃ የመጀመሪያው ጫፍ ላይ የምትገኘው አሜሪካ፤ በዘመናችን ብቅ እያለች የመጣችውን አዲሲቷን ተቀናቃኝ ሃገር፣ ቻይናን፣ ለመፈተን ከመፈለግ አንፃር ራሷን ከፍለጋው ያገለለች ይመስላል የሚለው ሚዛን የደፋ ጉዳይ እየሆነ ነው።
አሜሪካ፣ ቻይና ያመጠቀቻቸውን ሳተላይቶች ብቃት ለመፈተንና የዚያችው ሃገር ስሪቶች የሆኑ ሚሳይሎች ምናልባት በአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿ ላይ ሊያደርሱ ይችሉ ይሆናል ተብሎ የሚገመተውን ጥቃት ለመፈተሽ አጋጣሚውን እየተጠቀመችበት እንደሆነ ነው ዓለም እያወራ ያለው። “ዋንት” የተባለው የታይዋኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘጋቢ ኤሪክ ሺህ እንደሚለው፤ አሜሪካ የአውሮፕላኑን ፍለጋ ውጤታማ የሚያደርጉ የተሻሉና ብቁ የሆኑ የስለላ ሳተላይቶችና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት ብትሆንም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምርጫዋ ዝምታ ብቻ ሆኖ ቆይቷል። እንደ ኤሪክ አባባል አሜሪካ የጠፋውን የማሌዥያ ኤም ኤች 370 አውሮፕላን በማፈላለጉ ስራ ላይ ላለመሳተፍ ስታንገራግር የቆየችው፣ የቻይና ሳተላይቶች ጉዳዩን አስመልክተው የሚያቀርቡትን ምስጢራዊ መረጃ ለማወቅ ከመፈለግ የተነሳ ነው።
ይሄ ጉዳይ ሌላውን የዘመናችንን ሀቅ እንድናስታውስም ያደርገናል። የሶማሌዎችን የባህር ላይ ውንብድና ለመከላከል በሚል በሰሜናዊው የህንድ ውቅያኖስ ላይ የተሰባሰቡት ሃገሮች፣ ሃያላኑን ጨምሮ፣ ፋታ ባገኙ ቁጥር በእርስ በእርስ ስለላና የፍተሻ ቁጥጥር ራሳቸውን ወጥረው መገኘታቸው፣ አሁን እያወጋን ስላለው ታላቅ የመሆን ፉክክር አንዱ ማሳያ ነው።
ብቅ ጥልቅ እያሉ በአካባቢው የሚጓዙ መርከቦችን ሳይታሰብ በድንገተኛ ጥቃቶቻቸው የሚያስደነግጡትን የምስራቅ አፍሪካ ዘራፊዎች ለማደን ግንባር የፈጠሩት እነዚህ ጉልበተኛ ሃገሮች፣ የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ጥቃት ጋብ ሲልላቸው የሚያደርጉት የእርስ በርስ የመፈታተሸ ወይም የመሞካከር ባህሪያቸው፣ ጅብ ሲመጣ ግንባር እንደሚፈጥሩትና ሲሄድ ደሞ እንደሚነካከሱት ውሾች ዓይነት ይመስላል።
እነዚህንና መሰል የዓለማችን ሃያላን ሃገራትን የጎሪጥ መተያየት ምክንያት በማድረግ ነው፣ ሮይተር በመጋቢት 28፤ 2014 ዕትሙ “በጂኦ ፖለተካዊ ጨዋታ ፍለጋው የተስተጓጎለው ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ ያቀረበው።
ሌላው አሜሪካንን በፍለጋው ላይ ወሳኝ ሚና ልትጫወት ትችላለች የሚያስብለው ምክንያት ወደ ጠፈር ያስወነጨፈቻቸው መረጃን የሚያቀብሉ ዘመናዊ ሳተላይቶች ባለቤት መሆኗ ነው። ሚያዚያ 6፣ 2012 አሜሪካ ከካልፎርኒያ ቫንደርበርግ የአየር ሃይል ጣቢያ የተኮሰችውና NROL-25 የሚል ስያሜ የተሰጠው የስለላ ሳተላይት ቀን  ለሊት ሳይል ጥቅጥቅ ደመናዎችን ሰንጥቆ በማለፍ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወታደራዊ ምሽጎችን፣ ተፈላጊ ዒላማዎችንና ሌሎችንም ተንቀሳቃሽ አካሎችን የማየት ሃይል እንዳለው ይነገራል። ይሄ በምስጢር ወደህዋ የተወነጨፈው ሳተላይት፣ በመቶ ማይሎች ከሚቆጠር ርቀት ላይ የሚገኙና በመጠን ያንድ ትልቅ ሰው ቡጢን የሚያህሉ አናሳ ነገሮችን እንኳን ሳይቀር እጅግ አጉልቶ የማሳየት ብቃቱ አስደናቂ ነው ተብሎለታል።
ይሄም ብቻ አይደለም። ይችው የዘመናችን ሃያል ሃገር አሜሪካ፣ በታህሳስ 2013 NROL-39 በሚል ስያሜ የሚጠራ አዲስ የስለላ ሳተላይት ወደ ህዋ ልካለች። አዲሱ ሳተላይት ከረጅም ርቀት ላይ ሆኖ በምድር ላይ ያሉ ተፈላጊ ነገሮችን መንጥሮ የማንሳት ችሎታው፣ ኦክታፐስ የሚል ስያሜን አሰገኝቶለታል። ይሄ የባህር ዓሣ ዝርያ፣ ኦክታፐስ፣ በርካታ እግርና እጆቹ ያሻውን የባህር ላይ አውሬ በቀላሉ ለመጥለፍ እንደሚያስችሉት ሁሉ፣ አዲሱ ሳተላይትም በተመሳሳይ ክንውኑ የሱን ስም እንዲወስድ ተደርጓል። የአሜሪካ ጠላት የሆነ ሁሉ፣ የትም ሆነ የት (ምጥ ይግባ ስምጥ) ከዚህ ሁሉ በእጁ ከሆነ ዘመናዊ የስለላ ሳተላይት እይታ ውጭ መሆን አይችልም። ራሳቸው አሜሪካኖቹ የመሳሪያውን ብቃት አስመልክተው ሲናገሩ nothing is beyond our reach ይላሉ።
እንግዲህ የዘመናችን ጉልበተኛዋ ሃገር፣ አሜሪካ፣ እነዚህንና መሰል ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ታጥቃ ነው ደብዛው በጠፋው በኤም ኤች 370 አውሮፕላን ፍለጋ ላይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ላለመሰማራት የፈለገችው። ከጥቂት ቀናት በፊት በባህር ሃይሏ በኩል በፍለጋው ላይ መሳተፍ እንደጀመረች መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ ብዙዎች ስለ ውጤታማነቱ ይጠራጠራሉ። የአሜሪካን ተሳትፎ “ከልብ ያልሆነ ወይም ካንገት በላይ የሆነ የዘገየ ተሳትፎዋ” በሚል ሌላው አሜሪካንን ባውሮፕላኑ ፍለጋ ላይ ውጤታማ ሚና ልትጫወት ትችላለች የሚያስብለው ሙግት አሳማኝ የሚሆነው ባካባቢው ባላት ወታደራዊ ጣቢያ ውስጥ ባደራጀቻችው ከፍተኛ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎቿ ብቃት ነው።
ንብረትነቱ የማሌዥያ የሆነው ኤም ኤች 370 የመንገደኞች አውሮፕላን ጠፋ በተባለበት ደቡባዊው የህንድ ውቅያኖስ ላይ አንዲት የውስጥ እግር ምስል ያላትና ዲያጎ ጋርሺያ እየተባለች የምትጠራ ደሴት ትገኛለች። ይህች ደሴት እ.ኤ.አ. እስከ 1966 ድረስ በእንግሊዝ ንብረትነት ተይዛ እንደቆየች ይነገራል። እንግሊዝ በጦር መሳሪያ ግዢ ሰበብ አሜሪካ ላይ የነበረባትን የ14 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ለማካካስ በሚል ነበር አሜሪካ ደሴቲቱን ለወታደራዊ ግልጋሎት እንድትጠቀምበት የፈቀደችላት። ሃያሏ ሃገር አሜሪካ ደሴቲቱን እንደተረከበች በውስጧ የሚኖሩትንና ቁጥራቸው 2,000 የሚሆነውን ቻጎሳውያን በድብቅ አፍሳ በ1,200 ማይልስ ርቀት ላይ ወደሚገኙት ሞሪሺየሰና ሲሺየልስ በጀልባ በማጓጓዝ አስፍራቸዋለች። አሜሪካ ያንን ብቻ በማድረግ አልተገታችም። የቻጎሳውያኑን ውሾችም ሰብስባ ነዋሪዎቹ ዓይናቸው እያየ በመርዝ ጋዝ አጋይታቸዋለች። ጉዳዩ ከዓለም ሕዝብ እይታ ተሰውሮ ይቆይ ዘንድ ሙከራ ቢደረግም፣  በአሜሪካ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ‘Island of Shame’… ወይም “የቅሌቱ ደሴት፣ የዩ. ኤስ. አሜሪካ ወታደራዊ ምስጢር በዲያጎ ጋርሺያ” በሚል ርዕስ በተፃፈ መፅሐፍ ሊጋለጥ ችሏል።
በደሴቲቱ የተቋቋመው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ጠፈር ጠቃሽ የቅኝት መሳሪያዎች ከተከማቹባቸው በጣት ከሚቆጠሩ የዓለማችን ወታደራዊ ጣቢያዎች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። ዛሬ የዲያጎ ጋርሺያ ወታደራዊ ደሴት ቢ-52ና ቢ-2ን የመሳሰሉ እጅግ ዘመናዊ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖችን ጨምሮ፣ ሌሎች የጦር መሳሪያ ክምችቶችና የስለላ መሳሪያዎች የሚገኙበትና አሜሪካ አሏት ከሚባሉት 1,000 መሰል የጦር ሰፈሮች አንዱ፣ ምናልባትም ዋንኛው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሜሪካ ይሄን በወታደራዊ የመጓጓዣ ዘዴ ብቻ የሚደረስበትን ደሴት፣ አፍጋኒስታንንና ኢራቅን ለመደብደብ መነሻና መድረሻ አድርጋ ከመገልገሏም በላይ፣ በሽብር ወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችንም ለማሰርና ለማሰቃየት እንደምትጠቀምበት ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። ወታደራዊ ጣቢያው ውቅያኖስ ወለል ድረስ ጠልቀው በመግባት ብረት ነክ ነገሮችን መልቀም የሚችሉ መሳሪዎች እንደተከማቹበትም ታውቋል።
ታዲያ በፍለጋው ላይ ከጅምሩ አንስቶ በሙሉ ልቧ አሜሪካ ተሳትፋ ቢሆን ኖሮ፣ ያ የጠፋው  የማሌዥያ አውሮፕላን በቅርብ ርቀት በዲያጎ ጋርሺያ ላይ ከሚገኙት የስለላ መሳሪያዎች እይታ ውጭ ይሆን ነበር? ብለው ይጠይቃሉ- ታዛቢዎች።
ከአመታት በፊት ተመሳሳይ የብልጣብልጥነት ልግመት ወይም ቸልተኝነት ከአሜሪካ በኩል ተስተውሎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በታህሳስ 2004 በህንድ ውቅያኖስ ላይ ተከስቶ የነበረው የሱናሚ አደጋ ለዚህ እንደማሳያነት ይጠቀሳል። የአሜሪካ ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት ተቋም ቃል አቀባይ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማረጋገጫ፤ የሱናሚ አደጋው በታህሳስ 26፣ 2004 የሴሪላንካንና የታይላንድን የባህር ዳርቻዎች ከመምታቱ አስቀድሞ፣ የተቋሙ የሃዋይ ማዕከል ለዋሺንግተንና በዲያጎ ጋርሺያ ደሴት ላይ ለሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምልክት ማስተላለፉን አስታውቋል። ቃል አቀባዩ አክሎ እንደተናገረው፣ የዲያጎ ጋርሺያው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ሃላፊዎች ባካባቢው ላሉ ሃገሮች ተመሳሳይ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መልእክት ስለማስተላለፋቸው የታወቀ ነገር የለም።
ያም ሆነ ይህ፣ ሃያሏ አሜሪካ ማድረግ የምትችለውን ብቻ ሳይሆን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን የፍለጋ ትብብር አስቀድማ በሙሉ ልቧ ለማድረግ ባለመፍቀዷ የማሌዥያው አውሮፕላን እስካሁን ድረስ የደረሰበት ሳይታወቅ ቀርቷል።
አሁንም ቀኖች እየነጎዱ በሄዱ ቁጥር፣ የዚህ አውሮፕላን ጠፍቶ መቅረት ሁሉንም ሰብአዊ ዜጋ እንዳስጨነቀው ነው። ከጎረቤት ሃገሮች ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የራዳር መረጃዎችን ለማግኘት እንኳን ያልታደለችው ማሌዥያ፤ ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ ስትገኝ፣ ደብዛው የጠፋው አውሮፕላኗ ደሞ በድብቁ ያካባቢው የፖለቲካ ጨዋታ ሰበብ ወጥመድ ላይ የተጣለ ቁራጭ ስጋ ሆኖ የቀረ ይመስላል።

Read 4753 times